• መንግስት ግማሽ ሚሊየን ዜጎችን በዚህ ዓመት ወደ ውጪ ሀገር ለመላክ እየሰራሁ ነው ብሏል

ዋዜማ- የሥራና ክህሎት ሚንስቴር በዘንድሮው ዓመት እስካሁን ባሉት ጊዜያት ከ261 ሺሕ በላይ ሥራ ፈላጊዎች መንግሥት የሥራ ስምሪት ውል ወደተዋዋለባቸው አገራት መላካቸውን ለዋዜማ ገልጿል።

በ2015 ዓ.ም ከ102 ሺሕ በላይ ሥራ ፈላጊዎች ወደ ውጭ አገራት መላካቸውን የገለጸው ሚንስቴሩ፣ በዘንድሮው ዓመት በውጭ አገራት እያደገ ከመጣው የሥራ ፍላጎት አንጻር 500 ሺሕ ዜጎችን ለመላክ ዕቅድ መያዙን የሚንስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አበበ አለሙ ለዋዜማ ተናግረዋል።

ወደ ውጭ ከተላኩት ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የሥራ ስምሪቱም ከቤት ውስጥ ሥራዎች ጋር የተገናኘ ነው ተበሏል።

በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ለውጭ አገራት የሥራ ስምሪት ብቻ የተመለመሉ 99 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት መኖራቸው ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት ወደ ውጭ የሚላኩ ሥራ ፈላጊዎች ለቤት ውስጥ ሥራ በመሆኑም፣ ተቋማቱ ከሶስት ወር የማይበልጥ ስለቤት ውስጥ ሥራዎች ስልጠና እና የብቃት መመዘኛ እየሰጡ እንደሚገኝ አበበ አስረድተዋል። 

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ሳውዲ አረቢያ ፣ ኳታር እና ጆርዳን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሥራ ስምሪት ስምምነት ተፈራርመው ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈላጊዎችን የሚቀበሉ መዳረሻ አገራት መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ ከፍተኛ የሥራ ፍላጎት እየመጣ ያለው ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች መሆኑንም የገለጹት አበበ፣ ለሥራ የሚላኩ ዜጎች ከፓስፖርት እና ከምርመራ ወጪ በስተቀር ምንም ዓይነት ክፍያ እንደማይከፍሉ ተናግረዋል።  

ሥራ አስፈጻሚው በቀጣይ መዳረሻ አገራቱን ለማብዛት ንግግርና ውይይት እያደረግንባቸው ያሉ አገራት አሉ ሲሉ ገልጸው፣ አገራቱን ንግግሩ ሲያልቅ ወደፊት እናሳውቃለን ብለዋል።

ሆኖም ወደፊት ሥራ ፈላጊዎችን ወደ አፍሪካ፣ አውሮፓና አሜሪካም ለመላክ በሰፊው መታሰቡን ነግረውናል።

መንግሥት የሰለጠኑ እና በከፊል የሰለጠኑ ዜጎችን ወደ ውጭ አገራት ለሥራ ለመላክ የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንዳለው የጠቀሱት አበበ፣ ለሙከራ ወደ ጀርመን አገር የተላኩ መሃንዲሶች እንዲሁም “ወደ ሌላ አገር” የተላኩ ነርሶች መኖራቸውን ገልጸዋል። 

የእነዚህ ባለሙያዎች ውጤት ታይቶ ሥራ ፈላጊ ዜጎችን አሰልጥኖ ወደ ተለያዪ አገራት ለመላክ በሰፊው መታቀዱን ነው የተናገሩት።

 መንግሥት ለአገር ውስጥ ሥራ ፈጠራ ቅድሚያ ይሰጣል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ ነገር ግን ፍልሰትን ማስቀረት ስለማይቻል ዜጎች በህጋዊ መንገድ ደህነታቸው ተጠብቆ በውጭ አገራ ሥራ እንዲፈጠርላቸው እየሰራ ነው ብለዋል።

መንግሥት ዜጎችን ለሥራ ወደ ውጭ የሚልከው የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ነው የሚሉና ሌሎች አንዳንድ ተገቢ ያልሆኑ ክሶች እንደሚሰሙም ጠቁመዋል።

መንግሥት ዜጎችን ወደ ውጭ ሲልክ አንድም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን እንደማያስብ በማንሳት፣ በእርግጥም ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኝ እና እንደ ቻይና ህንድና ፊሊፒንስ ባሉ አገራት የተለመደ አሰራር ነው ሲሉም ገልጸዋል።

መንግሥት ወደ ውጭ አገራት የሚላኩ ሥራ ፈላጊዎች የመብት ጥሰት እንዳይደርስባቸው እና ጥቅማጥቅማቸው እንዲከበር በየአገራቱ ካሉ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች ጋር እንደሚሰራ እንዲሁም፣ ገንዘባቸውን በአገር ውስጥ እንዲያጠራቅሙ ከባንኮችና ከኢትዮ ቴኮም ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አበበ፣ የውጭ አገራት የሥራ ስምሪት ላይ ድርሻ ካላቸው ተቋማት ጋር በየወሩ ግምገማ መኖሩንም ነግረውናል።

ዋዜማ በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ አውሮጳ አገራትና ወደ ካናዳ ትሄዳላችሁ ተብለው በመንግሥት ተቋማት የተመዘገቡና አሻራ የሰጡ፣ ወጣቶች መኖራቸውን ሰምታለች። 

አበበ ግን በመንግሥት እገዛ ከአራቱ አገራት (የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ሳውዲ አረቢያ ፣ ኳታር እና ጆርዳን)  ውጭ የሚላክ ሥራ ፈላጊ አለመኖሩን ጠቅሰው፣ በመንግሥት በኩል የሚመዘገቡ ሰዎች ስለሚሄዱበት አገር ቀድሞ እንደማይነገራቸው ገልጸዋል። [ዋዜማ]