ዋዜማ- የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በግፍና በኢ-ፍትሀዊነት  ከቀየው ፊንፊኔ (አዲስ አበባ) እንዲሰደድ የተደረገውን የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ቀደመ ስፍራው  እንዲመለስ እያደረግን ነው ሲሉ በይፋዊ ማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት ሲደርስበት በነበረው መገፋት የተነሳ ከተማዋን ለሌሎች ለቆ እስከመውጣት ደርሷል ያሉት ሽመልስ፣ይህም መገፋት ሄዶ ሄዶ እትብቱ በተቀበረባት ፊንፊኔ (አዲስ አበባ) የባዕድነት ስሜት እንዲሰማውና በራሱ ቀየ ላይ ባይተዋር እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።

ከተማዋ በሌሎች የበላይነት ስር ሆና በተለይም የኦሮሞን ሕዝብ ለዘመናት እንደ ባዕድ የመመልከት አካሄድን ስትከተል ቆይታለች ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፣ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በከተማዋ አንዳችም የኦሮሞን ህዝብ ማንነት የሚገልጽ ምልክት (symbolic represention) አለመኖሩ ነበር በማለት ጠቁመዋል።

“ከዚህ በኋላ ግን መንግሥታችን፣ያለፈውን የውድቀት ታሪክ፣ጉዳትና መፈናቀል ማውራት፣ እንዲህ ተደረግን ብሎ ስሞታ ማቅረብ አይሻም” ሲሉ ገልጸዋል።

ይልቁንም የተገኘውን ዕድል በመጠቀም፣ትላንት በሕዝባችን ላይ ሲደርስ የነበረውን ግፍና በደል ለመካስ ብሎም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም አዲስ ምዕራፍ ከፍተን ወደ ሥራ ገብተናል ብለዋል።

በዚህም መሠረት፣መንግሥት በግፍ ከቀየው የተፈናቀለውን ሕዝብ በመመለስ በከተማዋ በሁሉም ዘርፍ ካሉ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ይገኛልም ሲሉ ጠቁመዋል።

አዲስ አበባን በዚህ ወቅት ስንመለከት፣ በፖለቲካው፣በኢኮኖሚ፣በማኅበራዊ እንዲሁም በባሕል የሕዝባችንን ሰፊ ተሳትፎ የሚሹ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ይገኛሉ ያሉት ሽመልስ፣ይህም ሀሳባችንን ከግብ ለማድረስ ትልቅ መሳሪያ ይሆነናል ብለዋል።

እየተሠሩ ካሉት ከነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል፣የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣የኦቢኤን ሚዲያ ኮምፕሌክስ፣የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተፕራይዝ፣የኦሮሞ አርት ማሠልጠኛ ማዕከል፣የኦሮሞ ባሕላዊ ምግብ አሰራርና ዝግጅት ማዕከል፣የኦሮሞ ባሕላዊ እቃዎች ማሳያና የገበያ ማዕከል፣ሲንቄ ባንክ፣ቡሳ ጎኖፋ እንዲሁም የተለያዩ ኢንተርፕራይዞችን በጥቂቱ ማንሳት ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል።

እስካሁን ያለው አፈጻጸም፣መንግሥት የሕዝባችንን የዘመናት ጥያቄና እውነትን ወደ ቦታዋ ለመመለስ እንዲሁም ቃል የተገባውን ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኛነት ያሳየ ነው ብለዋል።

አሁንም የሕዝባችንን ያልተመለሱ ጥያቄዎች በሂደት ለመመለስ በትኩረት እንሰራለን ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፣ሕዝባችንን ከከተማው መግፋትና ማሳደድ ግን ከዚህ በኋላ አክትሞለታል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። [ዋዜማ]