Zemedieneh Nigatu
Zemedieneh Nigatu

(በሙሔ ሐዘን ጨርቆስ-በተለይ ለዋዜማ ራዲዮ )
እንዴት ናችሁልኝ? እኔ ደህና ነኝ፡፡ የመሐል አገር ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ ነው? ምን ቢከፋ ጦሙን አያድር፡፡

ሙሉ ጦማሩን በድምፅ እንዲህ ተሰናድቷል፡አድምጡት

መቼ ለታ መታወቂያ ላሳድስ ቀበሌ ሄድኩኝ፡፡ እርግጥ ነው መታወቂያዬ ጊዜው አላለፈበትም፡፡ ቢሆንም መጪውን ጊዜ ላምነውአልቻልኩም፡፡

አትፍረዱብኝ ወገኖች! የኢህአዴግ ሥልጣን፣ የአዲሳባ ዜግነትና የዛፍ ላይ እንቅልፍ አንድም ሦስትም ናቸው፡፡ አዲሳበባዊና ፍልስጤማዊ መሆን መሳ ሆነዋል፡፡ መሬቱ የማን እንደሆነ አለየለትም፡፡ መታወቂያ የሚያድሰው የቀበሌያችን ኃላፊ ራሱ በቀደም ነው ከሰሜኑ የአገራችን ክፍል የመጣው፡፡ ብቻህን ካዛንቺስ ደርሰህ ና ቢባል በእርግጠኝነት ተክለኃይማኖት ጋ ይጠፋል፡፡

ጊዜው ክፉ ነው፡፡ ማንነቴን የምነጠቅ እየመሰለኝ የማብቂያ ጊዜው ያላበቃ መታወቂያዬን አድሱልኝ እያልኩ ቀበሌ አስቸግራለሁ፡፡ ሰለቸኋቸው መሰለኝ ወረዳ ሂድ አሉኝ፡፡ ወረዳችን ባለ አራት ፎቅ ማስጠሎ የሆነ ሕንጻ ነው፡፡ እንዲህ አይነት መልከ ጥፉ ሕንጻ መሥራት መቻል በራሱ አስደናቂ ነው፡፡ አስደናቂ ብቻም ሳይሆን ስለ አናጺው የሚናገረው ብዙ አለ፡፡ ለጊዜው በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ቀያሹ የሸገርን ዉሀ አልጠጣም፡፡ ደዛኙ ቀበና አልዋኘም፡፡
=============

በወረዳችን ሕንጻ 4ኛ ፎቅ ላይ ሆኜ ወረፋ እየጠበቅኩ ነዋሪውን ቁልቁል ተመለከትኩት፡፡ ግማሹ ይጥራል፣ ግማሹ ያጣጥራል፣ ብዙዎች ይጥራሉ፣ ጥቂቶች ይስቃሉ፡፡ ለሰማይ ስለቀረብኩ ነው መሰለኝ ድንገት ዕውቀት ተገለጠልኝ፡፡ የአዲሳባ ነዋሪን በጥቅሉ በሁለት ከፍሎ ደረጃ በደረጃ ማየት እንደሚቻል ተረዳሁ፡፡

የቀበሌ መታወቂያ ያወጣና የቀበሌ መታወቂያ ያስወጣ፣
እትብቱ ከፎቅ በታች የተቀበረና እትብቱ ከፎቅ በላይ የተሰቀለ፣
መሬት አንጥፎ የሚለምንና መሬት ከሊዝ ነጻ እንዲሰጠው የሚለምን፤
የጀመረው ግንባታ በቅርቡ የሚፈፀምለትና፣ ግብአተ መሬቱ በቅርቡ የሚፈፀም
ለልማት አፈር የሚያስምስና ለመኖር አፈር የሚልስ….፡፡

