FILE

ዋዜማ –  የኢትዬጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአዲስአበባ ከተማ በጎዳና ላይ ኑሯቸው ያደረጉ ህፃናትና የጎዳና ተዳዳሪዎች በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ እንዳለ አስታወቀ።    

በመዲናዋ የተለያዩ ክብረ – በአሎች በሚደረግበት ወቅት በመንግስት ፀጥታ ሀይሎች በጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ በዘፈቀደና ሰብአዊ ክብራቸውን ባላከበረ መልኩ አፈሳ መደረጉን  ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ማረጋገጡ አስታውቋል።  

የኮሚሽኑ የክትትል ዐላማ የድርጊቱን አፈጻጸም ለማጣራትና በሕፃናቱ ላይ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እና አያያዝን ለመለየት በጎዳና ላይ ውሎ አዳራቸው ያደረጉ ሕፃናት የሚነሱበትን አሠራር እና ሂደት ከሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች እና መርሆች አንጻር ለመፈተሽ ነበር። 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ክትትሉ መነሻ ያደረገው ለኮሚሽኑ የቀረቡ አቤቱታዎችና ሰሞታዎች  ሲሆን ባደረገው ክትትልም ቁጥራቸው ከ6,000 እስከ 7,000 የሚደርሱ ህፃናት በፖሊስ እና የጸጥታ ኃይሎች ከጎዳና ላይ ታፍሰው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የተሐድሶ ማእከል ውስጥ ለተለያየ የጊዜ መጠን ተይዘው መቆየታቸውን አረጋግጧል ።  

ከነሐሴ 2014 ዓ.ም ጀምሮ  እስከ  ጥር ወር 2015 ዓ.ም ድረስ ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 14,000 ሰዎች ከጎዳና ላይ በኃይል በፖሊስ ታፍሰዋል ።

የአቃቂ ቃሊቲ የተሐድሶ ማእከልም በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ ከሚችለው አቅም በላይ ሕፃናቱን ጨምሮ እጅግ በርካታ ሰዎች በጅምላ ወደ ማእከሉ እንዲገቡ ተደርገዋል  ።

በተደረገው ክትትልም ህፃናቱ በማእከሉ ውስጥ በነበረቡት ጊዜ አስፈላጊውን የምግብ፣ አልባሳት የመሳሰሉት አቅርቦቶችን እየቀረበላቸው አልነበረም።

 የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ እንደሚሉት “ሕፃናትን ከጎዳና ላይ ማንሳት የህፃናቱ መልካም ፍቃድ የሚፈልግና  አስፈላጊ ሁኔታዎችን ሁሉ በማመቻቸት የሚተገበር እንጂ በኃይል፣ በዘፈቀደ እና በሕገ-ወጥ  መንገድ የሚፈፀም  አይደለም ”  

ሆኖም፣  የመንግስት የፀጥታ አካላት አፈሳ በሚያደርጉበት ወቅት በህፃናቱ ላይ የሀይል እርምጃ በተቀላቀለበትና በዘፈቀደ አፈሳ መካሄዱን ከኮሚሽኑ የወጣ ሰነድ መስክሯል ።

በተለይም የመስቀል ፣ ኢሬቻን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ሰብሰባ በተካሄደባቸው ወቅቶች ላይ  ህፃናቱን አንዳንዴ “የደህንነት ስጋት ናቸው” በሚልና በሌላ ጊዜ ደግሞ ” የከተማዋ ገፅታ ያበላሻሉ” ተብለው መታፈሳቸውን የህፃናቱ ሰብአዊ ክብር መጣሱን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አረጋግጫለሁ ብሏል ።

በማእከሉ በቆዩባቸው ጊዜያትም ጠዋት 12፡00 ሰዓት እና ማታ 12፡00 ሰዓት መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም መውጣት ከመፍቀድ ውጪ ሕፃናቱ ቀን ላይ በተለያዩ ክፍሎች ተዘግቶባቸው እንደሚውሉና መውጣት ስለማይፈቀድላቸው በክፍሎቻቸው ውስጥ በሚገኙ የፕላስቲክ እቃዎች ሽንት ለመሽናት እንደሚገደዱና  ለመጸዳዳት በሚሹ ጊዜም  ወደ ውጪ ለመውጣት ሲሞክሩም “ረብሻችኋል” በሚል በማዕከሉ በሚገኙ ተቆጣጣሪዎች ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል ፡፡ 

ኮሚሽኑ በማእከሉ በተገኘበት ወቅት ወደ መጡበት ክልል የሚመለሱ ናቸው በሚል ተለይተው በጠባብ ክፍሎች ውስጥ ተጨናንቀው ከተቀመጡ 240 ሕፃናት በተጨማሪም ለአካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ጋር በአንድ ላይ ተቀላቅለው እንደተያዙም አረጋግጧል ፡፡

በማእከሉ ውስጥ ሴቶች ለብቻቸው የመኝታ ክፍል ያላቸው ቢሆንም ክፍሎቹ ቁልፍ የሌላቸውና በቀላሉ የሚከፈት በር ያላቸው በመሆኑ በተለይ ከጥቃት ተጋላጭነት አኳያ በሴት ሕፃናት ላይ ከፍ ያለ ሥጋት የሚያሳድር ነው፡፡

ከማእከሉ ከወጡ በኋላም ስለሚከናወነው ቤተሰብን የማፈላለግ እና መልሶ የማገናኘት፣ ጉዲፈቻ እና አሳዳጊዎችን የመፈለግ፣ የሥራ ዕድልና የትስስር ፈጠራ ወዘተ… ጉዳዮችን  ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት እና በማሳመን ላይ በመመሥረት ብቻ የሚከናወን ተግባር ነው ።

በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሕፃናት ከፊሎቹ በልመና የሚተዳደሩ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሠማርተው በአብዛኛው አነስተኛ ገቢ በሚያስገኙ “እንደ ጫማ መጥረግ ” እና “የጎዳና ላይ ሽያጭ” በመሥራት ራሳቸውን ለማስተዳደር የሚጥሩ መሆናቸውን በክትትሉ የተገኘ መረጃ ጠቅሶ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን መጠን እና አይነት በተመለከተ የተደራጀ፣ የተሰባጠረ እና ወቅታዊ አሃዛዊ መረጃ ማግኘት ባይቻልም አንዳድ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ወደ 150,000 የሚሆኑ ሕፃናት በጎዳና እንደሚገኙ እና ወደ 60,000 የሚሆኑት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ እንደሆነ ይገመታል፡፡ [ዋዜማ]