ዋዜማ- በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዘቦች ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች ማለትም ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ የሚሳተፉበት እና ራሱን የቻለ አንድ ክልል ለማቋቋም የሚወሰኑበት የህዝበ ውሳኔ ምርጫ ዛሬ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ. ማለዳ ይጀምራል::

ባለፉት አራት ዓመታት ከ56 በላይ ብሔረሰቦችን በውስጡ የያዘው የደቡብ ክልል፣ የክልልነትና የዞን አደረጃጀት ጥያቄ እየበረታ መጥቶ ከዋናው ክልል ተገንጥለው የወጡት ክልሎች ሁለት የደረሱ ሲሆን ዛሬ የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ደግሞ የሶስተኛውን የክልልነት እጣ ፋንታ የሚወስን ይሆናል፡፡

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሲዳማን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ህዳር 2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም የህዝብ ውሳኔ ምርጫ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ በዚህ የሕዝበ ውሣኔ ምርጫ የሲዳማን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ለመወሰን ለመራጭነት ተመዝግቦ ድምጽ ከሰጠው አጠቃላይ 2,279,022 መራጭ ውስጥ  1,984,283 ወይንም 97.7 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የሲዳማን በክልልነት መደራጀት መርጦ ሲዳማ የመጀመሪያው ራሱን ችሎ ክልል ሆኖ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ከ 2 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላቸው የከፋ ፣ ሸካ፣ ቤንች-ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እና ኮንታ ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ክልል የመሆን ጥያቄያቸውን ለምርጫ ቦርድ አቅርበው መስከረም 20፤ 2014 ዓ.ም በተካሄደ የህዝበ ውሳኔ ምርጫ ድምጽ ከሰጡ አጠቃላይ 1.245.116 መራጮች ውስጥ 1.221.092 የሚሆኑት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት እራሱን ችሎ እንዲቋቋም በሰጡት አብለጫ ድምጽ ክልሉን መስረተዋል፡፡

አሁንም በቀጠለው የክልል እንሁን ጥያቄ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የተካተተው የጉራጌ ሕዝብ እራሱን በቻለ ክልል እንዲዋቀር በተከታታይ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

የዞኑ ነዋሪዎች የጉራጌ ዞን ከስልጤ፣ ከየም ልዩ ወረዳ፣ከከንባታ ጠንባሮ እና ሀድያ ዞኖች ጋር በመሆን በክላስተር እንዲደራጂ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ተከትሎ በነሃሴ 2014 ዓ፣ም ለበርካታ ቀናት የስራ ማቆም አድማ አድርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በመጨረሻም የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የ’ክላስተር’ ክልል አደረጃጀትን ውድቅ አድርጎ ከነባሩ የደቡብ ክልል ጋር አብሮ ቀጥሏል፡፡

ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎችን አጠቃሎ ክልል ለመመስረት ዋዜማ ላይ የሚገኙት የኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ ዞኖችና የ ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ አምስት ልዩ ወረዳዎች የህዝበ ውሳኔ ምርጫ ዛሬ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን የህዘብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉበዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ድምጻቸውን በአርባ ምንጭ ከተማ የሚሰጡ ይሆናል፡፡

በዚህ የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ በ3769 ምርጫ ጣቢያዎች በተካሄደ የመራጮች ምዝገባ በአጠቃላይ 3,028,770 የመራጮች ቁጥር መመዝገባቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡ 

ቦርዱ በ31 ማዕከላት ሥር ባሉ 3771 ምርጫ ጣቢያዎች ለሕዝበ ዉሣኔው ድምፅ መስጫ ቀን የሚያገለግሉ የተለያዩ ሠነዶችና ቁሳቁሶችን ስርጭት ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፤ ከምርጫ ጣቢያዎቹ መካካከል የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ብርብርና ቁጫ በተባሉ ቦታዎች ላይ የተከፈቱ የተፈናቃይ ጣቢያዎች ስለመኖራቸው ተገልጿል፡፡

ቦርዱ ዜጎች ዕለቱን ለድምፅ መስጫ እንዲጠቀሙ በሚል በተጠቀሱት ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ የመንግስት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ እና የግል ተቋማት ጥር 29 ቀን 2015 ዓ. ም. ስራ ዝግ እንዲያደርጉ ያሳሰበ ሲሆን፤ የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ የዕለት ተዕለት አገልግሎት ሰጪዎች በተለይም ሆቴሎች፣ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፓርት አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

የዋዜማ ሪፖርተር በምርጫው ዋዜማ በአርባ ምንጭና ወላይታ ሶዶ አካባቢ ተንቀሳቅሳ ያለውን የምርጫ ድባብ እንደተመለከተችው በከተሞች ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ ከተለመዱት ቀናት ባልተለየ መልኩ ዜጎች ስራቸውን እየከወኑ መሆኑን መታዘብ ተችሏል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች እምበዛም የክልል ምስረት ምርጫ ዋዜማ በማይመሰል መልኩ ህይወት እንደተለመደው የቀጠለ ሲሆን እሁድ አመሻሹ ተዘዋውረን ካነገርናቸው ዜጎች ግራ የተጋቡ አይነት መልሶች ተደምጠዋል፡፡ 

በዚህ የህዝብ ውሳኔ አሰጣጥ ከሚሳተፉ ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ ውጤቱ በእያንዳንዳቸው ዞኖችና ወረዳዎች በሚመጣው ውጤት የሚወሰን ሲሆን በአንድ ዞን ውስጥ የሚመመዘገበው ውጤት በአጠቃላይ የምርጨው ውጤት ድምር ተጽእኖ የማይወደቅ መሆኑን የገለጹት  የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ የአንድ ዞን ወይንም ልዩ የወረዳ በክልልነት እንደራጂ ወይንም ባለንበት እንቀጥል የሚለው የምርጫ ውጤት መበላለጥ በቀጣይ ወደ አዲሱ ክልል የመጠቃለል ወይንም አሁን ባለበት የደቡብ ክልል እንዲቀጥል የሚወሰን ይሆናል፡፡

ዛሬ በሚከሄደው የህዝበ ውሳኔ የክልል እንሁን የሚለው ድምጽ አሸናፊ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የፌደራል መንግሥቱ አባላ የሆኑትን ክልሎች ብዛት ወደ 12 ከፍ ያደርጋቸዋል። [ዋዜማ]