Ethiopian currency note
Ethiopian currency note

እንደ ኢትዮጵያ ያለ በዜጎቹ ዝቅተኛ ዕምነት የተጣለበት መንግስት የመገበያያ ገንዘብ ኖት ሀገር ውስጥ አሳትማለሁ ሲል ቀልብ መሳቡ አይቀርም፤ እንዴት? የሚል ጥያቄም ያስከትላል፡፡ መንግስት ግን… የኢትዮጵያ መገበያያ የገንዘብ ኖት፣ ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት እና ቼክን የመሳሰሉ ምስጢራዊ ሕትመቶችን በሀገር ውስጥ ለማተም ዝግጅት መጨረሱን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡

[ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን ሪፖርት መሰሉ ንጉስ ታቀርበዋለች]

በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኘው የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት አመራሮች የገንዘብ ኖት በማተም የዓመታት ልምድ ካለው “ሱዳን ከረንሲ ፕሪንቲንግ ፕሬስ” (SCPP) ኃላፊዎች ጋር ባለፈው ሳምንት ተወያይተዋል፤ የመግባቢያ ሰነድም ተፈራርመዋል፡፡… ማተሚያ ድርጅቱ ከሁለት ዓመት በፊት ያወጣውን ጨረታ ሲያራዝመው ቆይቶ የዛሬ ዓመት በየካቲት 2007 ዓ.ም ከአስራ ሁለት ተወዳዳሪ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መሀከል የጀርመኑ Koenig & Bauer AG (KBA) በአሸናፊነት መርጧል፤ የባንክ ቼክ ማተሚያ ማሽን ተከላውን በማካሄድ ላይ የሚገኘውም ይሕ የጀርመን ኩባንያ ነው፡፡
በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ መሰረት የሱዳኑ ገንዘብ አታሚ SCPP የረጅም ዓመታት ልምዱን ለብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ያካፍላል፡፡ በKBA እየተተከለ ባለው ማሽን በቀጣዩ ዓመት የቼክ ሕትመት ሥራው ይጀመራል፡፡ ጊዜው መቼ እንደሆነ ባይጠቀስም በቀጣይነት የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት እና የመገበያያ ገንዘብ ኖት ህትመት ሥራ ለመጀመር እየተንደረደረ መሆኑንም ኃላፊዎች አሳውቀዋል፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የብርሐን እና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተካ አባዲ “…የገንዘብ ኖት፣ ኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርት እና ቼክ በሃገር ውስጥ መታተማቸው ሃገሪቱ የምታወጣውን የውጪ ምንዛሪ ከማዳን ባሻገር ለደህንነት ጭምር በእጅጉ ጠቃሚ ነው” ሲሉ መናገራቸውን ከመንግስታዊው ኢትዮጵያን ሄራልድ መመልከት ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ የራሷን ገንዘብ ኖት ታሳትም ዘንድ ልምዱን እንዲያካፍል የተመረጠው “ሱዳን ከረንሲ ፕሪንቲንግ ፕሬስ” (SCPP) እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1994 ዓም ነው በግል ኩባንያነት ተመዝግቦ ሥራውን የጀመረው፡፡ ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርትን ጨምሮ ሁሉም ዓይነት የሱዳን መገበያያ ኖቶች የሚመረቱት በዚሁ ተቋም ነው፡፡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኝ፣ የረቀቀ የሕትመት ቴክኖሎጂን የሚጠቀመው (SCPP) የጎረቤት ሃገራት ምስጢራዊ ትሕመት ውጤቶችን የሚሰራ ሲሆን፣ ለምሳሌ ያሕል የሶማሊያን መገበያያ ገንዘብ እንደሚያትም ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራም የዚህ ዘመናዊ ሕትመት ተቋም ደንበኞች ናቸው፡፡

 በአሕጉረ አፍሪካ እና በአረብ ክልል የራሳቸውን መገበያያ ገንዘብ የሚያትሙ ሃገራት ስምንት ብቻ ሲሆኑ… እነሱም ግብጽ፣ አልጀሪያ፣ ሞሮኮ፣ ናይጀሪያ፣ ሳውዝ አፍሪካ፣ ኮንጎ፣ ዚምባብዌ፣ እና ሱዳን ናቸው፡፡

ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ የተገኘው ወቅታዊ መረጃ እንደሚያመላክተው በሃገሪቱ ስምንት መቶ ሠማንያ ስድስት ማተሚያ ቤቶች በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በምስጢር ሕትመቶች ላይ የተሰማራው ግን ብርሃንና ሠላም ብቻ ነው፡፡ ፓስፖርት፣ ሎተሪ፣ የአውቶቡስ ቲኬት፣ የባንክ ቼክ፣ መንጃ ፈቃድ፣ ብሔራዊ ፈተናዎች፣ ሠርቲፊኬቶችን… ወዘተ የሚያትመው ይሄው ተቋም ነው፡፡ ሆኖም ከዘመኑ የሕትመት ቴክኖሎጂ ጋር መጓዝ ባለመቻሉ የመንግስት ተቋማት ደንበኞቹ ሳይቀሩ ጥለውት እየሄዱ፣ ሌላ የውጪ ሃገር አታሚ ሲያፈላልጉ ነው የሚስተዋለው፡፡

