book vendor

እንዴት ሰነበታችሁ! እኔ ደህና ነኝ፡፡ የመሐል አገር ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ?! ምን ቢከፋ ጦሙን አያድር! ለነገሩ በዚህ ክረምት የሸገር ሕዝብ ከሆዱ ይልቅ አእምሮዉን ለመመገብ መጨነቅ ይዟል፡፡ እሸት ትቶ መጻሕፍት ጠብሶ እየበላ ነው፡፡ ይህኔ አጋነንክ ትሉኝ ይሆናል፡፡ አላጋነንኩም፡፡ ከሰላምታዬ ቀጥዬ የማሳስባችሁ ነገር ቢኖርም ይኸው ጉዳይ ነው፡፡ አገር ቤት የዶላር እጥረት፣ የአንባቢ ንዝረትና የደራሲ ግሽበት ተከስቷል፡፡

ማስቲካ አዝዋሪዎች ባናና ማስቲካ መሸጥ ትተው ‹‹ቄንጠኛ የማስቲካ አስተኛኘክ ጥበብ በኢትዮጵያ›› የሚል መጽሐፍ ማዞር ጀምረዋል ብላችሁስ፡፡ አታምኑኝም፡፡ የታክሲ ወያሎች በቀኝ እጃቸው ከተሳፋሪ ሳንቲም እየለቀሙ በግራ እጃቸው ‹‹የሎስ›› የሚል ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ እንደያዙ ብነግራችሁስ፡፡ አታምኑኝም፡፡ የአንበሳ አውቶቡስ ትኬት ሻጮች ‹‹ባቡሩ ሲመጣ›› የሚል ልቦለድ ላይ አቀርቅረው ብዙ ተሳፋሪ ያለ ትኬት እንደሚጓዝ ባረዳችሁስ! አታምኑኝም፡፡

ሊስትሮዎች ጫማ ለማስዋብ ብሩሽ ከሳጥናቸው ሲመዙ አብሮ አንድ መጽሐፍ ዱብ ይላል፤ ‹‹በ30 ቀናት ሚሊየነር የመሆን ታላቅ ምስጢር›› የሚል፡፡ እንዲያውም ከአራት ኪሎ በላይ ባለው ሰፈር አንድ ጩሉሌን ‹‹ማነህ ሊስትሮ!›› ብላችሁ ስትጠሩት፣ ‹‹ይቅርታ ጋሼ! እያነበብኩ ነው! አያናጥቡኝ!›› ብሎ ኩም፡፡ 6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ የዋናው ግቢ በር ፊት ለፊት ድባብ መናፈሻ መግቢያ ላይ የሚገኝ ጢሙን ያንዠረገገ አንድ ሊስትሮ ሳጥኑ ጎን ላይ እንዲህ የሚል ጥቅስ ለጥፏል- “ከጫማችን በፊት አእምሯችንን በመጻሕፍት እናስቦርሽ” ቶልስቶይ፡፡ ይህን ይህን ሳይ…”የመጨረሻው ዘመን እየቀረበ ይሆን?” እላለሁ፡፡

ከመጻሕፍት ንጣፍ በተረፉ የሸገር ጎዳናዎች ላይ ጎዳና ተዳዳሪዎች ይተኙባቸዋል፡፡ የጎዳና ልጆች እንደ ትራስ ከሚጠቀሙበት ጠፍጣፋ ድንጋይ ሥር ታዲያ አንድ አሮጌ መጽሐፍ ሸጎጥ መደረጉ አይቀርም፡፡ እንቅልፍ እስኪወስዳቸው የሚያነቡት መሆኑ ነው፡፡ብሔራዊ ትአትር አካባቢ በወጨፎ የራሱ የእግረኛ መንገዶች ሳይቀር የላስቲክ ንጣፍ ተጎዝጎዞላቸዋል የመጻሕፍት ጉልቶች ሆነዋል፡፡ ሸገራዊያን ዘንድሮ ምን እንደነካቸው እንጃ ክፉ አንባቢ ሆነዋል፡፡ ይህን ይህን ሳይ…”ይመጣል የተባለው ዘመን እየቀረበ ይሆን?” እላለሁ፡፡

