ዋዜማ- በቅርቡ መንግስታዊው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የሕገ መንግስት ማሻሻያ አስፈላጊነት ላይ ያቀረበው የጥናት ውጤት “ጊዜውን ያልጠበቀና ግልፅነት የጎደለው ነው” ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር አጣጣሉት። 

አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለዋዜማ እንደገለፁት ሕገ መንግስቱ የፖለቲካና የሕግ ሰነድ መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግና ከነባራዊው ሁኔታ አንፃር ጥናቱ በችኮላ መሰራት የነበረበት አይደለም ብለዋል። 

በቅርቡ በመንግስታዊው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የሕገመንግስት ማሻሻያ ያስፈልጋል የሚል መደምደሚያ ያለው ጥናት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

“ጥናቱ የሁሉንም ብሔሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ያላካተተ በመሆኑ በርከት ያሉ ጉድለቶች የተመለከትንበት የጥናት ሰነድ ነው” ሲሉ አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል።

አፈጉባኤ ተሻገር እንደሚሉት የጥናቱን ናሙና ተብለው የተወሰዱት መረጃዎች ግልፅነትና  የውክልናተአማኒነት የሚጎድላቸው ናቸው ብለዋል።

ህገ-መንግስቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች ቃልኪዳን ሰነድ እንደመሆኑ መጠን ህዝቦች በህገ – መንግስቱ ዙርያ ካላቸው ፍላጎት አንፃር “በመሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር የሚጋጭ ነው” ይላሉ አፈጉባዔው።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ከሶስት አስርት አመታት በኋላ መሻሻል ይገባዋልን? ከሆነስ ምን ምን ይሻላል በሚል ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሂልተን ሆቴል የጥናት ግኝቱን አቅርቦ ነበር።

ኢንስቲትዩቱ ግን ጥናቱ ከመላው ሀገሪቱ በተወሰደ ናሙና ላይ የተመሰረተ መሆኑን በጥናቱ መግቢያ ላይ አብራርቷል። 

ፓሊሲ ኢንስቲትዩቱ ያቀረበው ጥናት አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህገ- መንግስት “መሻሻል አለበት”  በተለይም ብሔር ነክ የሆኑ አንቀፆች ጠቅሶ የመገንጠል መብት፣ የብሔሮች የሉአላዊነት ስልጣን ባለቤትነት ፣ ብሔራዊ አርማ እና ክልሎች የሚዋቀሩበት መንገድ መሻሻል እንደሚኖርባቸው በጥናት ተደርሶበታል ሲል አስታውቆ ነበር ።

አፈጉባኤ አገኘሁ “ጥናቱ አካታችነት የጎደለውና ጥቂት ልሒቃን አነጋግረህ እንዲህ አይነት ሰነድ ማቅረብ የህገ-መንግስቱን መሠረት በውል ካለመረዳት የሚመነጭ ነው” ባይ ናቸው። [ዋዜማ]