US Secretary of States Mike Pompeo

ዋዜማ ራዲዮ- ውጥረትና ውዝግብ የበረታበትና የመጨረሻ ነው የተባለው የህዳሴው ግድብ የውሀ አያያዝና አለቃቀቅ ድርድር በሱዳን በኢትዮጵያና ግብፅ የውሀ ሚንስትሮች መካከል ረቡዕና ሐሙስ በዋሽንግተን ሲካሄድ ቆይቶ በሚቀጥሉት ሳምንታት በመሪዎች ደረጃ ስምምነት ለመፈራረም የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን ለማድረግ እቅድ በማውጣት ተበትኗል።

ዋዜማ ያገኘችው መረጃ እንዳመለከተው ከፍተኛ የአሜሪካ መንግስት ሹማምንት ባለቀ ሰዓት ተደራዳሪዎችን ለማግባባት ቢሞክሩም በግብፅ በኩል በተነሱና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ፍላጎቶች ሳቢያ ድርድሩ ወደተፈለገው ስምምነት አልደረሰም።


የአሜሪካ መንግስት ምንጮች እንደሚሉት በቀሪ ጉዳዮች ላይ አጭር የባለሙያዎች የማጠቃለያ ምክክር ተደርጎ ከዚያም በመሪዎች ደረጃ ስምምነት ለማፈራረም ዋሽንግተን ዝግጅት ታደርጋለች። ይህን እውን ለማድረግም የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፓምፒዮ በቀጣይ ቀናት የአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን በተዘጋጀ ረቂቅ ሰነድ ላይ እንደሚያነጋግሯቸው ስምተናል።


የዚህ ሳምንት ውይይት ላይ በኢትዮጵያ በኩል ድርድሩን በስምምነት ለመቋጨት ሙከራ ቢደረግም ከግብፅና ከአደራዳሪዎቹ ሲቀርቡ የነበሩት የድርድር ነጥቦች ልዩነትን የሚያሰፉ ስለነበር ስምምነት ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል።

ሶስቱ ሀገራት ሲከራከሩበት በነበረው የህግ ሰነድ ላይ ከሀያ በላይ ጉዳዮች በቅንፍ ውስጥ ተቀምጠዋል። በአሰራሩ መሰረት በቅንፍ ውስጥ የሚቀመጡ ይዘቶች ያልተስማሙባቸው ናቸው ። ከዚህ ውስጥ “የውሀ ፍሰት” የሚባለው ይገኝበታል። ሀገራቱ “ፍሰት” የሚለው ቃል ምን ማለት ነው የሚለው ላይ ግልጽነት ሳይኖር ነው ኢትዮጵያ የስምምነት ሰነዱን እንድትፈርም ጫና ሲፈጠርባት የነበረው። የውሀ ፍሰት ሲባል ግድብ ውስጥ የገባው ነው ወይስ ሌላ? በሚል ልዩነት ተከስቷል ። ግብጽ ከአሜሪካና አለም ባንክ ጋር ሆና ያሰናዳችው የውሀ አለቃቀቅ ሰነድ ግን ስለ ውሀ ፍሰት ምንነት ሳያብራራ ቀመር በማውጣት ስለማሚለቀቅ ውሀ መጠን ይገልጻል። ይህ አንዱ በቅንፍ የተቀመጠ የልዩነት ምንጭ ሆኗል።

“ድርቅ” ፣ “የተራዘመ ድርቅና” ፣ ” ረጅም ዝናብ አልባ ወቅቶች” የሚባሉት በተገቢው መንገድ አለመበየናቸውም ሌላው ጉዳይ ነው። እሮብና ሀሙስ በተደረገው ስብሰባም እነዚህ ይዘቶች ባለመጠናቀቃቸው ውጤት ሳይመዘገብበት ቀርቷል። በቴክኒክ ጉዳዮች ላይም ግልጽነት ጎድሎ ታይቷል።

የህግ ሰነዶች በዚህ ጉድለት ላይ እያሉ ኢትዮጵያ ሶስተኛ ወገን አደራዳሪ ከግብጽ ጋር ሆኖ ያዘጋጀው ሰነድ ላይ እንድትፈርም ጫና መደረጉ አለማቀፍ ህግን የጣሰ ነበር ይላሉ ስለድርድሩ በቅርበት የሚያውቁ ምንጮቻችን። ሆኖም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በኩል ድርድሩን በስምምነት የመጨረስ ፍላጎት የነበረ ቢሆንም በዋሽንግተን ሲሳተፉ ከነበሩ የህግና የቴክኒክ ጉዳይ ሙያተኞች መካከል አራት ቁልፍ ተደራዳሪዎች ቀድመው ድርድሩን አቋርጠው ወጥተዋል። እንደገና ለሙያዊ እርዳታ ቢፈለጉም የድርድር ሂደቱ ተገቢ አልነበረም ብለው በማመናቸው ፍቃደኛ አልሆኑም።

በጥቅሉ ሲታይ አሁን ላይ በህዳሴው ግድብ ላይ ምንም አይነት ስምምነት አለመደረሱ በመልካም ጎኑ የሚወሰድና በይበልጥ በሂደቶች ላይ ግልጽነት ተፈጥሮ ብሄራዊ ጥቅምን ለማስከበር እድልን የሰጠ ነው።

የውሀና መስኖ ሚንስትሩ ስለሺ በቀለ (ኢ/ር) ከድርድሩ በኋላ እንደተናገሩት በድርድሩ ይዘትና ባጋጠሙ መሰናክሎች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች ጋር በቅርቡ ምክክር ይደረጋል። ይህም ምክረ ሀሳብ ለማሰባሰብ ያለመ ነው።

አንድ የድርድሩ ተሳታፊ እንደሚሉት ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ፈተና ገጥሟት አያውቅም። የዚህ ድርድር ውጤት የአሜሪካና የኢትዮጵያን ግንኙነት ሊያናጋ የሚችል ነው።

“አሁን የምንደራደረው ግብፅን ለማሳመን ሳይሆን አሜሪካንን ላለማስከፋት ነው” ባለሙያው ያሰምሩበታል።