Merkatoየማሻሻያ ረቂቅ ደንቡ

  • የግለሰብ ይዞታ ጋር ተቀላቅለው የሚገኙ ደቃቃ የቀበሌ ቤቶች ግለሰቦች እንዲያለሟቸው ይፈቅዳል፡፡
  • ልዩ አገራዊ ፋይዳ ይዘው ለሚቀርቡ የላቁ ባለሐብቶች መሬት ከሊዝ ደንብ ዉጭ በምደባ ይሰጣል፡፡
  • ነባር ይዞታዎችን ወደ ሊዝ ሥርዓት ለማስገባት ተጨማሪ 2 ዓመት ጊዜን ይፈቅዳል፡፡
  • በሕገወጥ ወረራ የተያዙ ቦታዎች በ2 ዓመት ዉስጥ ወደ ሊዝ ሥርዓት እንዲገቡ ያስገድዳል፡፡
  • በከተሞች ለማኑፋክቸሪንግ  በተናጥል ቦታ የሚጠይቁ ባለሐብቶች እንዳይስተናገዱ ያግዳል፡፡
  • በከተሞች አንድ ግለሰብ ከአንድ በላይ የመኖርያ ቤት በሊዝ እንዳይጫረት ገደብ ይጥላል ተብሏል፡፡

ዋዜማ ራዲዮ- በ2004 ዓ.ም በብዙ ዉዝግቦች ታጅቦ ጸድቆ የነበረው የሊዝ አዋጅ 721/2004 በርካታ ክፍተቶች እንዳሉበት በመገለጹ ከአምስት ዓመት በኋላ በቅርቡ ሊሻሻል እንደሚችል የዋዜማ ምንጮች ጠቆሙ፡፡

በአዲስ አበባ መስተዳደር የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በከፍተኛ ኃላፊነት የሚሠሩና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ በተቋቋመው የሊዝ ኦዲት ኮሚቴ ዉስጥ በአባልነት የሠሩ ባለሞያ ለዋዜማ እንደተናገሩት አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገው ለትርጉም ክፍት የኾኑ አንቀጾችን በመያዙ፣ አሁን ካለው ፈጣን የልማት ጥያቄ ጋር ባለመጣጣሙና ለአገር ከፍ ያለ ፋይዳ ያላቸው አልሚዎችን ለማስተናገድ አዋጁ ማነቆ ኾኖ በመቆየቱ ነው፡፡

ኃላፊው ጨምረው እንዳብራሩት ከሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ፈጻሚዎች ጋር በአዋጁ ማሻሻያ ላይ ሰፊ የዉይይትና የምክክር መድረክ ይከፈታል፡፡ በዉይይቱም በአገር ደረጃ መሬት ልማት ላይ የሚሠሩ ከፍተኛና መካከለኛ ኃላፊዎች ይገኛሉ፡፡ ይህም የሚደረገው አዋጁን ሲያስፈጽሙ በነበሩ አመራሮች  ዘንድ ተመሳሳይ ግንዛቤን ለመፍጠርና የአዋጁን ክፍተቶች በዉይይት ለማዳበር ታስቦ ነው ብለዋል፡፡

ከተሞች ከ2004 ቀደም ባሉት ጊዜያት መሬት የሚያስተላልፉበት ወጥ አሠራር አለመኖሩ መሬት ማግኘት በግለሰቦች በጎ ፍቃድ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከአዋጁ በኋላ ሁሉም ዓይነት የመሬት ስሪቶች በሂደት ወደ ሊዝ እንዲገቡ በማድረግና የመሬት አቅርቦትን በግልጽ ጨረታ ለአልሚዎች ለማስተላለፍ ተሞክሯል፡፡ በአንጻሩ የሊዝ አዋጁ ሁነኛ ግብና መነሻ በአነስተኛ ዋጋ ዜጎች ቦታ እንዲያገኙ ማድረግን ያለመ ነው ቢባልም በዉጤቱ መሬት የጥቂት ባለፀጎች የግል ንብረት ኾኖ እንዲቆይ አድርጓል ይላሉ ተቺዎች፡፡

