ዋዜማ ራዲዮ- በሶማሊ ክልል “ሄሎ ካሽ” በሚባል የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቱ የሚታወቀው የሶማሊ ማይክሮፋይናንስ ተቋም ወደ ሸበሌ ባንክ አደገ።

ባለፈው አመት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ባንክ የማደግ  ፈቃድ ያገኘው ሸበሌ ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚያቀርብ መሆኑ ተገልጿል ። በሶማሊ ክልል ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ በተካሄደ ስነስርዓት አገልግሎቱን በይፋ የጀመረው ሸበሌ ባንክ በክልሉና ከክልሉ ውጭ በተለያዩ ከተሞች 43 ቅርንጫፎች አሉት ።

ሸበሌ ባንክ 500 ቋሚ ሰራተኞችን ይዞ  3.7 ቢሊየን ብር ጠቅላላ የሐብት መጠን በማስመዝገብ በ2013 አመተ ምህረት ከብሔራዊ ባንክ  ባገኘው እውቅና  ወደ ተሟላ የባንክ አገልግሎት ማደግ ችሏል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ዑመር በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባንኩ የመጀመሪያው በሶማሊ ተወላጆች የተቋቋመ ባንክ መሆኑን ገልጸው የባንኩ ስኬት በባለቤቶቹ ትጋት በአመራሮቹ ብቃት እንዲሁም በህዝቡ ድጋፍ የሚወሰን ነው ብለዋል። 

በ2011 ዓ.ም የሶማሊ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም    ‘ሄሎ ካሽ”   በሚል የገንዘብ ግብይትና ዝውውር አገልግሎት መስጠት የጀመረው ተቋሙ መቶ ሺህ  ለሚሆኑ የአካባቢው ዜጎች የስራ ዕድል ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን ከነዛ ውስጥም 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

በማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱም እስከ አሁን 1 ሚሊየን 3 መቶ ሺህ በላይ የሚደርሱ ደንበኞች  ያሉት ሲሆን ከዚህ ቀደም በዝቅተኛ የንግድ ስራ ለተሰማሩ ዜጎች የሚያደርገው የፋይናንስ አቅርቦት እንዳለ ሆኖ በቀጣይ በተለይ በክልሉ እያደገ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በማሟላት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል ።

ሸበሌ  ባንክን   በአሁኑ ጊዜ  አቶ ከዲር አህመድ በዋና ስራ አስፈጻሚነት እየመሩት እንደሚገኙ የክልሉ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ዘገባ ያመለክታል ።

የሶማሊ ማይክሮፋይናንስ ተቋም ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ጸደይ ባንክና ከኦሮሚያ ክልል ብድርና ቁጠባ ተቋም  ሲንቄ ባንክ በመቀጠል በአገሪቱ ራሱን ወደ ባንክ ያሳደገ ሶስተኛው ተቋም ሆኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መሰል የብድርና ቁጠባ ተቋማት ወደ ንግድ ባንክ ደረጃ ማደግ የሚችሉበትን መመሪያ በፈረንጆች 2020 አጋማሽ ላይ ማውጣቱ የሚታወስ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]