ስማቸውን ከዳርሰማ ተሻገር ወደ አርሴን ቬንገር ሊቀይሩ ይዳዳቸው የነበሩ የኤፍ.ኤም ጋዜጠኞች ሳይቀር ዘንድሮ አፋቸውን የሚያሟሹት ስለ መጻሕፍት በማውራት ሆኗል፡፡ ስለ ሊጉ ሰንጠረዥ ከማውራታቸው በፊት በዚህ ሳምንት ገበያውን እየመሩ ስለሚገኙ መጻሕፍት መረጃ ያቀብላሉ፡፡ ስለ ዝውውር መስኮት ለመናገር የመጻሕፍትን ታላቅነትን በሚያወሳ አባባል ይጀምራሉ- “መጻሕፍት የሕይወትን ገጽታ የሚያስቃኙ መስኮቶች ናቸው፣ አድማጮቻችን ስለመስኮት ካነሳን ዘንዳ የአውሮፓ ክለቦች የዝውውር መስኮት መከፈት ጋር ተያይዞ የተጫወቾችን የዝውውር ዜና ከዚህ እንደሚከተው እናቀርባለን…”

ካምቦሎጆ ጋዜጣ ይዞ መግባት ከመከልከሉ ጋር ተዳምሮ ይሁን አይሁን ባለውቅም አሁን አሁን መጽሐፍ በብብታቸው ሸጎጥ አድርገው ሚስማር ተራ የሚታደሙ የኳስ አፍቃሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ አዲሳባ ስታዲየም ዙርያ ከድራፍትና ከጆተኒ ቀጥሎ በብዛት የሚታዩት መጽሐፍ አዝዋሪዎች ናቸው፡፡ አሸናፊ የመሰሉ ድንቅ የመሐል ሜዳ ኢንጂነሮች የእግር ኳስ ሕይወታቸውን በመጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ በእግር ኳስ ዙርያ የኢንሳክሎፒዲያ እውቀት አለው የሚባለው ሊብሮም በሚያስገርም ሁኔታ ሦስት ተከታታይ መጻሕፍትን ለሕትመት ብርሃን አብቅቷል፡፡ ‹‹የእግር ኳስ ወጎች›› ብሎ የጀመረው ሊብሮ “ኢህአፓና ስፖርት” በሚል ጉዳይ ብቻ ተከታታይ ባለ ሁለት ቅጽ መጽሐፍትን አሰራጭቷል፡፡ እግር ኳስና ስፖርትን አጋብቷል፡፡ አንባቢው በወረፋ ገዝቶ አንብቦታል፡፡ በአንደኛው መጽሐፉ ላይ ስማቸው የተጠቀሰ አንድ የደርግ አባልም በስም ማጥፋት ከሰውታል፡፡ እግር ኳስና ፖለቲካው ይህን ያህል ተቀራርበዋል፡፡ የእግር ኳስ አራጋቢዎችም መጽሐፍ ያሳትማሉ ብዬ እንድጠብቅ ተገድጃለሁ፡፡ አእምሮዬ ርዕስ አዘጋጅቶ እየጠበቃቸው ነው፡፡ ‹‹ለእግር ኳስና ለገዢው መንግሥት የማራገብ ልዩነቶችና አንድነቶች›› የሚል ርዕስ በህሊናዬ ይመላለሳል፡፡ ታዲያ ይሄ ሁሉ የጤና ነው? ለነገሩ ‹‹አርሴናል ከየት ወዴት›› የሚል መጽሐፍ ገበያ ላይ ከዋለ ገና መንፈቅ ተኩል አላለፈውም፡፡ የኔ ፍርሃት ሌላ ነው፡፡ እግር ኳስ ሁሉ መጽሐፍ እየሆነ የኢህአፓ ዉልድ ወጣት እንዳይፈጠር፡፡