ሌላም ተያያዥ ዕውቀት ተገለጠልኝ፤ የሸገር የሀብት ሚስጢር መሬት መሆኑ፡፡

የዋዜማ አድማጮች!
ለመሆኑ አዲሳባ ዉስጥ እራፊ መሬት አላችሁ? ሸገር ላይ በስማችሁ መሬት ከሌላችሁማ ምን ንብረት አለን ትላላችሁ? እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በሸገር ምድር መኖርያ ይቅርና መቀበርያ ማግኘት ብርቅ የሚሆንበት ዘመን ተቃርቧልና የነፍስ ወዳጃችሁን እየፈለጋችሁ የቤት ማኅበር ግቡ፡፡ እየተደራጃችሁ ቤት ገንቡ፡፡ ያ ቢያቅታችሁ እንኳ ኮንዶሚንየም ተመዝገቡ፡፡

ዉድ በመላው ዓለም እንደ አሸዋ የተዘራችሁ…
እንዲሁም ‹‹ዳያስፖራ›› የሚል ተቀጽላ የተበጀላችሁ…
ስትደግፉ ‹‹የልማት አጋር››፣ ስትቃወሙ ‹‹አክራሪ ኃይሎች›› እየተባላችሁ የምትጠሩ ወገኖቼ ሁሉ!

ልብ ብላችሁ ስሙኝ! በፀሐዩ መንግሥታችን ላይ “ሙድ መያዝ” ትታችሁ አዲሳባ ዉስጥ መሬት ያዙ፡፡ የምማፀናችሁ ከልቤ ነው፡፡ የሸገር መሬት መጥፊያ ተቃርባለችና በሊዝም ይሁን በማኅበር ስም ንስሀ ግቡ!
ከተማጽኖዬ ቀጥዬ የማሳስባችሁ ነገር ቢኖር በዓለም ላይ ከኒዮርክም ሆነ ከፓሪስ፣ ከሎንዶንም ሆነ ከቶኪዮ በላቀ እጅግ ዉዱ ቁራሽ መሬት የሚገኘው በጭርንቁሷ ከተማ ሸገር ዉስጥ መሆኑን ነው፡፡
====================

አንዳንዴ እስቃለሁ፡፡ በምክንያትም ያለምክንያትም፡፡ ለምሳሌ “መሬት የሚሸጥ- የሚለወጠው መቃብሬ ላይ ብቻ ነው” ያለው ኢህአዴግ ሰልቫጅ መሬትን ሳይቀር በጨረቃ ብርሃን እያደነ እሳት በላሱ ካድሬዎቹ ደላላነት ሲቸበችብ ሳየው እስቃለሁ፡፡ ደግሞም የኢህአዴግ መቃብሩ አዲሳባ ዉስጥ ሊሆን እንደማይችል ሳስብ ሌላ ሳቅ እስቃለሁ፡፡ ቦታ የለማ! አዲሳባ ዉስጥ ኢህአዴግን የሚያህል ትልቅ ሬሳ የሚያስቀብር ባዶ ቦታ የት አለና?? የአራት ኪሎው ሥላሴ እንደሆን ሞልቷል፡፡

በአሁኑ ሰዓት እንኳን ለኢህአዴግ ይቅርና ለወፍራም ንብ የሚሆን መቀበርያ ቦታ የለም፡፡ ስፍራውን ያለፈው ሥርዓት አዛዦችና ናፋቂዎቻቸው ተቀራምተው ሞተውበታል፡፡ በተለይ የአጼው ሥርዓት አቀንቃኞች መለኛና አርቆ አሳቢ ሳይሆኑ አይቀሩም፣ አኗኗራቸውን ቀርቶ አሟሟታቸውን ያቅዱ ነበር ልበል? ሥላሴን አላስተረፉትም እኮ፡፡ አሁን ለኢህአዴግ መቀበርያ ተብሎ ትኩስ አጽም ተቆፍሮ አይወጣ ነገር!