የሊዝ አዋጁን ተከትሎ ባለፉት አምስት ዓመታት ከተሞችና ክልሎች የራሳቸውን የማስፈጸሚያ መመሪያና በማውጣት ሊተገብሩት ሲሞክሩ ቆይተዋል ያሉት የኦዲት ኮሚቴው አባል ኾኖም ከተሞች አዋጁን ለማስፈጸም የሄዱበት መንገድ ለዉዝግብና ለአሠራር ክፍተት የተመቸ ነበር ብለዋል፡፡

አዋጅ 721/2004 በመባል የሚጠራው የሊዝ አዋጅ አፈጻጸም የእስከዛሬ ሂደት መንግሥት በከፍተኛ ባለሞያዎች ኦዲት እንዲደረግ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ኮሚቴ ተዋቅሮ በመጠናት ሂደት ላይ ነበር፡፡ ኮሚቴው ባካሄደው ተከታታይ የሊዝ ኦዲትና ምዘና በአሠራር ላይ ከፍተኛ ክፍተት ተገኝቶበታል፡፡ አንዳንድ ከተሞች አዋጁን ገሸሽ አድርገው በራሳቸው መንገድ መሬት ሲያድሉ ነበር ያለው የኮሚቴው ሪፖርት ሌሎች ክልሎች ደግሞ አዋጁን በሚመቻው መንገድ ሲተረጉሙት እንደነበር ተደርሶበታል ብሏል፡፡

እንደ ምሳሌም ለአገር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች በሊዝ ደንብ ብቻ ለማስተናገድ ምቹ ሳይሆን በሚቀርበት ሁኔታ የክልል ካቢኔዎች፣ የከተማ ከንቲባዎችና የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች አዋጁን በሚጻረር ሁኔታ ለፈቀዱት ባለሐብት ሰፋፊ መሬቶችን ሲሰጡ ነበር ተብሏል፡፡ ይህም “ለልማት ልዩ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች” ናቸው በሚል ሽፋን ሲፈጸም የቆየ ተግባር ነው፡፡

የአዋጁ ሌላው ክፍተት ኾኖ የተመለከተው ከሊዝ የወለድ ስሌት ጋር የተያያዘ እንደነበርም ተመልክቷል፡፡ ሁሉም ክልሎች በሊዝ የተላለፈ መሬት የንግድ ባንክ የወለድ ተመንን ተከትለው በየዓመቱ ስሌቱን የሚሠሩ ሲሆን የአዲስ አበባ መስተዳደር ግን ከሌሎች ከተሞች በተለየ አልሚዎችን ድርብ ወለድ (compound Interest) እንዲከፍሉ በማስገደድ ባለሐብቱ ላይ ተገቢ ያልሆነ እዳን በመቆለል ከልማት በኋላ ሊገኝ የሚችልን የግብርና የሥራ ገቢን በወለድ መልክ በአቋራጭ ለመሰብሰብ ሞክሯል ተብሏል በሪፖርቱ፡፡ ይህም አልሚዎች በግንባታ ፍጻሜ ላይ እንዳያተኩሩ አድርጓል፡፡

