Afarዋዜማ ራዲዮ- ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ የባለቤትነት ሽርክና እንድታገኝ በመሠረተ ሃሳብ ደረጃ ከጅቡቲ መሪዎች ጋር መስማማታቸው የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ኢሳዎች በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ኢሌ አስተዳደር ዘይቤ ላይ ካነሱት ተቃውሞ ጋር ተገጣጥሟል፡፡

እንደተባለው ኢትዮጵያ የኢሳዎች የበላይነት ባለባት ጅቡቲ የወደብ ባለቤትነት ድርሻ ካገኘች በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ፖለቲካ፣ ፌደራል መንግስቱ ከአፋር እና ሱማሌ ክልሎች ጋር በሚኖረው ግንኙነት እና ከመቶ ዐመታት በላይ በዘለቀው የአፋር እና ኢሳ ጎሳ ግጭት ላይ የራሱ ጉልህ አንድምታ እንደሚኖረው ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይ እንደ መካከለኛው ምስራቅ ኩርዶች በተለያዩ የቀጠናው ሀገሮች ተበታትነው የሚኖሩት አፋሮችና ኢሳዎች ግጭት ክፍለ አህጉራዊ ባህሪ ያለው ሲሆን በተለይም ከጅቡቲ ውስጣዊ ፖለቲካ እና ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ካላት ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ነው ያለው፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

ኢትዮጵያ ደንበኛ ብቻ ሆና ከቆየችበት ጅቡቲ ወደብ የባለቤትነት ድርሻ እንድትይዝ በመሰረተ ሃሳብ የተደረሰው ስምምነት ወደ ተግባር ከተተረጎመ በርግጥም ለዘመናት ሁነኛ መፍትሄ ባጣው የአፋር እና ኢሳ ጎሳ ግጭት ላይ ዘላቂ አንድምታ ነው የሚያስከትለው፡፡

ጅቡቲ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ያላት ጥቅም ከኢሳ ጎሳ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፡፡ በሱማሌ ክልል፣ ሽንሌ ዞን ሦስት መቶ ሺህ ኪውቢክ ሜትር የሚገመት ንጹህ መጠጥ ውሃ ለ30 ዐመታት በነጻ አልምታ እንድትጠቀም ከተፈቀደላት ወዲህ ጥቅሟ ኢኮኖሚዊ ጭምር ሆኗል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ ወደ ጅቡቲ ሲሄዱ አቶ አብዲ ኢሌን አስከትለው መጓዛቸውም ተገቢ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ኢሳዎችና አፋሮች የሚቆጣጠሩት አካባቢ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር እና የወደፊቱ ነዳጅ መስመር መተላለፊያ ጭምር ነው፡፡ የሁለቱ ጎሳዎች ግጭት እና በሽንሌ አካባቢ ዞን የሚከሰት አለመረጋጋት ጅቡቲ ወደፊት በምትዘረጋው የውሃ ቧንቧ መስመር ላይም ስጋት ሊደቅን ይችላል፡፡ ባጭሩ አካባቢው ከኢትዮጵያና ጅቡቲ ብሄራዊ ደኅንነት ጋር ግንኙነት ያለው ስለሆነ የክልሉ ሰላም እና መረጋጋት የጅቡቲን ትኩረት በእጅጉ ይስበዋል፡፡ የሁለቱ ጎሳዎች ግጭትም በቀላሉ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ የኢትዮጵያንም ሆነ የጅቡቲን ውስጣዊ የጎሳ ፖለቲካ የመለወጥ አቅም አለው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሸንሌ ዞን ኢሳዎች የአብዲ ኢሌን አስተዳደር የመልካም አስተዳደር ብልሹነት፣ ስር የሰደደ ሙስና እና የዘመድ አዝማድ አሰራር አስፍኗል በማለት በአደባባይ ሲቃወሙ ሰንብተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የኢሳዎች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት የገነነባት ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ካሳየችው አዲስ መቀራረብና በሱማሌ ክልል ከሚታየው ተቃውሞ አንጻር አሁንም ሆነ ወደፊት ምን ዐይነት ታሳቢ አካሄዶች ይኖሯት ይሆን? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ሱማሌ ከልል ኢሳ ጎሳ ሽማግሌዎች ከአብዲ ኢሌ መንግስት ጋር ስምምነት በመፍጠር አብረው እንዲሰሩ መገፋፋት አንዱ የጅቡቲ ታሳቢ አካሄድ ሊሆን ይችላል፡፡ ጅቡቲ በቅርቡ ለኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነት ድርሻ ለመስጠት እንደምትስማማ ፍንጭ ከመስጠቷ አንጻር ስናየው ይሄ ታሳቢ አማራጭ ለጅቡቲያዊያኑ መሪዎች አዋጭ እና ቀላል አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