ውድ የዲያስፖራ አባላት!
እውነት እውነት እላችኋለሁ…ከእንግዲህ በሸገር መኖርያ ቀርቶ መቀበሪያ ቦታ ማግኘት የማይታሰብ እየሆነ ነው፡፡ ካላመናችሁኝ የኮልፌ ጎረቤታሞቹን ፊሊጶስና እስላም መቃብርን ተመልከቱ፡፡ የቀብር ቦታቸው ወደ ጎን ሰፍቶ ሰፍቶ ሳይፈልጉት ኩታ ገጠም ሆነዋል፡፡ ከኩታ ገጠምነትም አልፈው ተቃቅፈዋል፡፡ አንዱ የሌላው ክልል ዉስጥ ገብቶ መላዕክትን ጭመር ማደናገር ይዘዋል፡፡ የሆነ “የተቀናጀ የሙታን ማስተር ፕላን” የሚባል ሰነድ ካልተዘጋጀላቸው ነገሩ ፈታኝ ነው የሚሆነው፡፡የተቀናጀ ማስተር ፕላን ደግሞ ራሱን የቻለ ጣጣ አለው፡፡ በሙታን መንደር ያልተፈለገ አመጽ ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡

ብቻ ምን አለፋችሁ….በአሁኑ ሰዓት ፊሊጶስና እስላም መቃብር በመሬት መጣበብ የተነሳ ተሳስመዋል፡፡             “ተዋዶ ያለበት እስላም ክርስቲያኑ” የሚለው የቴዲ ሙዚቃ አሁን አንድ ስንኝ መደረብ ሳያስፈልገው አልቀረም፡፡

“ተቀብሮ ባንድነት እስላም ክርስቲያኑ፣
ተዘነጋሽ እንዴ በሸገር መሆኑ?” የሚል፡፡

አንድ በኮልፌና አካባቢዋ በመቃብር ቆፋሪነት ሥርዓቱን ያገለገለ ካድሬ በጉዳዩ ላይ ያለውን ስጋት እንዲህ ሲል ገለፀልኝ….፣
“እንደምታየው መቃብር ስፍራዎቹ ተገጣጥመዋል፡፡ ይህ መተራመስ ከቀጠለ ገነት መግባት የሚገባቸው ነፍሶች ጀሐነም ሊወርዱ ይችላሉ፡፡”
======================

አንዳንዴ እስቃለሁ፡፡ በምክንያትም ያለምክንያትም፡፡
ለምሳሌ የፊት ገጹን ለመሬት ነክ ዜናዎች ብቻ በሊዝ የሸጠ የሚመስለው ግዙፉ የ“ሪፖርተር” ጋዜጣ የአዲሳባ መሬትን እንደ ሙዳ ሥጋ እየዘለዘለ በቋንጣና በክትፎ መልክ በየሳምንቱ ሲያስነበብ እስቃለሁ፡፡ ለምን በሉኝ! ከዓመታት በፊት የዚሁ ጋዜጣ ዘጋቢ የኦሮሚያ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከመሬት ጋር የሠሩትን ጠብደል ሙስና በመያዝ ‹‹አጋልጦታለሁ›› እያለ አስፈራርቶ በስሙ 500 ካሬ መሬት ቦታ መቀበሉን ስለሰማሁ፡፡ ነገሩ እውነት ከሆነ የመሬት ጥቅም የገባው የመጀመርያው የግልኪራይ ሰብሳቢ ጋዜጠኛ ያደርገዋል፡፡ እንዲያውም በ‹‹ Brown Envelope Journalism›› ዘርፍ ‹‹Pulitzer Prize›› ሊሸለም ይገባዋል እላለሁ፡፡ ታዲያ ይሄ በራሱ አያስቅም?

የኢብኮ ጋዜጠኞች እንኳ በዚህ የ “ቡጬ ጋዜጠኝነት” ጥርሳቸውን የነቀሉ ናቸው፡፡ እንዲያውም የዘወትር ፀሎታቸው “ጌታ ሆይ ‹‹አይናችን›› የሚባል ፕሮግራም ላይ ወይ መድበን ወይ አስመድበን” የሚል ነው፡፡ ‹‹ዐይናችን›› ፕሮግራም ላይ መስራት ‹‹ዐይን›› የሆነ ቦታ ያስገኛል ይላሉ በብዝሀነትና ሕዳሴ ድምጽ መንፈስ የተጠመቁ ባለሞያዎች፡፡