ወለድ ባልተኖረበት የሊዝ ዓመትና ባልተሠራበት የሊዝ ዘመን ወደፊት ተኪዶ ሊሰላ አይችልም ያሉት የኮሚቴው አባል እስከዛሬ በመስተዳደሩ ይሠራበት የነበረው አሠራር ሕግን ያልተከተለ እንደነበር በመርህ ደረጃ መተማመን ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡ የሚሻሻለው የሊዝ አዋጅ ይህን ክፍተት በመሸፈን ሁሉም ክልሎች ወጥነት ባለው መንገድ ዓመታዊ የሊዝ ገቢን እንዲሰበስቡ የሚያስችል አሠራርን ይዘረጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የሊዝ አዋጁ አመጣቸው ከሚባሉ በጎ ዉጤቶች መካከል የመሬት ብክነትን መከላከል፣ የመሬት ወረራ እንዲቀንስ ማድረግ፣ አልሚዎች በጊዜ ገደቡ ምክንያት ልማታቸውን በግዴታ እንዲያጠናቅቁ አስገዳጅ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ እንዲሁም በዋናነት መሬት በግለሰቦች መልካም ፍቃድ የሚሰጥበትና የሚከለከልበትን እድል መቀነስ ዋናዎቹ ናቸው ተብሎ በኮሚቴው መገምገሙን የኦዲት ኮሚቴው አባል ያስረዳሉ፡፡

በተጨማሪም በሊዝ የሚተላለፉ መሬቶች ከማንኛውም የይገባኛል ጥያቄ ነጻ መሆናቸው፣ ከሞላ ጎደል የከተማ ፕላን ተከትለው መዘጋጀታቸው፣ አንጻራዊ የመሠረተ ልማት ምቹነት ያላቸው ስፍራዎች ላይ መወሰናቸው፣ እንዲሁም ልዩ የሽንሻኖ ኮድ ሳይት ፕላን የተዘጋጀላቸው ስለነበሩ ለአሠራር አመቺ ሆነው መገኘታቸው ተወስቷል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም ከተሞች በዚህ ሁኔታ የተዘጋጁ መሬቶችን ሲያቀርቡ ነበር ማለት እንዳልሆነ የኦዲት ኮሚቴው አባል ያስረዳሉ፡፡ ለአብነትም ቦታዎች በሊዝ ለባለሀብቶች ከተላለፉ በኋላ የመንገድና የአጎራባች ይገባኛል ጥያቄ በብዙ ከተሞች ላይ ይነሳ እንደነበር አልሸሸጉም፡፡

በሊዝ የሚተላለፍ መሬት ሲካሄድ የተጫራቾች ቁጥር በተመለከተ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ምክንያቱ በማይታወቅ የአሠራር መመሪያ አንድ ተጫራች በአንድ ዙር ከአንድ በላይ የጨረታ ሰነድ ገዝቶ መጫረት እንዳይችል የሚያግድ አሠራር እንደነበረም ኮሚቴው በኦዲት ሪፖርቱ እንደደረሰበት ተገልጧል፡፡ ይህ አሠራር በሌሎች ከተሞች የማይታወቅ ነው፡፡ ይልቁንም ግለሰቦች ያሻቸውን የጨረታ ሰነድ ገዝተው ባሻቸው መጠን መወዳደር የሚችሉበት እድል አላቸው፡፡

በሚሻሻለው የሊዝ አዋጅ ለጨረታ የቀረበው ቦታ ለመኖርያ ቤት ከኾነ ብቻ አንድ ተጫራች ከአንድ ቦታ በላይ እንዳይጫረት፣ የመኖርያ ቤት አንድ ጊዜ በሊዝ ያሸነፉ ግለሰቦች ከዚያ በኋላ ሌላ የመኖርያ ቤት ጨረታ ላይ እንዳይሳተፉ እንደሚደረግ ሐሳብ መቅረቡን የሊዝ ኦዲት ኮሚቴ አባሉ አስረድተዋል፡፡ 

ይህ እንዲሆን የተፈለገው መሬት በሊዝ በመግዛትና አትርፎ በመሸጥ ሥራ ላይ የተሠማሩ የመሬት ደላሎችን ለማግለልና በከተሞች ፍትሐዊ የመሬት ክፍፍል እንዲኖር ለማስቻል ነው ተብሏል፡፡ከ13 እስከ 18 የሚኾኑ ቁልፍ ቦታዎችን በሊዝ አሸንፈው የያዙ ግለሰቦች በኦዲት ሂደት እንደተገኙ የጠቆሙት የኮሚቴ አባሉ ይህ ዉድ ሀብት የኾነን የሕዝብና የመንግሥት መሬት በአቋራጭ የጥቂቶች እየኾነ እንደመጣ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል ተብሏል፡፡ ኾኖም ለቅይጥና ለቢዝነስ የሚወጡ ቦታዎች ባለሐብቶች እንደፈቃዳቸው መጫረት እንዲችሉ እንደሚደረግ አልሸሸጉም፡፡