ማተሚያ ድርጅቱ የረቀቀ ጥበብና ቴክኖሎጂ ወደሚጠይቀው የመገበያያ ገንዘብ ኖት ማተም ሥራ እንደሚገባ በገለጸበት ሰሞን እንኳን ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያዘጋጅ የነበረውን ቀረጥ መሰብሰቢያ ቴምብር ማቅረብ ባለመቻሉ ብዙ ችግር ተፈጥሯል፡፡ በባንኮች፣ በኢንሹራንስ ተቋማት፣ ፍርድ ቤቶች፣ በፖስታ አገልግሎት፣ የውልና ማስረጃ ዶክመንቶች ማረጋገጫና ምዝገባ የሚከናወነውም ሆነ ገቢ የሚሰበሰበው በተጠቀሱት ቴምብሮች ቢሆንም፣ ማተሚያ ቤቱ ግን ባለ ማጣበቂያው የቴምብር ወረቀት እጥረት አለብኝ በሚል ሠበብ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ ማሳወቁ ብርሐን እና ሰላም የት እንዳለ ማመላከቻ ነው ተብሏል፡፡
በሃገር ውስጥ የመገበያያ ገንዘብ ኖት የማተም ፍላጎት መኖሩ… በብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች መገለጽ ከጀመረ ሶስት ዓመት አልፎታል፡፡ በሰኔ 2005 ዓ.ም የባንኩ ከፍተኛ ሹማምንት ወደ ሱዳን በመጓዝ ከአሕጉሪቱ እጅግ ዘመናዊ ማተሚያ ተቋማት አንዱ የሚባለውን SCPP የጎበኙትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ ብሔራዊ ባንክ በታሕሳስ 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ባወጣው የጨረታ ማስታወቂያ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የገንዘብ ኖት ማተሚያ ቤት ለማቋቋም ይቻል ዘንድ ጥናት የሚያደርጉ አማካሪ ተቋማት እንዲሳተፉ ጠይቆ ነበር፡፡ በብሔራዊ ባንክ ባለቤትነት ሥር የሚሆን አዲስ የገንዘብ ኖት ማተሚያ ቤት ለማቋቋም በወጣው የመጀመሪያ ዙር ጨረታ… ከአምስት አስከ ሰባት የሚደርሱ ዓለም ዓቀፍ አማካሪ ድርጅቶች ይሳተፉበታል የሚል ግምት ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ መመዘኛው ሳይሳካ በመቅረቱ ሁለተኛ ዙር ጨረታ ወጥቶ ነበር፡፡ በዚህም ዙር የቀረበውን መስፈርት የሚያሟላ በመጥፋቱ ተሰረዘ እንጂ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ኖቶችን የሚያሳትመው በአውሮፓ ሲሆን፣ ዋና ደንበኞቹም የፈረንሳዩ “ኦበርቱር ቴክኖሎጂ” እና የዩናይትድ ኪንግደሙ “ደ ላ ሩ” ናቸው፡፡ የዓለማችን ግዙፉ ኖት አቅራቢ የሆነው “ደ ላ ሩ” DELARU ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአንድ እና የአምስት ብር ሕትመቶችን ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን፣ “ኦበርቱር ቴክኖሎጂ” ደግሞ የ50 እና 100 ብር ኖቶችን እያተመ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

አብላጫውን ጊዜ ኩባንያዎቹ ገንዘብ እንዲያትሙ ከብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ የሚላክላቸው በዝውውር ላይ የሚገኙ የባንክ ኖቶች ከአገልግሎት ውጪ ሆነው ከተቃጠሉ በኋላ ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ካለው የብር ማቃጠያ ባሻገር… የአገልግሎት ጊዜያቸው አብቅቶ የሚወገዱ ኖቶች የሚቃጠሉት መተሐራ ስኳር ፋብሪካ በሚገኝበት ወንጂ ከተማ ነበር፡፡ ባንኩ ባለፈው ዓመት “ጂ ኤንድ ኬ” ከተሰኘ የጀርመን ኩባንያ አዲስ ማሽን ከገዛ በኋላ ግን ብር ማቃጠል ቀርቶ፣ በማሽኑ አማካኝነት የሚወገደው የገንዘብ ኖት ወደ ጡብ ማምረቻ ኬሚካልነት ይቀየራል ተብሏል፡፡