ነገሩ በዚሁ ከቀጠለ ‹‹ጨጓራዎን ሳይልጡ አርሴናልን የመደገፍያ 10 ብልሀቶች›› የሚል በዓይነቱም በይዘቱም ልዩ የሆነ መጽሐፍ እንዳይታተም ነው ስጋቴ፡፡በዘንድሮ የክረምት አያያዝ ይህ አይሆንም ለማለት ይቸግረኛል፡፡ ሸገራዊያን ዘንድሮ ምን እንደነካቸው እንጃ፣ ብቻ ደፋር ፀሐፊና ክፉ አንባቢ ወጥቷቸዋል፡፡

ለምሳሌ ኪሎ ምስር 60 ብር ለመግዛት የተወደደበት ወንደላጤ ‹‹የእናት ጓዳ›› የሚል መጽሐፍ በ49 ብር ገዝቶ ወደ ኮንዶሚንየሙ ያዘግማል፡፡ በር ላይ ቆሞ ኪሶቹን ይዳብሳል፡፡ የቤት ቁልፉን የሆነ ቦታ እንደዘነጋው ይረዳል፡፡ መሥሪያ ቤት ረስቶት እንደሆነ በመጠርጠር ተመልሶ ይሄዳል፡፡ በአጋጣሚ መንገድ ላይ መጽሐፍ አዙዋሪ ያገኛል፡፡ የሕይወት ቁልፍ መጽሐፍ ዉስጥ እንደሚገኝ ጥቅስ ላይ ማንበቡ ትዝ ይለዋል፡፡ ‹‹የተቆለፈበት ቁልፍ››ን ገዝቶ ይመለሳል፡፡ ፡፡ የኮንዶሚንየም በሩን በመጽሐፍ ሊከፍት፡፡ ታዲያ ይሄ የጤና ነው ጎበዝ?

ክፍት የሥራ ቦታ የሚፈልጉ ትኩስ ተመራቂዎች ‹‹Hunting a white-collar job›› የሚል ቀትረ ቀላል መጽሐፍ በብብታቸው ሸጉጠው ያን አንጀት የሆነ ጋዜጣን ሲያገላብጡ አያለሁ፡፡ አዝናለሁም፡፡ ደግሞ ብዛታቸው፡፡ መቶ ሺ! ኸረ ከዚያም በላይ ይሆናሉ፡፡ ደግሞ ይሄ ሥራ የሚፈልጉበት ድልብ ጋዜጣ ጦሰኛ ነው፡፡ ማቃጠር እንጂ ማስቀጠር አያውቅበትም፡፡ ምላሱ ጥቁር ነው፡፡ ማሳሰርና ማሰደድ ያውቅበታል፡፡ ጠንቋይ ነው፤ ከተነበየ ይሆንለታል፡፡

አገሪቱ ዉስጥ ፀሐፊዎች ይታሰራሉ፡፡ ጋዜጦች ይዘጋሉ፡፡ ጋዜጠኞች ይሰደዳሉ፡፡ ከዚህ ከትልቁ ጋዜጣ በስተቀር፡፡ ትልቁን ጋዜጣ አተኩሬ ስመለከተው ትንንሾቹን ጋዜጦች ስልቅጥ አድርጎ የበላቸው ይመስለኛል፡፡ ለዚያ ነው መሰለኝ ወፍሯል፡፡ አለቅጥ ሰፍቷል፡፡ በየዘመኑ በአድርባይነት ይኖራል፡፡ አጎንብሶ ጥይት ማሳለፍ የሚያውቅ ጋዜጣ ነው፡፡ አራት ኪሎ በክረምት እሱን የማያነብ ወጣት የለም፡፡ እንደ ብርድልብስም ያገለግላል መሰለኝ አንባቢዎቹ ዶፍ ዝናብ እየዘነበም በዉስጡ ተከልለው ያነቡታል፡፡ ደግሞ የአንባቢው ብዛት፡፡ ጆሊ ባር አካባቢ ድንገት በሆነ ተገጣጣሚ ብሎኬት ቢታጠር ከምስራቅ አፍሪካ ትልቅ አስደናቂ ቤተ መጻሕፍት የሚፈጠር ይመስለኛል፡፡