የአቶ አብዲ መንግስታዊ አመራር ኢሳዎች ያነሷቸውን ቅሬታዎች የማይፈታ ሆኖ ከቀጠለ እና የክልሉን ልዩ ፖሊስ በመጠቀምም ሰላማዊ ተቃውሟቸውን በሃይል በመጨፍለቁ ከገፋበት ግን ጅቡቲ ሌሎች ሁለት ታሳቢ አማራጮችን ልትከተል እንደምትችል ግምት መያዝ ይቻላል፡፡

ባንድ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት የኦጋዴን ተወላጁን አቶ አብዲ ኢሌን በሌላ ጎሳ ከተቻለም ደሞ በኢሳ ጎሳ ተወላጅ እንዲተካቸው በተዘዋዋሪ መጎትጎት አንዱ ታሳቢ አካሄዷ ልታደርገው ትችል ይሆናል፡፡ አቶ አብዲ በቅርቡ ባካሄዱት የክልሉ ካቢኔ ሹም ሽርም የኢሳ ጎሳ ተወላጅ የሆኑትን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን አቶ አብዲከሪም ኢጋልን ከስልጣን ማሰናበታቸው ብዙ ጥያቄ አስነስቶባቸዋል፡፡ የጅቡቲ ኢሳ ልሂቃን አንዱ ፍላጎት ኢሳዎች በአብዲ ኢሌ ጠንካራ ክንድ ታፍነው ከተዳከሙ ለባላንጣዎቻቸው አፋሮች የልብ ልብ እንዳይሰጣቸው ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዐመታት ወደ ኢሳዎች ያዘነበለው የሁለቱ ባላንጣ ጎሳዎች የሃይል ሚዛንም እንዳይዛባና የኢሳዎች ክልላዊ እና ቀጠናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነትም እንዳይሟሽሸም ስጋት አላቸው፡፡ ለዚህም ነው የአብዲ ኢሌን አካሄድ በቅርብ እንደሚከታተሉ የሚታመነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ቢሆን ጅቡቲን ለማስደሰት ሲል የአብዲ ኢሌ መንግስት ኢሳዎችም ሆኑ ሌሎች ጎሳዎች የሚያነሱባቸውን ቅሬታዎች በቶሎ እንዲፈታ፤ ኢሳዎችንም በስልጣን እና ሃብት ክፍፍል ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር እንዲዘረጋ ሊገፋፋ ይችላል፡፡ የክልሉ ስልጣን አሁን ካለበት የኦጋዴን ጎሳ የበላይነት ወደ ኢሳዎች የበላይነት እንዲዞር መስራቱን ግን የሚሞክው አይመስልም፡፡

በርግጥ የክልሉ ኢሳዎችም አሁን እያነሱት ባለው ተቃውሞ ስለ መልካም አስተዳደር ብለሽት እና ሙስና እንጅ የጎሳ የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ እንደሌላቸው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የመብት ተሟጋቾቻቸውና የክሉሉም አንዳንድ ነዋሪዎች ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ የሆነው ሆኖ ኢሳዎችን ለይቶ በስልጣን ተጠቃሚ ለማድረግ ቢሞከር ከሚያስከትለው የሃይል ሚዛን መፋለስ አንጻር አፋሮችን ከምንጊዜው በበለጠ ክፉኛ ማስቆጣቱ አይቀርም፡፡

ጅቡቲ ይሄን ታሳቢ አካሄድ ካልተከተለች ወይንም ሞክራው ውጤት ካላገኘችበት ደሞ የኢሳ ተወላጅ የሆኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለሃብቶቿ እና አንዳንድ ፖለቲከኞቿ የኢትዮጵያ ኢሳዎች የአብዲ ኢሌን አስተዳደር በሃይል ጭምር እንዲታገሉት በተዘዋዋሪ በጦር መሳሪያ ጭምር ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚለውን ሌላ ታሳቢ አማራጭም በመጠኑ ግምት ውስጥ ማስገባት ይቻል ይሆናል፡፡ አካባቢው ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ዝውውር ያለበት በመሆኑ ከጅቡቲ ወደ ሱማሌ ክልል ሕገ ወጥ ጦር መሳሪያ ማስገባትም ከባድ እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ አሁን አዲስ መልክ እየያዘ ካለው የሁለቱ ሀገሮች ጥብቅ ትስስር አንጻር ግን እንዲህ ዐይነቱ ሉዓላዊነትን የሚዳፈር እና ግጭትን የሚያፋፍም ድርጊት ለጅቡቲያዊያኑ ፈጽሞ አይጠቅማቸውም፡፡ ቢያስቡተም እንኳ ከአማራጮች ሁሉ የመጨረሻው አማራጫቸው እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ በርግጥም እስካሁን ድረስ በኢሳዎች የሰሞኑ ተቃውሞ የጅቡቲያዊያኑ እጅ ስለመኖሩ የሚያሳይ ሁነኛ ፍንጭ የለም፡፡

