ዋዜማ- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መንግሥት በአማራ ክልል ያወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቆይታው “ከአንድ ወር ወይም የተወሰኑ ሳምንታት” እንዳይበልጥ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

ኮሚሽኑ ይህን የጠየቀው፣ መንግሥት በክልሉ የተፈጠረው ግጭትና የሰላም መደፍረስ ባለፉት ጥቂት ቀናት መረጋጋቱን በይፋ እንደገለጸ በመጥቀስ ነው። ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ የሰብዓዊ መብቶች ምክረ ሃሳቦችን የያዘ ባለ 26 ገጽ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን ገልጧል።

ኮሚሽኑ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን የሚያጸድቀው ከኾነ፣ አዋጁ ከአማራ ክልል አልፎ በጠቅላላ በአገሪቱ ተፈጻሚ እንዳይኾን ጭምር በሪፖርቴ ለምክር ቤቱ ምክረ ሃሳብ አቅርቤያለኹ ብሏል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጀ ላይ “ለትርጉም አሻሚ” የኾኑና “ተለጥጠው ተገቢ ላልኾነ አፈጻጸምና ለሰብዓዊ መብቶች አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ” ድንጋጌዎች ላይ ምክር ቤቱ ሊያደርጋቸው የሚገባቸውን ማሻሻያዎች በሪፖርቱ ማካተቱን ኮሚሽኑ ጨምሮ አመልክቷል።

ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ በሚያደርገው ውይይት፣ የኮሚሽኑን ምክረ ሃሳቦች ባግባቡ እንዲያጤናቸው ኮሚሽኑ ጠይቋል። የምክረ ሃሳብ ሰነዱ፣ ምክር ቤቱ ከአዋጁ ከባቢያዊና የጊዜ ተፈጻሚነት ወሰን በተጨማሪ፣ በተለይ አዋጁ የጣላቸውን ክልከላዎችና ግዴታዎች፣ አዋጁ ለመንግሥት የሰጠውን ሥልጣን፣ የሕዝብ ተወካዮችንና ዳኞችን ያለምክር ቤቱ ውሳኔ ያለመያዝና ያለመከሰስ ልዩ መብት ጥበቃ እንዲኹም የአዋጁ አንቀጾች “ከጥብቅ አስፈላጊነት”፣ “ከተመጣጣኝነት” እና “ሕጋዊነት” አንጻር ያላቸው ቅቡልነት በጥንቃቄ አንዲመረምር የሚጠይቅ እንደኾነ ተገልጧል።

ባኹኑ ወቅት እረፍት ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልልና “እንዳስፈላጊነቱ” በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ጭምር ተፈጻሚ ይኾናል በተባለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ለመስጠት፣ በቀጣዩ ሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ ይታወሳል።

የአገሪቱ ሕገመንግሥት አስፈጻሚው አካል የሚያውጃቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር በ15 ቀናት ውስጥ ማጽደቅ ወይም ውድቅ ማድረግ እንዳለበት ያዛል። [ዋዜማ]