• “የቲቪ ግብር ክፈሉ!” የቤት ለቤት ዘመቻ ተጀመረ
Birhane KidaneMariam, Photo credit ENA
Birhane KidaneMariam, Photo credit ENA

ዋዜማ ራዲዮ- ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት ሲካሄድ የሰነበተው የኢቲቪ/ኢቢሲ ጋዜጠኞች ጥልቅ ተሀድሶና ግምገማ በዋቢሸበሌ ሆቴል ተጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል ተጠናቋል፡፡ በመዝጊያው ሥነ ሥርዓት ላይ የድርጅቱ የቦርድ ሊቀመንበርና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ተገኝተዋል፡፡

በጥልቅ ተሀድሶው ወቅት በርካታ የከረሩ የብሶት ድምጾች ከሠራተኞች የተሰሙ ሲኾን አንድ ጋዜጠኛ  ለግማሽ ቀንና ለአንድ ሙሉ ቀን የተገመገመበት አጋጣሚ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ብዙዎቹ የግምገማ ነጥቦች ከጥቅማ ጥቅም፣ ከዉጭ ጉዞ፣ ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከቡድናዊነት ስሜት ጋር የተያያዙ እንደነበሩም ታውቋል፡፡

ዋና ዋና ጋዜጠኞችን በደቦና በሥራ ክፍላቸው በመሸንሸን ሂስና ግለሂስ እንዲያካሄዱ መደረጉን ዋዜማ ከተሳታፊዎቹ ያገኘቸው መረጃ ያትታል፡፡ ሠራተኞች ወገንተኛና  አዳሪነት ይታይባቸዋል ባሏቸው ጋዜጠኞች ላይ ተቃውሟቸውን በጩኸት ጭምር ይገልጹ ነበር ተብሏል፡፡

መስሪያ ቤቱ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በሁለት ጎራ የቆሙ ሠራተኞች የሚፋተጉበት፣ ከፍተኛ የሥልጣን ሽኩቻ የሚካሄድበት፣ መጠላለፍና የቢሮ ፖለቲካ የነገሰበት ኾኖ እንደቆየ ይነገራል፡፡ ከአማራ መገናኛ ብዙኃን ምክትል ኃላፊነት ተነስተው  በቅርቡ ለኮርፖሬሽኑ የተሾሙት አቶ ስዩም መኮንን  ይህን ቡድናዊነት እዋጋለሁ ሲሉ ለሠራተኞች በተደጋጋሚ ቃል ገብተዋል፡፡

በኢቢሲ ጋዜጠኞች ዘንድ ክፉኛ የሚተቹት የቀድመው ሥራ አስፈጻሚ በዚህ ግምገማ ስማቸው በተደጋጋሚ መነሳቱም ታውቋል፡፡ 52 ዓመታትን ባስቆጠረው ተቋም ዘርን መሠረት ያደረገ ድር እንዲያደራ ምክንያት ኾነዋል፣ ከርሳቸው ብሔር ዉጭ ለኾኑ ሠራተኞች ከፍተኛ ንቀት ያንፀባርቃሉ፣ ጥልቅ ቡድናዊነት በኮርፖሬሽኑ እንዲንሰራፋም ተግተው ሰርተዋል ተብለው በሰፊው ይተቹ የነበሩት እኚህ የሕወሓት ከፍተኛ አመራርና የቀድሞው የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም በቅርቡ በዲፕሎማትነት ወደ አሜሪካ መሸኘታቸውን ተከትሎ ለኮርፖሬሽኑ አዲስ የተሾሙት የብአዴኑ አባል አቶ ስዩም መኮንን ናቸው፡፡

አቶ ስዩም በነዚህ ግምገማዎች ላይ ቀኑን ሙሉ ይታደሙ እንደነበረና በሠራተኞች ይዘንብ የነበረው የብሶት መጠን ከጠበቁት በላይ እንደሆነባቸው መናገራቸውን ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡ አቶ ስዩም ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡

