Arkebe Shops Photo-Fortune
Arkebe Shops Photo-Fortune

ዋዜማ ራዲዮ- ከ10 አመታት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በነበሩት አቶ አርከበ እቁባይ ሀሳብ አመንጭነት በጥጋጥግ ክፍት ቦታዎች በጊዜያዊነት በብረት የተሰሩ እና ለስራ አጥ ወጣቶች ተብለው የተገነቡት ትናንሽ ሱቆች በአዲሱ የቀን ገቢ ግምት መሰረት አመታዊ ሽያጫችሁ ከ500 ሽህ ብር በላይ ነው በሚል ወደ ከፍተኛ ግብር ከፋዬች ጎራ መመደባቸው  ተቃውሞ አስነስቷል።

ቁጥራቸው ከ5ሽህ በላይ የሚገመተው የአርከበ ሱቅ ባለቤቶች ቀደም ሲል ንግድ ፈቃድ ከማውጣትና አመታዊ የስራ ግብር ከመክፈል ውጭ በየትኛውም የከፍተኛና መካከለኛ ግብር ከፋዬች ዘርፍ ውስጥ ያልነበሩ ሲሆን በአዲሱ የቀን ግብር ትመና ከከፍተኛ ግብር ከፋዬች ዝርዝር ጎራ መካተታቸው ተቃውሞ አስነስቷል።
የቀን ገቢ ግምቱ ከተሰማ በኅላ በተለያዩየአዲስ አበባ ከተማ ጥጋጥግ ውስጥ ሱቅ ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ሰዎችን ዋዜማ አነጋግሯ እንደሰማችው ከሆነ ድርጊቱ ከስራ ውጭ ሊያደርጋቸው እንደሚችልና ሱቆቹን እንዲያስረክቡ የሚያስገድዳቸው መሆኑን ነው።

ቀደም ሲል በአነስተኛ ደረጃ እንዲነግዱ በተሰጣቸው ሱቅ ውስጥ የሚከናወነው ንግድ ሌሎች ግብር ከፋዬችንና በሽያጭ ማሽን የሚነግዱን ሰዎች እየጎዳ ነው ግብር ስለማይከፍሉም በአነስተኛ ግብይት ሸቀጦችን ይሽጣሉ በሚል በሚል ስሞታ ይቀርብባቸው ነበር።
የአዲስ አበባ አስተዳደር በተለያዩ የመንገድ ስራዎቹ እና ከተከፈቱበት አላማ ውጭ ሆነዋው ለሌሎች ሰዎች በወር እስከ 10ሽህ ብር ድረስ ተከራይተው አግኝቻቸዋለሁ በሚል የተወስኑ ሱቆቹን ከመንጠቁም በላይ የፈረሱ መኖራቸውም ይታወቃል።
“የአሁኑ የቀን ገቢ ግምት የተጣለብን በርግጥ በዚያ ደረጃ ገቢ ታገኛላችሁ ተብለንና ጉዳዩ እውነታ ኖሮት ሳይሆን በሌሎች ነጋዴዎች ላይ የተጣለውን ከአቅም በላይ የሆነውን ግምትና ግብር ያስነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የተወሰነብን እርምጃ ነው” ሲሉም ባለሱቆቹ ለዋዜማ ቅሬታቸውን ነግረዋል።
በመጭዎቹ ቀናት ቅሬታቸውን ለመንግስት ለማቅረብ እየተነጋገሩ መሆኑንም ገልፀዋል።
በአብዛኛው ለወጣቶች እንዲሁ ሴት የኢህአዴግ ፎረም አባላት ቀደም ሲል የተሰጡት የአርከበ ሱቆች ጉዳይ በጊዜያዊነት ስራ የሚሰራባቸው ይሆኑና ወጣቶቹና ሴቶቹ እራሳቸውን ከቻሉ በኃላ የሚለቁት ነው ተብሎ የነበረ ቢሆንም በአገልግሎት ላይ ከ10 አመታት በላይ እያስቆጠሩ ይገኛሉ ።
አዲስ በተሰራው የቀን ገቢ ግምት መሰረት ሱቆቹ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን እንዲያስገቡ መታዘዛቸውን ለዋዜማ ነግረዋል።