ዘንድሮ ክረምቱ የበቆሎ ሳይሆን የመጽሐፍ ነው ብያችኋለሁ፡፡ የሸገር ሕዝብ በክረምት መጽሐፍ ካላነበበ እንቅልፍ አይወስደውም፡፡ ጃኬትና መጽሐፍ ካልገዛ ይበርደዋል፡፡ በመላው ሸገር አምስት መቶ አዝዋሪዎች በየዕለቱ ክንዳቸው ይዝላል፡፡ ደግነቱ የዛለ ክንዳቸው ምሽት ላይ በጥሩ ገቢ ይታሻል፡፡ ሁሉም ፀሀፍት የገቢያቸውን 10 እጅ ለአዝዋሪ በአስራት መልክ ያስገባሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ወደውና ፈቅደው አይደለም፡፡ ታዘው ነው፡፡ ደራሲዎች የአዝዋሪዎች ተዘዋዋሪ ቅጥረኛ ሆነዋል፡፡ አዝዋሪ ያደመበት ደራሲ ስሙኒ ኪሱ አይገባም፡፡ በቅርቡ አንድ ዶክተር ደራሲ ሲያዝበት በሬዲዮ ቀርቦ አዝዋሪዎችን ከፍ ዝቅ አድርጎ ተናግሮ ጉድ አልሆነ መሰላችሁ፡፡ አመጹበት፡፡ አማራጭ አልነበረውም፡፡ የቀሩትን ኮፒዎች በአምስት አምስት ብር ሽጦ ወደ ሕክምና ሙያው ተመለሰ፡፡ የሸገር አዝዋሪዎች አንድ ደራሲ ላይ አመጹ ማለት ጋንዲና ተከታዮቹ የእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ላይ ለገሙ እንደማለት ነው፡፡ ይህን ይህን ሳይ እሰጋለሁ፡፡ “የመጨረሻው ዘመን እየቀረበ ይሆን?” አላለሁ፡፡

ለማንኛውም በዚህ ክረምት የአዲሳባ ሕዝብ በሦስት ተከፍሏል፡፡ ደራሲ፣ አሳታሚና አንባቢ በሚል፡፡ የዘንድሮን ልዩ የሚያደርገው ግን የደራሲው ቁጥር ከአንባቢው የሚስተካከል መሆኑ ነው፡፡ አጋንኜ ይሆናል፡፡ ብዙ አይደለም ግን፡፡

ፖለቲከኞች ትግላቸውን እየከሰመ ከመሰላቸው መጻሕፍ ይጽፋሉ፡፡ ደርጎች አንድ ሐሙስ የቀራቸው ሲመስላቸው መጽሐፍ ይጽፋሉ፡፡ ጋዜጠኞች ልሳናቸው ሲዘጋ መጽሐፍ ይጽፋሉ፡፡ የፌስቡክ ልሂቃን ግድግዳቸው ላይ በጻፉት አንቀጽ 500 እና ከዚያ በላይ ‹‹መውደድ›› ሲያገኙ መጽሐፍ ይጽፋሉ፡፡ አምደኞች ግማሽ ደርዘን አጭር ልቦለድ ከጻፉ ጥሩ ሽፋን አስደዝነው ሲያበቁ ‹‹…እና ሌሎችም›› ብለው ያሳትሙታል፡፡ ሰሞኑን አንድ ‹‹የጉራጌ ልማት›› በሚል ዓመታዊ መጽሔት ላይ በተባራሪነት የሚጽፍን ወጣት አውቶቡስ ተራ አግኝቼው ‹‹ሕልምህ ምንድነው?›› ስለው ‹‹…እና ሌሎችም›› የሚል መጽሐፍ አሳትሜ ለመስቀል አገሬ መግባት ነው ብሎኛል፡፡