በመገማገሚያ መድረኮቹ አንድ ጋዜጠኛ  የሠራውን ኩነኔ በቅድሚያ እንዲናዘዝ ከተደረገ በኋላ ከባልደረቦቹ ነቀፌታና ሙገሳ እንዲሰነዘርበት ይደረግ እንደነበረ የተብራራ ሲኾን በግምገማው መጨረሻም ዝቅተኛ፣ ከፍተኛ ወይም መካከለኛ ነጥብ እንዲሰጠው ይወሰን የነበረው በድምጽ ብልጫ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ በዚህ ሂደት ከያዙት ሥልጣንና ኃላፊነት እንዲባረሩ የተደረጉ ጋዜጠኞች መኖራቸውም ተዘግቧል፡፡ በደቦ በሚካሄደው ዉሳኔ ደስተኛ ያልኾኑና ጋዜጠኛ በማንነቱ ሳይኾን በሠራው ዘገባ ነው መተቸት ያለበት ሲሉ የነበሩ ሠራተኞች እንደነበሩም ተዘግቧል፡፡

ከፍተኛ ራስ ወዳድነት፣ አድር ባይነትና ግለኝነት ታይቶባቸዋል በሚል ከተገመገሙት ዉስጥ የጥናትና ምርምር ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ ታደሰ ሚዛን ይገኙበታል፡፡ ከርሳቸው በተጨማሪ  የመዝናኛና ወቅታዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ የናትአለም መለሰ፣ የወቅታዊ ጉዳዮች ክፍል ኃላፊ አቶ ሰኢድ ሙሔና ሌሎች የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዳይሬክተሮች ከፍ ያለ ወቀሳ ከሠራተኞች ቀርቦባቸዋል፡፡

አቶ ታደሰ ሚዛን የኮርፖሬሽኑን አዲስ መዋቅር በማዘጋጀት ከተሳተፉ ባለሞያዎች አንዱ እንደነበሩና ለጊዝያዊ ጥቅም ሲል በርካታ ሰዎችን ችግር ዉስጥ መክተቱን አምነው በኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም በአድርባይነት ራሱን ክፉኛ ተችቷል፡፡ ለፈጸመው ይቅር የማይባል ጥፋትም የበደላቸውን ሠራተኞች በሙሉ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ሠራተኞችና የሥራ ባልደረቦቹ በበኩላቸው የርሱን ኃጢያት የሚያበዙ በርካታ መሰሪ ያሏቸውን ተግባራቱን በአደባባይ በመዘክዘክ ግማሽ ቀን ሙሉ እንዳጠፉ ግምገማውን የተሳተፉ ሠራተኞች  ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔ አንተን ብሆን ቆሜ ለመሄድ የምቸገር ይመስለኛል›› የሚል ትችት ከአንድ ባልደረባው ቀርቦበት ነበር ብለዋል ምንጮች፡፡

በተመሳሳይ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዳይሬክተርና የመዝናኛና ወቅታዊ ጉዳዮች ኃላፊ ወይዘሮ የናትዓለም በጥቅም የተሳሰረ ቡድናዊ አሠራር በመዘርጋት፣ የምትቀርባቸውን ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለሥልጣናትን ለመጥቀም ሲባል ፕሮግራሞችን ቆርጦ በመቀጠልና በእያንዳንዱ ዜና ከፍ ያለ ሳንሱር በማድረግ ተገምግማ በሠራተኞች ዝቅተኛ ነጥብ እንዲሰጣት በድምጽ ብልጫ ቢወሰንም የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስዩም መኮንን “እሷ ከአመራሮች ብቸኛዋ ሴት በመኾኗ መካከለኛ ነጥብ እንዲሰጣት እጠይቃለሁ” በማለታቸው የብዙኃኑን ድምጽን በድምጻቸው መሻራቸው ታውቋል፡፡

ለሳምንታት በዘለቀው በዚህ የጋዜጠኞች የግምገማ መድረኮች የዉጭ ጉዞን አነፍንፎ ለግል ጥቅም በማድረግ ረገድ የተተቹት ወይዘሮ የናትዓለም መሰለ የደቡብ ሱዳን ድርድር ጁባ ወይም ናይሮቢ ላይ ሲካሄድ እኔ ካልሄድኩ እንደሚሉና ድርድሩ አዲስ አበባ ሲኾን ግን ተራ ጋዜጠኞችን እንደሚልኩ ተመልክቷል፡፡ የዜና ክፍል ጋዜጠኞች በዉጭ ጉዞ ለማድረግ ከፍተኛ የሞት ሽረት ትንቅንቅ እንደሚያሳዩና ለፖርቲው ይበልጥ ታማኝነቱን የሚያሳዩ ጋዜጠኞች ብቻ ይህን እድል እንደሚያገኙ ይታወቃል፡፡