ወደፊት በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል የሚጠበቀው ጥብቅ ትስስር የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ይቅርና ላለፉት ጥቂት ዐመታት ባለው ነባራዊ ሁኔታም የኢትዮጵያ ኢሳዎች በአፋሮች ላይ በአንጻራዊ ሃይል ሚዛን ረገድ የበላይነትን ይዘው ነው እየቀጠሉ ያሉት፡፡ አፋሮች የራሳቸውን ክልል ሲያገኙ ኢሳዎች በሽንሌ ዞን ብቻ ተወስነው ቢቀሩም ባለፉት ዐመታት በተካሄዱት ግጭቶችና መስፋፋቶች ግን እንደ ገዳማይቱ እና ሚሌ ያሉ የቀድሞ የአፋር ግዛቶችን መቆጣጠር ችለዋል፡፡ ከጊዜ ወደጊዜም አፋሮች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ደኅንነት ወስጥ ያላቸው ሚና ቀንሷል ማለት ይቻላል፡፡

ባሁኑ ጊዜ በማዕከላዊው መንግስት በኩል ጎልቶ የሚታየው ሚና የሱማሌ ክልል ሚና እንጅ የአፋሮች ድምጽ እንኳ ቀዝቀዝ ብሏል፡፡ እንዲያውም በውጭ ሀገራት ያሉ የአፋር ጎሳ ተወላጆች የፌደራሉ መንግስት በሁለቱ ጎሳዎቸ ግጭት ለኢሳዎች እንደወገነ በመግለጽ ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ ኢሳዎች ከጅቡቲ ድጋፍ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ አፋሮች ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ኢሳዎች በድንበር፣ ግጦሽ፣ መጠጥ ውሃና ግዛት ማስፋፋት ሳቢያ በህዝባችን ላይ ከሚከፍቱበት ጥቃቶች ራሱን እንዳይከላከል ደሞ የኢትዮጵያ መንግስት በጅቡቲ ወደብ ፖለቲካ ምክንያት እንቅፋት ሆኖብናል ባይ ናቸው- በተለይ በውጭ ሀገራት ያሉ የአፋር ተወላጆች፡፡

በርግጥም ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ከጅቡቲ፣ ሱማሌላንድ እና ከዋናዋ ሱማሊያ ጋር በወደብ እና ጸጥታ መስኮች እየገባበት ካለው ውስብስብ ጅኦፖለቲካ አንጻር ከአፋሮች ይልቅ በይፋም ሆነ በስውር የኢሳዎችን ጥቅም ለማስቀደም መትጋቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ኢሳዎች ደሞ ላሁኑ ተቃውሟቸው በክልሉ መንግስት ላይ እንጅ በፌደራሉ መንግስት ላይ አለመሆኑን ደጋግመው እየገለጹ ነው፡፡

ምንም እንኳ የአብዲ ኢሌ ክልላዊ መንግስት የዘመድ አዝማድ ሙስና መረብ ሲተበተብ የፌደራሉ መንግስት አበጀህ በሚል አኳኋን ዝም ብሎ እንደሚያየው፤ እንዲያውም የፌደራሉ መንግስት ጸጥታ ተቋማት ጥበቃ እና ድጋፍ እንደሚያደረጉለት ቢታወቅም ኢሳዎች ግን ጣታቸውን በፌደራል መንግስቱ ላይ አለመቀሰራቸው በከፊል ከአፋሮች ጋር ባላቸው ውጥረት የተሞላበት ግንኙነት ሳቢያ ፌደራል መንግስቱን ማስቀየም ስለማይፈልጉ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከድንበር ባሻገር ያሉ የኤርትራም ሆነ የጅቡቲ አፋሮች ደሞ ከመንግስታቱ ጋር በተቃዋሚነት ጎራ ተሰልፈው ስላሉ ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት ከጎረቤት ሀገራት ይመጣብኛል ብሎ የሚሰጋው የብሄራዊ ደኅንነት አደጋ እምብዛም ስለሆነ የአፋሮችን ነገር በሁለተኛ ደረጃ እንዲያየው ሳያደርገው አልቀረም፡፡