Amare Aregawi
Amare Aregawi

ዉድ የዋዜማ አድማጮችና አንባቢዎች!
ሪፖርተርን አንስቶ ጌታውን አለማንሳት አግባብ አይመስለኝም፡፡ ሙስናን ክፉኛ እንደሚጠየፉ የሚነገርላቸው የሪፖርተር ጌታ ይህን ስነምግባር የጎደለውን ጋዜጠኛቸውን የት እንዳደረሱት አላውቅም፡፡ አፈር ከድሜ አስግጠውት እንደሚሆን ግን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አፈር ከድሜ ለማስጋጥ የሚሆን ቦታ ካገኙ ነው ታዲያ፡፡ ልክ ነዋ! አዲሳባ ዉስጥ በአሁኑ ሰዓት አይደለም አንድን ጠብደል ሙሰኛ ጋዜጠኛ አፈር ከድሜ ለማብላት ከሲታ ዶሮን ለማረድስ በቂ ቦታ አለ እንዴ? እርሳቸውም ታዲያ የዋዛ አይደሉም፡፡ “እርሳቸው” ስል የ“ሪፖርተሩ”ን ጌታ ማለቴ ነው፡፡ “የዋዛ አይደሉም” ስል ደግሞ ከመሬት ጋር በተያያዘ ያላቸውን ንቃት ማለቴ ነው፡፡ በርግጥ ሰውየው የማስታወቂያ ቦታ ብቻም ሳይሆን የመሬት ቦታ ጥቅምም ገብቷቸዋል፡፡

እንደምታውቁት አሁን አሁን ተሰሚነታቸው እያየለ መጥቶ የአፍሪካ ቀንዱ ‹‹ሩፐርት መርዶክ›› እስከመባል የደረሱ ሰው ናቸው፡፡ ታዲያ እኚህ ሰው ሠርተው ጥረው ግረው ቢሆንም ቅሉ እዚያም እዚም ኪስ ቦታዎችን መያዛቸው አልቀረም፡፡

አትላስ አካባቢ ከነበራቸውና ንብረትነቱ የኪራይ ቤቶች ከነበረ አንድ ደከም ያለ ቪላ ከተፈናቀሉ ወዲህ ደግሞ ቀንቷቸዋል፡፡ ከአቶ በረከት ጋር በገቡት እልህ ይሁን አይሁን ባይታወቅም ብቻ ሰውየው በመገናኛ የካ ኮረብታ ላይ ከጀግናው ኃይሌ ገብረሥላሴ የሚጎራበት ቪላ ሸምተው ሰፊውን ሕዝብ ቁልቁል እያዩት ይኖራሉ ይላሉ የዚህ ጦማር ምንጮች፡፡ አንድ ያጣላል ያሉት እኚሁ የሪፖርተሩ አባት ቦሌ ሲቲ ፕላዛ ከ “ዶክተር” ቆስጠንጢኖስ የሚጎራበት አፓርትመንት ቢጤም ነበራቸው፡፡ ‹‹ሲኤምሲ›› አካባቢ ሌላ ጋሻ መሬት ይዘዋል የሚባል ወሬ ሰማሁ ልበል? ኸረ እንዲያውም ባለ 8 ፎቅ ሕንጻ እያጠናቀቁበት ነው ያሉኝ፡፡

የአፍሪካ ቀንዱ ሩፐርት መርዶክ በእርግጥም ዘይደዋል፡፡ ‹‹ክቡር ሚኒስትር›› አምድ ላይ በሚኒስትሮች ‹‹ሙድ እየያዙ›› ጎን ለጎን ደግሞ አዲሳባ ዉስጥ ኪስ መሬት መያዛቸው አርቆ አሳቢ የመረጃ ሰው እንደሆኑ የሚመሰክር ነው፡፡