አቶ ሰኢድ ሙሔ ካሜራን በማፍቀር እንደተገመገመና ራሱም ግለ ሂስ እንዳደረገ ተነግሯል፡፡ አንድ የኢቢሲ ባልደረባ አቶ ሰኢድን “አንተ የኔ ቢጤ ነው የምትመስለው፣ ምናለ ካሜራ ላይ ባትጣድ” የሚል የሰላ ሂስ ከሰነዘሩባቸው በኋላ በከሰዓቱ ክፍለ ጊዜ በግለሰቡ ላይ ለሰነዘሩት ትችት ይቅርታን መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ለስምንት ተከታታይ ዓመታት በሥራ አስፈጻሚነት የመሩት አቶ ዘርዓይ ዓስገዶም ድምጸ ወያነን ዘለግ ላለ ጊዜ ያስተዳደሩ ሰው ሲኾኑ የብሮድካስት ባለሥልጣን ኃላፊ ኾነው ዝውውር ሲያደርጉ እርሳቸውን ተክተው ኮርፖሬሽኑን ለሁለት ዓመታት ያገለገሉት አቶ ብርሃነ ኪዳነ ማርያም ደግሞ በትዕምእት ዉስጥ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ከመሥራታቸውም በላይ የዋልታ ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡ አቶ ብርሃነ ሹመታቸውን ተከትሎ በወቅቱ በዋቢሸበሌ ሆቴል ለሠራተኞች ባደረጉት ንግግር ድርጅቱን ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሻግሩ፣ ሹመት በብቃት ብቻ እንደሚሰጡ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ኾኖም ከተናገሩት በተቃራኒው ለመቆም የወሰደባቸው ጊዜ ረዥም አልነበረም ይላሉ ተቺዎቻቸው፡፡

ዘረኝነትና ጠባብነት የነገሰባቸው፣ ከርሳቸው ሐሳብ ጋር የማይስማማን ሰው ከማጥቃት ወደኋላ የማይሉ፣ የለየላቸው አምባገነን እንደነበሩ በርካታ የድርጅቱ ሠራተኞች ይመሰክራሉ፡፡ በአንጻሩ አቶ ዘርዓይ የራሳቸው ደክመቶች ቢኖሩባቸውም አቅም ያላቸውን ጋዜጠኞችን ኃላፊነት በመስጠት ጥሩ ስም እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ በአቶ ብርሃነ ዘመን ሰባት የሚኾኑ ጋዜጠኞች ከአገር መኮብለላቸውን፣ በአቅም ደረጃ ጥሩ የነበሩ ጋዜጠኞችም መስሪያ ቤቱን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸው ይነገራል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የወቅታዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበረው ጋዜጠኛ አሸብር ጌትነት፣ የትምህርታዊ ፕሮግራሞች ክፍል ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ተመስገን ገ/ህይወት፣ የመዝናኛ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ፍቅር ይልቃል የአቶ ዘርአይ ተወዳጅ ሰራተኞች የነበሩ ሲኾን የአቶ ብርሃነን መምጣት ተከትሎ በወራት ልዩነት ድርጅቱን መልቀቃቸው ይታወሳል። 

በአቶ ብርሃነና በአቶ ዘርአይ መካከል በነበረ የግል ቁርሾ  ምክንያት ዋና ዋና የአቶ ዘርአይ ስብስብ እንደሆኑ የሚታመኑ የኮርፖሬሽኑ ጋዜጠኞች የአቶ ብርሃነን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ከሥራ ተባረዋል፣ ከፊሎቹም በገዛ ፍቃዳቸው ለቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በአዋጅ  ቁጥር 858/2006 የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽኑ በሚል በአዲስ መልክ ከተዋቀረ በኋላ ለሰራተኞቹ እስከ 200 እጅ የደመወዝ ጭማሪ በማድረግ፣ በአራት ክልሎች ስቱዲዮ በመክፈት ሥራውን በአዲስ መልክ ጀምሮ ነበር፡፡ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት መጥቶ የነበረውን የብሔራዊ ሬዲዮ አገልግሎት ወደ ቀድመው ዘነበወርቅ እንዲመለስ የኾነውም በአቶ ብርሃነ የግዛት ዘመን ነው፡፡