የሊዝ አዋጁ የሊዝ መነሻ ዋጋን በተመለከተ በየሁለት ዓመቱ ሁኔታዎች ተገናዝበው መከለስ እንዳለበት ቢደነግግም በብዙዎቹ ከተሞች ይህ እንዳልተፈጸመ ግንዛቤ ተይዟል ይላሉ ባለሞያው፡፡ ለምሳሌ በሐረር ከተማ የሊዝ መነሻ ዋጋ የሚወሰነው ጨረታው ሊጀመር ሲል የወቅቱን አማካይ ዋጋ በመውሰድ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ አዲስ አበባ ትንሹ የሊዝ መነሻ ዋጋ 191 ብር ኾኖ ዘለግ ላለ ጊዜ መቆየቱንና ይህም የጊዜውን የመሬት ዋጋ የሚወክል እንዳልሆነ ተመልክቷል፡፡ የሊዝ መነሻ ዋጋ ማስተካከያ ሲደረግ በካቢኔ መጽደቅ እንዳለበት አዋጁ ቢደነግግም አንዳንድ ከተሞች በከንቲባቸው በጎ ፍቃድ ወይም በበታች የመሬት ኃላፊዎች ፍላጎት ብቻ ዋጋ ሲወስኑ እንደነበረ የኦዲት ኮሚቴው ደርሶበታል ተብሏል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 8 ንኡስ አንቀጽ 7 እና 8 በተደነገገው መሠረት በልዩ ጨረታ ሊስተናገዱ የሚገባቸውን እንደ ሪልስቴት፣ ትምህርት ቤትና ከባለ 4 ኮከብ ሆቴል በላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ለባለሀብቶች ለማስተላለፍ የተሞከረበት ሂደት ደካማ እንደነበር ተረጋግጧል፡፡ ለአንዳንድ ባለሀብቶች እነዚህ ቦታዎች በድርድርና አንዳንዴም በሹሞች ፈቃድ ሲተላለፍ እንደነበረና ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲከለከል እንደነበር፣ በአጠቃላይ ወጥነት የጎደለው አሰራር እንደተንሰራፋ ኮሚቴው በሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

“ልዩ ሊዝ ጨረታ” ተብለው የሚወጡ የከተማ ቦታዎች ለምን አገልግሎት እንደሚውሉ መሬት አቅራቢው አስቀድሞ ወስኖ የሚያስተላለፋቸው ልዩ ቦታዎች ሲኾኑ ከሌሎች የሊዝ ጨረታዎች በተለየ አንድ ተጫራች ብቻውን ቢቀርብ እንኳ ባቀረበው ዋጋ ቦታዎቹን መውሰድ ይችላል፡፡ ኾኖም በልዩ ጨረታ ለትምህርት ቤት የተወሰዱ ቦታዎች ለአልሚዎች ከተላለፉ በኋላ ላልተፈቀዱ አገልግሎቶች ሲዉሉ እንደተገኘም የሊዝ ኦዲት ሪፖርቱ ላይ ተገልጧል፡፡ በአዲስ አበባ ለትምህርት ቤት በሚል የተወሰዱ አብዛኛዎቹ ቦታዎች ተሸንሽው ለሱቅ አገልግሎት ዉለው  እንደተገኙ የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