‹‹ጫወታን ጫወታ ያነሳዋል›› ይላል የአዲስ አድማሱ ወገኛ ኤፍሬም እንዳለ፡፡ ስለ መሬት ሳነሳ መሬት ነክ ጉዳዮችን አድምቶ በመዘገብ የተካነ፣ በዚህም ስሙን ከመሬት በላይ ያኖረ አንድ የሪፖርተር ጋዜጣ ዘጋቢ ትዝ አለኝ፡፡ ስለ መሬት በመዘገብ የሚስተካከለው የለም፡፡ ለመሬት ካለው ቅርበት የተነሳ‹‹ምድር ጠፍጣፋ እንጂ ክብ አይደለችም›› ቢል እንኳ ይታመናል፡፡ በርግጥም ብርቱ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ከነከሰ አይለቅም፡፡ አከታትሎ በመዘገብ ይኸው ከህንዱ ካራቱሬ 98 ሺ ካሬ ያስመለሰ የቁርጥ ቀን ዘጋቢ ነው፡፡ በዚያ ላይ ቁርጥ ይወዳል፡፡ ከንቲባው ስብሰባ ላይ የሰፈር ስም ሲጠፋባቸው ይደውሉለታል ይላሉ ምንጮች፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም The Invisible Mayor እያሉ ያቆላምጡታል፡፡ ታዲያ ከአድናቆታቸው ብዛት እንዲህ ሲሉ ቀለዱበት አሉ፣ የሙያ ባልደረቦቹ፣
“አንተኮ ስለአዲሳባ መሬት የዘገብከው ዜና መሬት ላይ ቢዘረጋ ከአዲሳባ የቆዳ ስፋት ይበልጣል፡፡”
=================
አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የኢህአዴግ የቅርብ ዘመድ ናቸው፡፡ የእንግሊዙን ዲያጆ ጨምሮ ግዙፍ የቢራ ጠማቂ ፋብሪካዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ሕዝቡ ራሱን በቢራ እንዲችል፣ የመንግሥት ኪስ ደግሞ እንዲደረጅና እንዲዳብር ያደረጉ ተራማጅ የቢዝነስ አዋቂ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ አዲሳባ ሁለተኛውን ሸራተን እንድትገነባ ያስቻሉትም እርሳቸው ናቸው፡፡ ‹‹የቀጥተኛ የዉጭ ኢንቨስትመንት ማግኔት›› ይሏቸዋል በቅርብ የሚያውቋቸው፡፡

የትኛውም ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ በኢንቨስትመንት ጉዳይ እሳቸውን ሳይዝ ወደየትም ንቅንቅ አይልም፡፡ እንዲያውም ሚኒስትሮቻችን እርሳቸውን ሳይዙ ወደ ዉጭ አገር መንቀሳቀስ ፓስፖርት ሳይዙ ጉዞ እንደመጀመር ይሆንባቸው ይባላል፡፡

አቶ ዘመዴነህ የአዲሳባ መሬት ‹‹ቤንዚል የማይፈልቅበት ቤንዚል›› መሆኑ ከገባቸው ጥቂት ትውለደ ኢትዮጵያዊያን ይደመራሉ፡፡ አንደበተ ርቱእ የኢኮኖሚ ተንታኝ እንደመሆናቸው ታዲያ ዘመን መጽሔት በአዲሳባ የመሬት የዋጋ መናር ጉዳይ ላይ ጥያቄ አንስቶላቸው ነበር፡፡ እንዲህ አሉት፣

“…(በፊት)ሚስቴ ጁሊያ መሬት በሊዝ እንግዛ አለችኝ፡፡ ምን ያደርግልናል ስላት ወደፊት በጣም ጠቃሚ ይሆናል አለችኝ፡፡ ተደራድራ ይሄ አሁን ያለበንበትን 1ሺ ካሬ ቦታ በ2 ሚሊዮን ብር ገዛችው፡፡ ያኔ ተናድጄ ለአንድ ወር አላናገርኳትም፡፡ አሁን የቦታው ግምት 65 ሚሊየን ብር ደርሷል፡፡ (ከቦታችን) ተያያዥ በሆነው ቦታ 1500 ካሬ በሊዝ ወጥቷል፡፡ ብቻ በአጠቃላይ አሁን የያዝነው መሬት ግምት 140 ሚሊዮን ነው፡፡ የቦታውን ግምት በሰማሁ ቁጥር ሚስቴን ሁሌ በደስታ እስማታለሁ፡፡”

አቶ ዘመዴነህ እውነታቸውን ነው፡፡ የሚስታቸው ጁሊያን ጉንጭ ለካሬ መቶ ሺ ጊዜ አገላብጠው ቢስሙት ይገባታል እላለሁ፡፡ ቆንጆ ብቻ ሳትሆን በሳልና አርቆ አሳቢ ናት፡፡