ቂሊንጦ በቦታ ጥበት የተነሳ የማስፋፊያ ፕሮጀክት እያካሄደ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ደስም ብሎኛል፡፡ ብዙዎች ቂሊንጦን እንደ ማጎርያ ያዩታል፡፡ እኔ እንደ “ወመዘክር” አየዋለሁ፡፡ የብዙ ደራሲዎቻችን ምንጭ ማን ሆነና፡፡ ዛሬም እንደ ወትሮው ታሳሪዎች መጽሐፍ በማሳተም የሚስተካከላቸው አልተገኘም፡፡ በዘንድሮ ክረምት የታሳሪው ቁጥር ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ከቂሊንጦ የሚመጡ ደራሲዎች ቁጥር ከፍ እንደሚል ይጠበቃል፡፡

አንዷለም አራጌ 2ኛ መጽሐፉን በቅርቡ አድርሶናል፡፡ ርዕዮት ‹‹የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ›› ክፍል ሁለት ይዛ እንደምትወጣ ተገምቷል፡፡ አሕመዲን ጀበል የ “Writing Fellowship” ያሸነፈ ይመስል መጽሐፍ ለአንባቢ በማድረስ የሚስተካከለው አልተገኘም፡፡ ‹‹ፍርኦኖቹ››ን በቅርቡ አድርሶናል፡፡ ከዚህ በመነሳት የኔ የረዥም ጊዜ ሕልም ‹‹አቃቂና ቂሊንጦ የቀድሞ ታሳሪዎች ደራሲያን ማኅበር›› የሚል መያድ መክፈት ነው፡፡ ምናልባት በዚህ ምክንያት ከታሰርኩም ‹‹በአጭር የተቀጨው ማኅበር የመመስረት ሕልሜ›› የሚል መጽሐፍ ከዚያው ሆኜ እጽፋለሁ፡፡ ‹‹የሰይጣን አምላኪዎች ማኅበር›› ተብሎ ስንት ሺ መጽሐፍ በሚታተምበት አገር የኔ ምኑ ይገርማል?

በክረምት የመጻሕፍት ከተፋም ተስተውሏል፡፡ የጋዜጣ ጽሑፍን ጠርዞ ማሳተም፡፡ ቃለ መጠይቆችን ጠርዞ ማሳተም፡፡ የሰዎችን ሐሳብ ጠርዞ ማሳተም፡፡ የዶክተር ዳኛቸው ሐሳቦችን ዳኝቶ ማሳተም… ጥራዝ ነጠቅነት ጠርዞ ማሳተም ወዘተ፡፡ ይዘት እምብዛምም የማያስጨንቃቸው የመጻሕፍት ሰልባጅ አዝዋሪዎች ከፕሮፌሰሩ ጀምሮ እስከ አማተሩ ድረስ የተጠረዘን ነገር ሁሉ የትም ይዘው ይዞራሉ፡፡ አይደለም ዶፍ ዝናብ “አዳፍኔ” ቢተኮስባቸው እንኳ ገለል በማይሉት በእነዚህ መጽሐፍ አዙዋሪዎች አሳላፊነት የአዲሳባ ሕዝብ በክረምቱ የመጽሐፍ ጮማ እየቆረጠ ይገኛል፡፡ ‹‹አዳፍኔ›› ከጮማዎቹ ዉስጥ ነጪ ሥጋ ነው ይላሉ ተንታኞች፡፡ ጥቂት የስድብ ገጾች ታከሉበት እንጂ አዲስ ነገር የለዉም ባይ ናቸው፡፡ “መክሸፍ በተግባር ሲገለጥ” ብለው ያላገጡም አሉ፡፡