በተለይም የአዋጁ አንቀጽ 12 ንኡስ አንቀጽ 1 (ሰ) የተቀመጠው መመሪያ ሁሉም ከተሞች በተመቻቸው መንገድና ሁኔታ እየተረጎሙ ሰፊ የሙስና በር ኾኖ ይታሰብ እንደነበር አጥኚው ኮሚቴ ደርሶበታል፡፡  ይህ አንቀጽ “ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ብቻ” መሬት በምደባ እንደሚተላለፉ ይደነግጋል፡፡ ኾኖም “ልዩ አገራዊ ፋይዳ” ማለት በግልጽ ትርጉሙ ምን አይነት ፕሮጀክቶችን ያካትታል የሚለው በግለጽ አልተቀመጠም፡፡ ይህ ሁኔታ ለከፍተኛ የመሬት ምዝበራ አጋልጧል ተብሏል፡፡ በተለይም በሐረርና ድሬዳዋ የመሬት ባለሞያዎች ለፈቀዱት ባለሐብት ሊዝ ጨረታ እንዲሳተፍ ከማድረግ ይልቅ “ፕሮጀክቱ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያለው ነው” በሚል ሽፋን መሬት ያለአግባብ በስፋት ሲያድሉ እንደነበር የኦዲት ኮሚቴው በሪፖርቱ አብራርቷል፡፡

ሌላው የሊዝ አዋጁ ክፍተት ተብሎ የተጠቀሰው አልሚዎች የሚያጎራብቷቸው መሬቶች ለማስፋፊያ የሚጠይቁበት መንገድ በግልጽ አለማስቀመጡ ነው፡፡ አልሚዎች ባዶ መሬት ከጎናቸው ሲያገኙ ለፕሮጀክታቸው ማስፋፊያ በሚል ወደራሳቸው እንደሚጠቀልሉትና ይህም በብዙዎቹ የመሬት ባለሞያዎች እንደ መልካም ክፍተት እየታየ ሁነኛ የኪራይ ሰብሳቢነት መንገድ ኾኖ አገልግሏል ተብሏል፡፡ “የማስፋፊያ ፕሮጀክት ጽፈንላችሁ የምትጎራበታችሁን ባዶ መሬት በሊዝ ዋጋ እናሰጣችኋለን” በማለት የመሬት ባለሞያዎች ባለሐብቶችን ያግባቡ እንደነበረ ተደርሶበታልም ተብሏል፡፡