የፍሊንስቶን ባለቤት አቶ ፀደቀ ይሁኔ ደግሞ በአንድ መድረክ ላይ እንዲህ አሉ፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ መሬት በአሁኑ ሰዓት ልክ ፕሌን ዉስጥ እንደሚገኝ የመንሳፈፊያ ጃኬት ነው፡፡ እንዴትም ዉድ ቢሆን ሁሉም ሰው አንድ እንዲኖረው ይፈልጋል”

እውነት ብለዋል፡፡ የአዲሳባ መሬት ወይን ነው፡፡ እያደር ይጣፍጣል፡፡ የዛሬ ሳምንት 5 ሚሊዮን ብር የተባላችሁት 250 ካሬ መሬት ተስማምታችሁ የክፍያ ቼክ ከደረት ኪሳችሁ እስክታወጡ 5.1 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት እንዲያውም የመሬት ዋጋ መጠነኛ መረጋጋት ታይቶበት ነው ከሰሞኑ ንረቱ የረገበው፡፡ እድሜ ለጨረቃ ቤት ገንቢዎች፡፡

ከምርጫ 97 በፊት በሕገወጥ መንገድ የመሬት ወረራ አካሄደው በድፍረት ጎጆ ቀልሰው የኖሩ 44 ሸህ 547 ዜጎች ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት ካርታ እየተሰራላቸው መሆኑ ከሰሞኑ ጦዞ የነበረውን የመሬት ዋጋ ሊያሰክነው እንደቻለ ነው በመሬት ጉዳይ ላይ ጥርሳቸውን የነቀሉ ደላሎች የሚተነትኑት፡፡ እንዴት ማለት ጥሩ ነው፡፡

ከ97 በፊት የጨረቃ ቤት ሰርተው ቤታቸው በአየር ካርታ ላይ የሚታይ ከሆነ ምንም ሕገወጥ ቢሆኑም እንኳ ለሁሉም ዜጎች ካርታ እንዲሰጣቸው መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ከያዙት መሬት ዉስጥ በሊዝ መነሻ ዋጋ እንዲወስዱ የሚፈቀድላቸው 75 ካሬ ሜትሯን ብቻ ነው፡፡ ባለቤቶቹ ቀሪውን ሕገወጥ ቦታ ወደ ካርታ ለማስገባት የሚከጅሉ ከሆነ ግን በአካባቢው አማካይ የሊዝ ዋጋ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡ ይህ መሆኑ ታዲያ እንዴት የመሬት ዋጋን ሊያረጋጋ ይችላል ለሚለው ጥያቄያችሁ ከዚህ እንደሚከተለው እመልሳለሁ፡፡

መሬት ወራሪዎቹ ለምሳሌ አንድ ሺህ ካሬ ቦታን ይዘዋል ቢባልና የያዙት ቦታ የሚገኘው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለከተማ ቤቴል አካባቢ ነው ብንል ቦታውን ሕጋዊ ለማድረግ ለ75 ካሬው 192 ብር የሊዝ መነሻ ዋጋ በድምሩ 14ሺ 4መቶ ብር ብቻ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡ ኾኖም ቀሪውን 925 ካሬ ሕጋዊ ለማድረግ ለአንድ ካሬ ወደ 8ሺ ብር አካባቢ ይጠየቃሉ፡፡ ይህም የአካባቢው አማካይ የሊዝ ዋጋ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የቦታው ግምት 7.5 ሚሊዮን ብር ይጠጋል ማለት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ብር ለጨረቃ ቤት ባለቤት የሚሞከር ባለመሆኑ ቤቱን ቆርሶ ለባለሀብቶች ለመሸጥ ይገደዳል፡፡ ይህም ወደ 50 ሺ ለሚጠጉ የጨረቃ ቦታዎች ላይ የሚተገበር በመሆኑ በከተማው መጠነኛ የመሬት ዋጋ መረጋጋትን እንዳስከተለና እንደሚያስከትል ተንታኞች ይስማሙበታል፡፡
=============