መጽሐፍ ዶፍ ሆኖ በዘነበበት በዚህ ክረምት የድሮ ሙዚቃ እንደሚከለሰው ሁሉ መጻሕፍትም ዘመነኛ ልባድ ተሰፍቶላቸው መከለስ ጀምረዋል፡፡ በዓሉ ግርማ ሐዲስ ነሽ፣ ደራሲው ነሽ፣ ኦሮማይ ነሽ ሁሉም ተደግመዉ ታትመውለታል፡፡ የሰመመኑ ደራሲ ‹‹የቅናት ዛር›› ሳይቀር ተደግሞለታል፡፡ ሰርቅ ዳ. ቆንጆዎቹ ታትመውለታል፡፡ የክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” ለዚህ ዘመን ስስ አንባቢ ሲባል በአጠሬራ መልክ በሦሰት በአራት ቅጽ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ የዳኛቸው ወርቁ ብሉይ ሥራ በእንግሊዝ አፍ ማስነጠስ ለሚቀናው ለዚህ ዘመን ሰው በድጋሚ ቀርቦ የወጣቱን የቋንቋ ክህሎት አደፍርሶታል፡፡ የዳኛቸው ሥራ ‹‹አልገባንም›› የሚሉ የአዲሱ ትውልድ አንባቢዎች ደራሲው ያካብዳል፣ ቀለል አድርጎ እንዲጽፍልን ንገሩልን የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ደራሲው በሕይወት እንደሌለ አያውቁም፡፡ ጥያቄያቸው በአሳታሚዎች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት በቀጣዩ ክረምት ‹‹አደፍርስን›› እንደመጽሐፍ ቅዱስ ከቃላት መፍቻ ጋር ለማቅረብ እንደሚሞከር ይጠረጠራል፡፡

ክረምቱ ፀሐፍት እንደ አሸን የፈሉበት ነው፡፡ የድረገጽ ዉልድ የሆኑት የ‹‹መካነ ገጽ›› ፀሐፊያን ብዙዎቹ ማተሚያ ቤት ደጅ ተኮልኩለዋል፡፡ አውራዎቹ ግን ቀደም ብለው የህትመት ገበያውን እፍታ ወስደው ተሰውረዋል፡፡ ዙበይዳ በ25ሺ ኮፒ ሊጉን በከፍተኛ ነጥብ ይመራል፡፡ ባርቾ በ7ሺ ኮፒ በሊጉ ሰንጠረዥ 2ኛ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በታችኛው ዲቪዚዮን የሚጫወቱት ግን ለቁጥር ያታክታሉ፡፡ ለምሳሌ ገጣሚያን፡፡ በክረምቱ ገጣሚያን ከመብዛታቸው የተነሳ ሳድስ ፊደል መስለዋል፡፡ ለነዚህ ወጣቶች ግጥም ማሳተም የትምህርት ማስረጃን ፎቶ ኮፒ እንደማድረግ እንኳን አይከብዳቸውም፡፡ ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ የገዛ ምስላቸውን በሽፋኑ ጀርባ በጉልህ ማኖራቸው ነው፡፡ መቶ ኮፒ እንኳን አይሸጡም፡፡ አለመሸጡ እምብዛምም አያስከፋቸውም፡፡ አጥብቀው የሚሹት መነበብን ሳይሆን ማዕረግን ይመስለኛል፡፡ ሲተዋወቋችሁ “ጤና ይስጥልኝ! ገጣሚ እንቶኔ እባላለሁ…” ብለው ነው፡፡ ታዲያ ይሄ የጤና ነው? ያ የሚባለው ዘመን እየቀረበ ይሆን?

