የሕወሓት አጋር የሆነውና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከክልሉ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሙን ዋዜማ ስምታለች። በምስጢር የተያዘው ስምምነት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለህዝብ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ዝርዝሩን ያንብቡት

ዋዜማ- የአማራ ክልል መንግሥት እና በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀሰው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን) ድርድር ተቀምጠው ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ዋዜማ ሰምታለች። 

የክልልነት ጥያቄ አንግቦ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን የሚንቀሳቀሰው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን) እና የክልሉ መንግሥት በተለይ ባለፈው 2015 ዓ.ም ተደጋጋሚ የሰላም ንግግሮችን ሲያደጉ ነበር። 

ይሁን እንጂ በአገር ሸማግሌዎች አመቻችነት የተሞከረውን ሽምግልና ታጣቂ ኃይሉ አልቀበልም በማለቱ መስተጓጎሉ የሚታወስ ነው።

ሁለት ጊዜ የተሞከረው የሽምግልና ጥረት ከከሸፈ በኃላ፣ የክልሉ መንግሥት ከታጣቂ ኃይሉ የሰላም ስምምነት ተብሎና ደረጃው ከፍ ብሎ እንዲደረግ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ሁለቱ ወገኖች ተደራድረዋል።

ድርድሩ የተካሄደው አዲስ አበባ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ለስምምነት የበቃው ተደራዳሪ አካላት በተደጋጋሚ ተገናኝተው ሰፊ ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው። 

ሁለቱ ወገኖች የመጨረሻው ድርድር አድርገው የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ከተደራዳሪዎቹ አንዱ ለዋዜማ አረጋግጠዋል፡፡ 

በድርድሩ ሁለቱን ወገኖች በማቀራረብ በዋና አደራዳሪነት የተሰየመው፣ መከላከያ ሚኒስቴር መሆኑን ዋዜማ ከድርድሩ ተሳታፊዎች ሰምታለች። 

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የድርድሩ ተሳታፊ ሰምምነቱ ይፋ የሚደረግበት ጊዜ ምስጢራዊነት አንዱ  የስምምነቱ አካል መሆኑን ነግረውናል። የስምምነት ሰነዱን ይዘት በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ምንጩ ምንም እንኳን የሰነዱን ዝርዝር ከመናገር ቢቆጠቡም፣ በጥቅሉ “ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ ተስማምተናል” ሲሉ ገልጠውታል። ሰፊ ክርክር የተደረገበት ነው የተባለለት ድርድር እንደ ክልልም ይሁን እንደ አገር ጠቃሚ በሆነ አግባብ ተፈጽሟል ተብሏል።

በተለይም ታጣቂ ኃይሉ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ሰላም እንደሚፈጥርና ሁለቱን ተሰማሚ ወገኖች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ምንጩ ጠቁመዋል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውና የሰላም ንግግሩን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ  ሌላኛው የዋዜማ ምንጭ፣ ስምምነቱ በአዴን በኩል ትጥቅ መፍታትና ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሸጋገር ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ መንግሥት በኩል ደግሞ አዴን ያነገበውን ራስን በራስ የማስተዳደር ብሎም የክልልነት ጥያቄ ማስተናድ የሚሉት ጉዳዮች ዋናዎቹ መሆናቸውን ምንጩ አመላክተዋል።

በአማራ ክልል መንግሥት እና በአዴን መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት በመጭው ታህሳስ 21/2016 ዓ.ም ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። 

በድርድሩ ላይ ከአማራ ክልል መንግሥት በኩል የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው የመሩት ቡድን ተሳትፏል። 

እንዲሁም በአደራዳሪነት በተሰየመው መከላከያ በኩል ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ተሳትፈዋል። በዋና አደራዳሪነት የተቀመጠው መከላከያ የሰላም ስምምነቱ ተዋዋይ ወገኖች፣ ያቀረቧቸውን መከራከሪያ ነጥቦች አቀራርቦ የጋራ መግባባት የተደረሰበትን ሰነድ አፈራርሟል።

ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ ሲሞከር የነበረው የሰላም ንግግር በወቅቱ ያልተሳካው፣ ታጣቂ ኃይሉ ከድርድር በታች ያሉ የሰላም መንገዶችን አልቀበልም፣ የምንታገልበትን አላማ በድርድር ማስጠበቅ አለብኝ በማለት ነበር።

በ2013 ዓ.ም የተጀመረው የታጣቂ ኃይሉ እንቅስቃሴ፣ ዋና አላማ አካባቢውን በክልልነት የማደራጀት መሆኑን ሲገልጥ ነበር።

አዴን ዋነኛ አላማውን “የአገው ክልላዊ መንግሥት መመስረት” ነው ብሎ የተነሳ የፖለቲካ ፓርቲ ተገንጣይ  ክንፍ ነው። ታጣቂ ኃይሉን የሚመሩት በተፎካካሪ ፖርቲነት በአካባቢው የሚንቀሳቀስው የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ውስጥ እስከ ሥራ አስፈጻሚ አባልነት ሚና የነበራቸው ናቸው።

የዛሬዎቹ የአዴን መሪዎች ከአገው ብሔራዊ ሸንጎ ከተገነጠሉ በኋላ፣ ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር ተሰልፈው በሰሜኑ ጦርነት ተሰታፈዋል። 

በወቅቱ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ቁርሾ ውስጥ ገብቶ ከነበረው ህወሓት ጋር የተሰለፈው አዴን፣ ከጦርነቱ መቋጨት በኋላ የተወሰኑ የትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎችን ይዞ ቀይቷል። 

አዴን በፌዴራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተፈረመውኝ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት አልቀበልም ብሎ መቆየቱ የሚታወስ ነው። በዚህም በትግራይ ክልል አዋሳኝ የሚገኙ የተወሰኑ በዋግ ኽምራ ዞን ሚገኙ የወረዳ ቀበሌዎችን ተቆጣጥሮ ቆይቷል።

የአዴን አመራሮች በዋናነት መቀመጫቸውን በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ አድረገው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። አጋራችን ከሚሉት ህወሓት ጋርም ያላቸው ግንኙነት በጋራ ተሰልፎ ከመዋጋት የዘለቀ ነበር።

የአዴን ታጣቂ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በዋግ ኽምራ ዞን ሰፊ እንቅስቃሴ የነበረው ቢሆንም፣ በሰላም ስምምነቱ በኋላ በውስን ቀበሌዎች ላይ ተገድቧል።

የሦስት ዓመት ገደማ ዕድሜ ያለው አዴን ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ያለው ቅርበት መሬት የረገጠ እንዳልሆነም ይሰማል። ውልደቱና አብዛኛውን ዕድሜውም ከሰሜኑና የትግራይ ጦርነት ወቅት ጋር የተገናኘ ነው።

አዴን ይዞት የተነሳው አገውን ክልል የማድረግ አላማ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለማረጋገጥ እንደሆነ ሲገልጥ ይደመጣል። 

ዋዜማ የተመለከተችው ስለ አዴን እንቅስቃሴ አላማና መዳረሻ የሚያትተው አስረጅ ማብራሪያ “አገው የብሔር ጭቆናና የግዛት ወረራ ተፈጽሞበታል”  ይላል። [ዋዜማ]