Prof Birhanu Nega- FILE

ዋዜማ- የመምህራንን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል ይረዳል የተባለ “የመምህራን ማህበር ባንክ” ለመመስረት ዕቅድ መኖሩን ሰሞኑንን ለ3ኛ ጊዜ በጂግጂጋ በተካሄደው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አመታዊ ጉባዔ የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መናገራቸው ዋዜማ ሰምታለች፡፡

ሚንስትሩ የማህበሩን ባንክ መመስረት በተመለከተ በስብሰባው ተገኝተው ይፋ ባደረጉበት ንግግር መንግስት በሚያደርገው እገዛ ባንኩን እውን ለማድረግ ጥናቶችና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጀመራቸውንና በቀጠይ በጉዳዩ ላይ ከማህበሩ ስራ አስፈጻሚዎች ጋር ወይይት ይደረግበታል መባሉን ዋዜማ ተረድታለች፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ከ 700ሽህ በላይ አባላት ያሉት የመምህራን ማህበሩ በየጊዜው የሚያነሱትን የደመወዝ ማስተካካያና የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ለማካካስ ይረዳል በሚል እሳቤ በሁሉም ክልሎች ለመምሀራን የቤት መሰሪያ ቦታ አቅርቦት እየተመቻቸ ቢሆንም መምህራኑ በሚከፈላቸው ደመወዝ ቤት መስራት ቀርቶ የዕለት ፍላጎታቸውን ማሳካት እንደተሳናቸው እየተጠቀሰ በተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበላቸው መሆኑን ሚንስትሩ በመድረኩ አንስተዋል፡፡

ይመሰረታል የተባለው ባንክ ይህንን የመምህራኑን ችግር ለመፍታትና በቀረበላቸው የቤት መሰሪያ ቦታ ላይ ቤት እንዲገነቡ ብደር የሚቀርብና የሚደግፍ ይሆናል፡፡

መንግስት ባንኩ አንዲመሰረት እገዛ ቢያደርግም በዋነኝነት ግን በአገሪቱ ለሚገኙ መምሀራን የአከስዮን ሽያጭ በማቅረብ በባለቤትነት እንዲይዙት ይደረጋል ተብሏል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚመሰረተው ባንክ በተጨማሪ በአንዳንድ ክልሎች የሚገኙ የክልል መምህራን ማህበራት የክልል መምህራን ቁጠባ ማህበራትን ለማቋቋም ትልም እንዳላቸው ተሰምቷል፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በጂግጂጋ ከተማ ለሶስት ቀናት በተካሄደው ስብሰባ የኢትዮጵያ መምህራን እና ማህበሩን ወደ ቀደመ የሙያ ክብሩ ለመመለስ ብርቱ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ [ዋዜማ]