መጸሐፍ ማሳተም የጭቁኑ ማኅበረሰብ ተግባር ብቻ ሳይሆን የባለሥልጣናትም ጭምር መሆኑን ያስመሰከረ ሐምሌ ነው ዘንድሮ፡፡ ከአንድ ወር በፊት የአገር ዉስጥ በረራ ለማድረግ ቦንባርዴ ዉስጥ ተሳፍሬ ከፊት ለፊቴ የተሸጎጠውን የበረራ መጽሔት መገላለጥ ጀመርኩ፡፡ BOOK REVIEW ይላል፡፡ እስከዛሬ መጽሐፍ በዚህ መጽሔት ሲገመገም ገጥሞኝ ስለማያውቅ ተስገብግቤ አነበብኩት፡፡ የአቶ አርከበ መጽሐፍ አንድ ሙሉ የሰላምታ መጽሔት ሽፋን አግኝቷል፡፡ ብዙ ቦታ ይህ ነገር አጋጥሞኛል፡፡ የነገሩ መደጋገም ገረመኝ፡፡ በአገሪቱ ዉስጥ ሌላ የፒኤችዲ መመረቂያ የሰራ ሰው ያለ አይመስልም፡፡ የመጀመርያው አፍሪካዊ ዶክተር እንኳን ይህን ያህል ሽፋን ያገኙ አይመስለኝም፡፡ የተከበሩ አቶ አርከበ (ከፍተኛ ይቅርታ በመጠየቅ በድጋሚ ይህን አረፍተ ነገር እጽፋለሁ) የተከበሩ ዶክተር አርከበ መመረቂያ ጽሑፋቸውን መጽሐፍ አድርገው አሳትመዋል፤ ወይም ታትሞላቸዋል፡፡ ደስ ይላል፡፡ ኾኖም የአንዱ መጽሐፍ ዋጋ አንድ አርከበ ሱቅ ከነ መጽሐፍ መደርደሪያው ይገዛል፡፡ አንዳንድ በአንድ ጀንበር የበለጸጉ ነጋዴዎች እንደሆኑ የሚጠረጠሩ ግለሰቦች ‹‹ቡክ ወርልድ›› እየገቡ ‹‹እስቲ ማነህ…ከዚህ መጽሐፍ አንድ ደርዘን አድርግልኝ! ፍጠን ፍጠን” ብለው ያዛሉ አሉ፡፡ አንድ ደርዘን መጽሐፍ ገዝተው የ23 ሺ ብር ቼክ ይቆርጣሉ፡፡ አዲስ በገነቡት ቪላቸው ሼልፍ ዉስጥ ሊያኖሩት እኮ ነው፡፡ በጭራሽ አያነቡትም፡፡ ታዲያ ይሄ የጤና ነው ጎበዝ? የመጨረሻው ዘመን አልቀረበምን?

ለማጠቃለል ያህል….የአዲስ አበባ እርጥብ መንገዶች በበቆሎ መድመቅ ሲገባቸው ስለምን በመጻሕፍት አበቡ? ለሚለው አንኳር ጥያቄ መላምት እንጂ ምላሽ የለም፡፡ ከመቶ ሺ የሚልቁ ማንበብ የሚችሉ ምሩቃን ከየዩኒቨርስቲው መመረቃቸው እንደ አንድ መላምት የሚጠቀስ ነው፡፡ ተመርቆ ሥራ የማያገኝ ዜጋ እንደ መቆያ አንድ ነገር ማድረግ አለበት፡፡ ከነዚህ ድርጊቶች አንዱ አንዳንድ መጻሕፍትን ማንበብ ነው ይላሉ ተንታኞች፡፡ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ከመጻሕፍት ይገኝ ይመስል፡፡