በዚህ የግምገማ ሂደት የተገኙት የቀድመው የእርሻ ሚኒስትርና የኢቢሲ የቦርድ አባል አቶ ተፈራ ደርበው የሠራተኞቹን የርስበርስ ሽኩቻ ከተመለከቱ በኋላ “እንዴት ነው በዚህ ዓይነት በዚህ ትልቅ ተቋም ዉስጥ በጋራ የምትሰሩት?” ሲሉ መገረማቸውን በይፋ ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የቴሌቪዥን ግብር የማያይከፍሉ ዜጎችን ወደ ሥርኣቱ ለማስገባት ያለመ የቤት ለቤት ፍተሻ ከትናንት ጀምሮ መጀመሩ ታውቋል፡፡ በዋናነት በከተማዋ በሚገኙ የጋራ መኖርያ ቤቶች አካባቢ ያተኮረው ይህ ፍተሻ የቤት ለቤት ምዝገባ በማካሄድ ላይ የተወሰነ ሲኾን ነዋሪዎች የቴሌቪዥን ቀረጥ የከፈሉበትን ሰነድ እንዲያቀርቡ የሚያስገደድ ሦስት፣ ሦስት ሠራተኞች የተሰማሩበት ነው፡፡ ቴሌቪዥን ኑሯቸው ግብር ሳይከፍሉ በቀሩ ነዋሪዎች ላይ ወደፊት የሚወሰደው እርምጃ ምን እንደሆነ ባይታወቅም የከፈሉበትን ደረሰኝ ያላሳዩ ነዋሪዎች ሙሉ ስማቸውና ስልካቸውን በመመዝገብ በየአካባቢው ለተቋቋሙ የክፍያ ጣቢያ ይተላለፋል ተብሏል፡፡

በዚህ የምዝገባ ሥራ ላይ የተሰማሩና በመገናኛ የጋራ መኖርያ ቤት ምዝገባ በማካሄድ ላይ ሳሉ የዋዜማ ዘጋቢ አግኝቶ  ያናገራቸው አንዲት የወረዳ ሠራተኛ በርካታ ነዋሪዎች ለመመዝገብ ፍቃደኛነታቸውን እንደማያሳዩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ኢቢሲን ማየት አቁመናል››፣ ‹‹የናንተን ጣቢያ ከከፈትን ለልጆቻችን ዉሸትን ማስተማር ነው የሚኾንብን››፣ ‹‹ለቃና ቲቪ ብንከፍል አይቆጨንም›› የሚሉ ንግግሮች ከነዋሪዎች ይነሱ እንደነበር አልሸሸጉም፡፡

በዚያው መጠን ግብር የከፈሉበትን ደረሰኝ ያሳዩ ዜጎችም ቁጥራቸው ጥቂት አልነበረም ብለዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት የኮሚኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ክፍያ ለሁሉ ከተባለ የግል ተቋም ጋር በመሆን በፈጸመው ዉል ዜጎች የቴሌቪዥን ግብር ከዉሀና መብራት ክፍያ ጋር ደርበው እንዲክፍሉ የሚያስገድድ አሰራር ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህም በዓመት 60 ብር ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ቴሌቪዥን ኖሯቸው ግብር እንደማይከፍሉ በተቋሙ በተሰራው የዳሰሳ ጥናት ተመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ ጣቢያው በየዓመቱ በምዝገባና በዓመታዊ የቲቪ ግብር አማካኝነት  ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያደርጋል፡፡

የሕዝብ ተብለው የሚፈረጁ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ከሕዝብ ከሚሰበሰብ የምዝገባ ግብር ማስተዳደር በብዙ አገራት የተለመደ አሰራር እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህም ጣቢያዎች በግዙፍ የማስታወቂያ ድርጅቶችና የንግድ ኮርፖሬሽኖች አማካኝነት ተጽእኖ እንዳይደርስባቸውና ያልተዘቡ መረጃዎችን ለሕዝብ እንዲያቀርቡ በሚል ነው፡፡

ለሕዝብ የተዛባ መረጃ በማሰራጨት የሚታወቀውና በዜጎች ዘንድ መልካም ስም ያሌለውን ጣቢያ ከሕዝብ በሚሰበሰብ ቀጥተኛ ግብር ለማስተዳደር መሞከር ትክክለኛነቱን የሚጠራጠሩ ብዙዎች ናቸው፡፡