IMG_1680ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራሉ ዋና ዓቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ለዓመታት በርካቶችን ባልተጨበጠ የሽብር ወንጀልና ተያያዥ ከፍተኛ ወንጀሎችን በመክሰስና በማሰፈረድ የሚታወቁትን ዓቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝን ከኃላፊነት በማሰናበት በቦታቸው አቶ ፍቃዱ ፀጋን መሾሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዋና ዓቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ አቶ ብርሃኑ ሐምሌ 12፣ 2010 ዓ.ም የመስሪያ ቤታቸውን የለውጥ ሂደት (ሪፎርም) በተመለከተ የተለያዩ ርምጃዎችን ለስራተኞቹ ያስተዋወቁ ሲሆን በአቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ ሲመራ የነበረውን ጭምሮ የበርካታ ዳይሬከቶሬት ኃላፊዎችን በማንሳት በአዲስ እንደተኩ የውስጥ ምንጮች ለዋዜማ አረጋግጠዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ ለዓመታት የሽብርና የተደራጁ ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የዚሁ የፌደራሉ መንግሰት ዋና ዐቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ቁልፍ ሰዎች አንዱ እነደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡

በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላቶቻቸውን እንዲሁም የመብት አቀንቃኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪዎችንና የተለያዩ ግለሰቦችን የመንግሰት አቃቤ በመሆን በተለያየ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በሽብርና በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ክስ በመመስረትና በማሰፈረድ ይታወቃሉ፡፡

እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጉዳይ በበጎ የማይንሳው አቶ ብርሃኑ ወንድምአገኝ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በእስር የሚገኙ ተከሳሾችን የፍርድ ሁደት በማጓተትና በእስር የሚገኙ ታራሚዎች የመብት ጥሰት እዲፈጸምባቸው ተደጋጋሚ ምክንያት ይሆኑ እንደነበርም ወቀሳ ሲሰማባቸው ይሰማል፡፡
ዋና ዓቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በጻፉት የሹመት ደብዳቤ አቶ ፍቃዱ ጸጋ የተባሉ ነባር የህግ ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ወንድምአገኝን እንዲተኩ ማድረጋቸውንና አቶ ተመስገን ላጲሶን በምክትል ዳይሬከተር መሾማቸውን የዋዜማ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ሌሎች በርካታ ሀላፊዎችም በአዳዲስ የተተኩ ሲሆን ለሹም ሽር ምክንያት የሆነው የቀደሙት ሀላፊዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የነበሩ በመሆናቸው ጭምር እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ስር የሚቀጠሩ ዓቃብያነ ህጎች ከዚህ በኋላ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባልነት ነጻ መሆን እንዳለባቸው የሚያስገድድ ድንጋጌ የያዘ መመሪያ መውጣቱ ታውቋል፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/cjCUF-UkvqA