የአዲሳባ መሬት በሦስት የሊዝ መንገዶች ወደ አልሚዎች ይተላለፋል፡፡ አንደኛው መደበኛው ሊዝ ነው፡፡ ይህ በየወሩ የሚወጣ ሲሆን ይበርዳል ሲባል የሚግል በባህሪው የሰሞኑን ኦሮሚያ ወጣቶች አመጽን የሚመስል ነው፡፡ ሁለተኛው ‹‹ልዩ›› የሊዝ ጨረታ የሚባለው ነው፡፡ ይህ ለባለሐብቶች ቦታው ለምን እንደሚሆን አስቀድሞ በካቢኔ ተወስኖ የሚወጣ የጨረታ አይነት ነው፡፡ ሪልስቴቶች፣ ከ4 ኮከብ በላይ የሆኑ ሆቴሎች፣ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች በዚህ ዓይነቱ ጨረታ ይካተታሉ፡፡ ጨረታውን ‹‹ልዩ›› የሚያደርገው ለቀረበው መሬት አንድ ተጫራች ብቻ ቀርቦ እጅግ ዝቅተኛ ዋጋ ቢያቀርብ እንኳ ተፎካካሪ የለም ተብሎ ጨረታው የማይሰረዝ መሆኑ ነው፡፡ ሦስተኛው አግባብ ለኤምባሲዎችና ለእምነት ቦታዎች መሬት በምሪት የሚሰጥበት አሰራር ነው፡፡ ከዚህ አሠራር ዉጭ ስንዝር መሬት አትሰጥም ይላሉ ከተማዋን የሚዘውሯት ሹማምንት፡፡

የአዲሳባ አስተዳደር በአንድ ዓመት ብቻ 759 ቦታዎችን ቸብችቦ አራት ቢሊየን ብር ወደ ኪሱ አስገብቷል፡፡ ይህ ገንዘብ ኩራታችን የሆነው አየር መንገዳችን በተገባደደው ዓመት ካስገባው የተጣራ ትርፍ በላይ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ እስከዛሬ ለሕዳሴው ግድብ በቦንድ የተሰበሰበው ገንዘብ ግማሽ የሚሆን ነው፡፡ የሸገር መሬት ቤንዚል የማይወጣበት፣ ነገር ግን ራሱ ቤንዚል የሆነ ነው” የምለውም ለዚሁ ነው፡፡

ስኬት ኢንተርናሽናል መርካቶ ይርጋ ኃይሌ አጠገብ ለሚገኝና 242 ካሬ ለምትሆን ብጣሽ መሬት 86 ሚሊዮን ብር ሆጭ አድርጎ የከተማችንን የመሬት ዋጋ ከኒውዮርክ ተርታ ያሰለፈ የአገር ባለዉለታ ነው፡፡ ሁሴን ዳውድ የተባሉ ሰው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለ173 ካሬ ባዶ መሬት 8 ሚሊዮን ብር ለመክፈል የደፈሩ አገር ወዳድ ዜጋ ናቸው፡፡

ከተማዋ ወደ ጎን የመስፋቷ ነገር ከሰሞኑ ትኩሳት ጋር ተያይዞ እያበቃላት ይመስላል፡፡ ለዚህም ይመስላል መሀሉን ማፅዳት በስፋት የተያዘው፡፡ መጤ ሚሊየነሮችና ወርቃማ የሸገር መሬቶች ጋብቻቸው ቀጥሏል፡፡ በሚቀጥለው የሊዝ ጨረታ ለሞጃ ዜጎች ሊሞሸሩ ከተዘጋጁት ደናግላን ዉስጥ ተክለኃይማኖት፣ ሜክሲኮ ሸበሌ ጀርባ፣ አሜሪካን ግቢና አውቶቡስ ተራ ይገኙበታል፡፡ ‹‹ጋብቻው ሳይሆን ትዳሩ ነው ዋናው፡፡ ጥያቄው መሆን ያለበት ትዳራቸው ይዘልቃል ወይ ነው?›› ይላሉ ከዛሬ ይልቅ ነገ የሚያስጨንቃቸው የከተማዋ ልሂቃን፡፡ እውነት ለመናገር የአዲስ አበባን ነገ ማንም አያውቅም፡፡ መሪዎቿም፣ ነዋሪዎቿም፣ ወራሪዎቿም፡፡