እንግዲህ ቀደም ሲል በውሃ፣ ግጦሽ፣ ከበት ዝርፊያና በባህላዊ ተቃርኖዎች ተወስኖ የኖረው የኢሳ እና አፋር ግጭት በየጊዜው የተለያዩ ቀጠናዊ ክስተቶች ተጽዕኖ ሲፈጥሩበት የኖረ ግጭት ነው፡፡ በተለይ የጣሊያን ወረራ፣ የሱማሊያና ጅቡቲ ነጻ ሀገር መሆን፣ ታላቋ አፋር እና ታላቋ ሱማሊያ የሚሉ ትርክቶች መፈጠር፣ የሱማሊያ መፈራረስ፣ የኤርትራ መገንጠል፣ ከ1983 ወዲህ አፋሮችና ሱማሌዎች የራሳቸው ክልል ባለቤት መሆናቸው፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ መሆኗ የሁለቱን ጎሳዎቸ ታሪካዊ ግጭትና የሃይል ሚዛን ላይ ጉልህ ለውጦችን ሲያስከተሉ ከኖሩት ክስተቶች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ ባካባቢው የተደረጉ በርካታ ጥናቶች ያሳዩናል፡፡

መንግስት የአካባቢውን ጅኦፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል በጥድፊያ የአፋር እና ኢሳ ግጭት በእርቅ እንደተፈታ ባለፉት ጥቂት ዐመታት ሲናገር ነበር፡፡ ግጭቱ ግን ከምዕተ ዐመት በላይ ከመቀጠሉም በላይ በየሀገሮቹ እነ በጠቅላላው በቀጠናው ያለው ጅኦፖለቲካዊ ሁኔታ መቀያየር ግጭቱን እያወሳሰበው ሲሄድ እንጅ ሲያቃልለው አልታየም፡፡

ኢትዮጵያ ከሱማሌላንዱ በርበራ ወደብ የባለቤትነት ድርሻ ከገዛች ወዲህ ከቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚንስትሮች ከአቶ መለሰ ዜናዊ አና ከአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስልጣን ዘመን በተሻለ በጅቡቲ ላይ አንጻራዊ የመደራደር አቅሟን አጎልብታለች ማለት ይቻላል፡፡ እናም ጅቡቲ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ቴሌኮሚኒዩኬሽን ዘርፎች የይዞታ ድርሻ እንዲኖራት የቀረበላት ሃሳብ በእጅቡ የሚያስጎመዥ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የወደብ ድርሻ ለመስጠት መስማማቷ ግን በዋናነት ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ በርበራ ወደብ ጠቅልላ እንዳታዞር ለማማለል እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በጅቡቲና ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ መሠረተ ልማት፣ ፖለቲካና ጸጥታ ትስስር እየጎለበተ ሲሄድ አፋሮች የመገለል ስሜታቸው እያደር እንደሚጠነክር መገመት አይከበድም፡፡

ላለፉት በርካታ አስርት ዐመታት ንጉሰ ነገስቱን ጨምሮ ሦስቱም የኢትዮጵያ መንግስታት በሁለቱ ጎሳዎች ግጭት ላይ በቅጥታ እጃቸውን ከማስገባት ይልቅ ግጭቱን ለሁለቱ ጎሳዎች የመተው፣ የአስታራቂነት ሚና መያዝ፣ ቀጠናዊ ይዘቱ ገፍቶ ሲመጣ ደሞ ተጻራሪ ብሄርተኝነታቸውን ውስጥ ለውስጥ ርስበርሱ የማላተም አካሄድ ነው ሲከተሉ የኖሩት፡፡ ሆኖም በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ባለፉት አመታት በተካሄዱ ጅኦፖለቲካዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች ሳቢያ ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት አፋሮችን ገሸሽ እያደረገ ወደ ኢሳዎች ያደላ መስሏል፡፡ አሁን ከጅቡቲ ጋር የሚታየው መቀራረብ በበለጠ መልክ ከያዘ ደሞ ኢሳዎች በአፋሮች ላይ ያላቸው የሃይል ሚዛን እየገነነ እንደሚሄድ ነው መጠበቅ የሚቻለው፡፡ ይሄ ሁኔታ ወደፊት በአፋሮች በፌደራሉ መንግስት፣ በአፋሮችና በጅቡቲ መንግስት ብሎም በኢትዮጵያ አፋሮች እና ኢትዮጵያ ኢሳዎች መካከል ያለውን መስተጋብር እንደምን ይቀይረው እንደሆነ ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ ላሁኑ በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ከምንጊዘው በበለጠ በጅቡቲ ወደብ ተጠቃሚነቷ ከጎለበተ ለኢሳዎች ቀን የወጣላቸው ያህል እንደሆነ ነው፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ ]

https://youtu.be/QlkCW6aH2-g