PHOTO-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ ሆነው አዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር በአራት ወራት ውስጥ ብቻ በኮሮና ምክንያት ሁለት ሚሊየን አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ማጣቱን ዋዜማ ከቅርብ ምንጮች ስምታለች።


አስተዳደሩ ኪሳራው የደረሰበት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በከተማዋ ከተወሰዱ እርምጃውች መካከል አንዱ በሆነው  ሲኒማ ቤቶች እንዲዘጉ የሚለውን መመሪያ ተከትሎ የስራ እንቅስቃሴ በመቆረጡ  ነው፡፡


በአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ስር የሚገኙ ሲኒማ ቤቶች ቀደም ሲል ለዕይታ ከሚያቀርቧቸው የሀገር ውስጥ እና ውጭ ፊልሞች በተጨማሪ በርካታ ፊልሞች ተመርቀው ለመታየት ዝግጅት እያደረጉ በነበረበት ወቅት ህጉ መተላለፉ የከፋ  ኪሳራን በሙያተኛው እና በሲኒማ ቤቶቹ ላይ አስከትሏል፡፡


የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር የ 16 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግለት ጥያቄንም አቅርቧል። ገንዘቡን ያረጁትን ሲኒማ ቤቶች በማዘመን ለገበያ ተወዳዳሪ በማድረግ የተሻለ ትርፍ ለማግኘት አቅዷል። ገንዘቡ ከተፈቀደ አሁን ዝግ በሆነበት ወቅት ዕድሳት የማድረግ ዕቅድም አለ። በስሩ  ከሚተዳደሩ ሲኒማ ቤቶች መካከል  ሲኒማ አምፒር ፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ፣አምባሳደር ሲኒማ ይገኙበታል።


በየሲኒማ ቤቶቹ በየወሩ 15 ፊልሞች ለዕይታ ያቀርቡ የነበረ ሲሆን ተመልካቾችን በወር ውስጥ ስማንያ ሺህ ያህል ተመልካቾችን ያስተናግዳሉ። ፊልም ከማሳየት በተጨማሪም ከአዳራሽ ኪራይ ገቢን ያገኝ ነበር፡፡


የልማት ድርጅት የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር በስሩ 102 ሰራተኞችን ያስተዳድራል ፡፡ የገጠመውን ኪሳራ ተከትሎ በጠየቀው የ16 ሚሊየን ብር ድጎማ ኪሳራውን ለማካካስ እና ስራዉን እንደ አዲስ ለማነቃቃት  ሌሎች አማራጭ አሰራሮችን ለመከተል አውለዋለሁ ብሏል፡፡


የፊልም ፕሮዲሰሮች እና የተለያዩ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ሲኒማ ቤቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ተደርጎ ወደ ስራ እንዲመለሱ ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በአስተዳደሩ ስር የሚገኙት ሲኒማ ኢትዮጵያ አንድ ሺህ ዘጠና ተመልካቾችን፣ አምባሳደር ሲኒማ አንድ ሺህ አራት መቶ እንዲሁም ሲኒማ አምፒር ስምንት መቶ ተመልከቾችን ይይዛሉ ፡፡ ሲኒማ ቤቶቹ በግማሽም ሆነ ከዚያ በታች ተመልካቾን ቀንሰው አገልግሎት ቢሰጡ የሚሉ ሀሳቦችም እየተነሱ ይገኛሉ፣ ምንም እንኳን ገና ምላሽ ባያገኙም።

የአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት በአዋጅ ቁጥር 14/1985 ዓ.ም የመንግስት የልማት ድርጀት ሆኖ የተቋቋመ  ነው፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]