የአነስተኛና ጥቃቅን ደራሲዎች ክፉኛ በፍዝ ኢኮኖሚው መደቆስ ሌላው መላምት ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ ፀሐፍት በቁጥር ገንፍለዋል፡፡ መጻፍ እችላለሁ የሚል ዜጋ የገቢ ምንጩ ሲደርቅ ማድረግ የሚችለው የዶሎዶመ ብዕሩንም ቢሆን እስኪገነፍል ድረስ ማሾል ነው፡፡ ብዙ ብዕሮች ሲሾሉ ከተደራሲ የማይተናነሱ ደራሲዎች ይፈጠራሉ፡፡ አሁን እየሆነ ያለውም ይህ ነው ይላሉ በጉዳዩ ላይ ትዝብት ያደረጉ ተንታኞች፡፡ ያም ሆነ ይህ አንባቢም ተነባቢም መብዛቱ ብስራት እንጂ መርገምት ሊሆን አይችልም፡፡

በዚህ ጦማሬ ፀሐፍትና መጽሐፍትን አብዝቼ ካነሳሁ ዘንዳ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ነጥቦችን በመጥቀስ ጦማሬን ልደምድም፤

1. የገዛ ታሪኮችን ከሚጽፉልን መካከል አንዱ የነበረው ሕንዳዊው ጆሴፍ ፍራንሲስ ኦሎምፒያ አካባቢ በሚገኘው ቤቱ በረንዳ ላይ መነጽሩን በእጁ እንደያዘ፣ ላፕቶፑን እንዳነገተ ሞቶ ተገኘ፡፡ ከመሞቱ ከሁለት ቀናት በፊት ‹‹ባቡሩ ሲመጣ›› በሚል ልቦለድ መጽሐፍ ምረቃ ላይ ተገኝቶ ነበር፡፡ የሟች ወዳጆች እንዳወጉኝ ከሆነ የራሱን መጽሐፍት ለመሸጥ በኤግዚብሽን ማዕከል 7 ሺ ብር ቦታ ኪራይ ከፍሎ ነበር፡፡ ሞተ! ነፍስ ይማር!

2. ዓመታዊው ‹‹ንባብ ለሕይወት›› የመጻሕፍት አውድ ርዕይ በድምቀት ተከፍቶ፣ በብዙ ሺ ሸገራዊያን ተጎብኝቶ፣ ብዙ ሺ መጻሕፍት ተሸጠው፣ ብዙ የንባብ አምባሳደሮች ተሹመው፣ አንድ የወርቅ ብዕር ለአምባሳደር ዘውዴ ረታ ተበርክቶ ተጠናቋል፡፡ ይህን የመጽሐፍት አውደ ርዕይ ግማሽ ሚሊዮን ሰው ጎብኝቶታል ተብሎ ይገመታል፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ለማካሄድ ሐሳብ እንዳለ ወጣኞቹ ነግረውኛል፡፡

3. ለሞት ፍርደኛው አንዳርጋቸው ጽጌ መተየቢያ ላፕቶፕ የሚለግሰው መንግሥታችን ለተራ እስረኞች ብዕር አያቀብልም ተብሎ አይታመንም፡፡ ኾኖም ከሰሞኑ የደረሰኝ ዜና የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ ኮስተር ያለ መጽሐፍ እየጻፈ ነበር፡፡ 80 ገጽ ደርሶለትም ነበር፡፡ እነዚህኑ 80 ገጽ ረቂቅ ገጾችን አሾልኮ ሲያሳልፍለት የነበረ የፖሊስ ባልደረባ በድንገተኛ ክትትል ተደረሰበት፡፡ ፖሊሱ ወዲያውኑ በልዩ ኃይል ወደ ማዕከላዊ ታፍኖ ተወስዷል፡፡ ይህንን ተከትሎ የቂሊንጦና የቃሊቲ ፖሊሶች ለከፍተኛ ግምገማ ተሰብስበዋል፡፡ የግምገማው ዋና ዓላማም ለፀረ-ሰላም ታሳሪዎች ልዩ ፍቅር ያላቸው አሳሪዎችን ነቅሶ ማውጣት ነው፡፡ 80 ገጽ ረቂቆቹ ምን ተጽፎባቸው ይሆን?

ደህና ሰንብቱልኝ!