የንግድ ቦታዎችን በተመለከተም የኦዲት ኮሚቴው የአዋጁ ክፍተቶች ነበሩ በሚል በርካታ ነጥቦችን አንስቷል በሪፖርቱ፡፡

በአዲስ አበባ የገበያ ቦታዎች በልማት ምክንያት ሲፈርሱ የፈረሱት የንግድ ቤቶች የመንግሥት ከነበሩ ለፈረሰባቸው ነጋዴዎች 25 ካሬ መሬት በነፍስ ወከፍ በሊዝ መነሻ ዋጋ እንዲወስዱ መመሪያው ቢያዝም እስካሁን የነበረው አሰራር ግን ነጋዴዎች መሬቱን በዉድ ብናቀርብላቸው እንኳ የሚከፍሉት የብር መጠን ትንሽ ነው በሚል እሳቤ በአካባቢው የጨረታ ግምት እየተሰላ ከፍ ያለ ዋጋ እንዲከፍሉ ይገደዱ እንደነበር ተብራርቷል፡፡ መርካቶና አካባቢዋ ቀደም ያሉ የኪራይና የቀበሌ ቤቶች በዚህ አግባብ ሲስተናገድ እንደነበር ሪፖርቱ ያብራራል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 22 እና 23 ሥር ግንባታ ስለመጀመርና ስለማጠናቀቅ የሚደነግጉ አንቀጾች ላይ ሰፊ ማሻሻያ በአዲሱ አዋጅ ላይ እንደሚጠበቅ ተብራርቷል፡፡ ሁሉም ከተሞች በሊዝ ጨረታ እና በምደባ የተላለፉ ይዞታዎች ላይ ክትትል እንዲያደርጉ የሚጠበቅ ቢኾንም አልሚዎች በገቡት ዉል መሠረት እየሄዱ ስለመሆኑ ማንም የሚከታተላቸው አልነበረም ተብሏል፡፡ ወደ ልማት ባልገቡት ላይ የሚወሰድ እርምጃ በወጥነት እና በተከታታይነት ያካሄደ ክልል አልተገኘም ይላል ሪፖርቱ፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 20 ንኡስ አንቀጽ 5 እና 6 መሰረት ዓመታዊ የሊዝ ክፍያን በተመለከተ አብዛኛዎቹ ከተሞች በባለቤትነት ስሜት ክትትል እንደማያደርጉ፣ በማይከፍሉት ላይም ተከታትሎ እርምጃ እንደማይወስዱ በሊዝ ኦዲት ኮሚቴው ዘንድ ተደርሶበታል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ማንኛውም የሊዝ ባለይዞታ መብቱን ለማስተላለፍ ወይም በከፈለው የሊዝ ክፍያ መጠን በዋስትና ለማስያዝ፣ እንዲሁም በካፒታል አስተዋጽኦነት መጠቀም ይችላል በሚል የተደነገገ ቢኖርም ከተሞች ለሊዝ ባለመብቶች ጊዜያዊ የባለቤትን ማረጋገጫ ካርታ ብቻ ስለሚሰጡና ቋሚ ካርታ ለማግኘት ግንባታው የግድ ከ50 በመቶ በላይ መሆን አለበት ስለሚባል አሰራሩ አልሚዎችን ለችግር ዳርጎ ቆይቷል፡፡ ባንኮች በበኩላቸው ያለ ቋሚ ካርታ በዋስትና መያዝ ባለመቻላቸው የሊዝ ባለይዞታዎች የሊዝ መብታቸውን መጠቀም እንዳይችሉ ተደርጎ ቆይቷል፣ ይህም በአዲሱ አዋጅ ይሻሻላል ተብሏል፡፡

ወደሊዝ ስሪት የሚገቡ ይዞታዎችን በተመለከተ ተፈጻሚ የሚሆነው የሊዝ ክፍያ መጠን በአካባቢው የሊዝ መነሻ ዋጋ መሠረት እንደሚሆን የሚደነገግገው የአዋጁ ክፍል ሐረርን በመሰሉ ከተሞች ሙሉ በሙሉ እንደሚጣስና ከዚያ ይልቅ ከነባር ወደ ሊዝ የሚገቡ ይዞታዎች ዋጋ የሚወሰነው በአመታዊ የቦታ ኪራይ ተመን እንደነበር ተደርሶበታል ተብሏል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2 የከተማ ቦታ በሊዝ የሚፈቀደው በጨረታ ወይም በምደባ ስልት ብቻ እንደሆነ መደንገጉ በሊዝ አግባብ ቦታ ወስደው ወይም በነባር ይዞታዎቻቸው ላይ የላቀ ልማት ለማካሄድ የማስፋፊያ ጥያቄ ለሚያቀርቡ ባለሀብቶች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ድንጋጌ በሊዝ አዋጁ በግልጽ አለመቀመጡና ይህም ክፍተት ፈጥሮ መቆየቱ ተወስቷል፡፡ በመኾኑም በአዲሱ አዋጅ ላቅ ያሉ አልሚዎች የሚስተናገዱበት አዲስ አሠራር ይዘረጋል ተብሏል፡፡

ራሳቸውን ችለው የማይለሙ ክፍት ቦታዎች (Negative plots) ከዚህ ቀደም ለምን አገልግሎት እንደሚውሉ ግልጽ መመሪያ ባለመኖሩ እንዲሁ ቆመው ይቀሩ እንደነበርና በአዲሱ አዋጅ ግን ቦታዎቹ ከከተማ ፕላን ጋር እየተናበቡ ለአካባቢው አልሚዎች በሊዝ ገበያ ዋጋ የሚካተቱበት እድል እንደሚፈጠር ተመልክቷል፡፡

