የዋዜማ ራዲዮ- የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ሁለተኛ ምዕራፍ የውሃ ሙሌት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል የሲሚንቶና ሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶችን በወቅቱ ለማድረስ ብርቱ የትራንስፖርት ችግር መከሰቱን ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

የትራንስፖርት አገልግሎቱን ስድስት የከባድ ደረቅ ጭነት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከጣሊያኑ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ሳሊኒ ጋር ውል በማሰር ይሰጡ የነበረ ሲሆን በአገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ እና እና በሌሎችም ምክንያች የሲሚንቶና ሌሎች የግንባታ ግብዓቶች አቅርቦት የተፈለገውን ያህል አልነበረም።

ይህን ተከትሎ የፌደራል የትራንስፖርት ባለስልጣን የትራንስፖርት ማኅበራት እና ድርጅቶች ኮታ ተሰጥቷቸው ከሳሊኒ ጋር ውል በማሰር እንዲያስሩ ምከረ ሃሳብ አቅርቦ ነበር ፤ የሚፈለገውን ለውጥ አላመጣም።

ከዚህ ተደጋጋሚ ጥረት በኋላ የትራንስፖርት ባለስልጣን ቀጣዩ የመፍትሔ ሃሳብ የነበረው ለትራንስፖርት ድርጅቶችና ማኅበራት ጥሪ ማድረግ ነበር፡፡ ይህም በሚፈልገው መጠን ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን ዋዜማ አረጋግጣለች፡፡

በኋላም መንግስት የትራንስፖርት ማኅበራት እና ድርጅቶችን ከመብራት ኃይል ጋር ውል አስረው በአስገዳጅ ሁኔታ የሚሰሩበት አሰራርን አውጥቷል፡፡

የፌደራል ትራንሰፖርት ባለስልጣን ያወጣው አስገዳጅ አሰራር የትራንስፖርት ድርጅቶችና ሾፌሮች በሳምንት የተሰጣቸውን ኮታ ሳያጠናቅቁ ወደ ጅቡቲ እንዳይንቀሳቀሱ የሚያግድ ነው፡፡

ነገር ግን ባለስልጣኑ ያወጣውን መመሪያ ጉድለቶች የነበሩትና ለሙስና በር የከፈተ ስለነበር ሁነኛ መፍትሔ መሆን አልቻለም፡፡

አሽከርካሪዎቹ ስራውን ላለመስራት ከሚያቀርቧቸው ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ እና በተለያዩ ጊዜያት እየተደጋገመ የመጣው የሾፌሮች ግድያ ይጠቀሳል፡፡
እንደመጨረሻ አማራጭ የትራንስፖርት አስሪዎች ፌድሬሽን በከባድ ደረቅ ጭነት ሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ባለንብረቶችን ኃላፊነታቸውን እና ግዴታቸውን እንዲወጡ በዚህ ሳምንት በይፋ ጥሪ ሊቀርብላቸው እንደሆነም ለዋዜማ የደረሰው ማስረጃ ያሳያል፡፡

የሕዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በሐምሌ ወር ለማካሄድ ዕቅድ አለ። [ዋዜማ ራዲዮ]