በአዲሱ ማሻሻያ ከተካተቱና ሰፊ ዉዝግብ ይፈጥራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ዉሳኔዎች አንዱ በከተሞች ከአንድ ቦታ በላይ ለመኖርያ በጨረታ አሸንፎ መያዝ እንደማይቻል ገደብ መቀመጡ ነው፡፡ ግለሰቦች በሊዝ አሸንፈው የገነቡት መኖርያ ቤት በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ሳይፈልጉት ቀርተው ሌላ ሰፊ መሬት በሊዝ አሸንፎ ለመግዛት ቢፈልጉ መብታቸው መገደቡ ምን ያህል ያስኬዳል የሚለው ጥያቄ ፈጥሯል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ  4 በአምስት አመት ጊዜ ዉስጥ ሁሉም ከተሞች ወደ ሊዝ መግባት አለባቸው ተብሎ የተደነገገ ቢኾንም ይህ ባለመሳካቱ በአዲስ አዋጅ ይህ ገደብ በ2 ዓመት እንዲራዘም ይደረጋልም ተብሏል፡፡

ያለፈቃድ የተያዙ ቦታዎች በአራት ዓመት ጊዜ ዉስጥ ስርአት ይዘው ይጠናቀቃሉ ተብሎ የተደነገገውም በ2 አመት ተጫመሪ ጊዜ እንደሚሰጠው ተመልክቷል፡፡ አዲስ አበባ ዉስጥ ከ19988 እስከ 1997 ያለፈቃድ በወረራ የተያዙ ቦታዎች በ2006 በጀት አመት ደንብኛ መመሪያ ወጥቶ የነበረ ሲኾን 45ሺ ሕገወጥ ቤቶች ተገኝተው ለ25ሺው ካርታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከ1997 ወዲህ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ቦታዎች እጣ ፈንታ ግን በካቢኔው ወደፊት የሚወሰን ይኾናል ተብሏል፡፡

የቀበሌና የኪራይ ቤቶች ከግል ቤቶች ጋር በአንድ ግቢ ተዳብለው በሚገኙባቸው የከተማ ሰፈሮች ቦታዎቹ እስከዛሬ በንጽጽር ካርታ የሚተዳደሩ የነበረ ሲኾን በአዲሱ አዋጅ ግን ይዞታዎች በምደባ ወደ ግለሰቡ እንዲካተቱ የሚያስችል አንቀጽ  ይካተታል ተብሏል፡፡

ሌላው በአዲሱ አዋጅ ትኩረት የሚሰጠው ለማኑፋክቸሪንግ ተብለው በሚሰጡ የከተማ ቦታዎች ሲኾን ግለሰቦች በተናጥል ለማኑፋክቸሪንግ የቦታ ጥያቄን በከተሞች ሲያቀርቡ ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀ የኢንደስትሪ ዞን ዉስጥ እንዲገቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ይህም የከተማ ቦታዎች ዉስን ከመሆናቸው ጋር ለእያንዳንዱ ተበጣጥሶ ለሚገነባ ኢንዱስትሪና ፋብሪካ የተናጥል መሠረተ ልማት መገንባት ለመንግሥት ፈታኝ ስለሚሆን ነው ተብሏል፡፡ አሁን በመሐል ከተማ የሚገኙ ሰፋፊ ፋብሪካዎችም ይዞታቸውን ለቀው መንግሥት በሚያዘጋጃቸው የፋብሪካ ዞኖች እንዲሸጋገሩ ልዩ ማበረታቻ ይደረጋልም ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የከተማ ደረጃን ባገኙ 1600 በሚኾኑ የአገሪቱ ከተሞች 721/2004 በመባል የሚጠራው የሊዝ አዋጅ ብቸኛ የመሬት መተዳደሪያ ኾኖ ቆይቷል፡፡ ይህ አዋጅ በዉይይት ዳብሮ በዚህ ዓመት መጨረሻ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