ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት መርሀ ግብር ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተገነቡ 20/80 የጋራ መኖርያ ቤት ኮንደሚኒየሞች ውስጥ 22915 ቤቶች ነገ በአዲስ አበባ ዳርቻ ለልማት በሚል ተነስተዋል ለተባሉ አርሶ አደር አባወራዎችና 18 አመት ለሞላቸው ልጆቻቸው ለመስጠት ዝግጅቶች ተጠናቋል።

ዋዜማ ራዲዮ ቤቶቹን ለመረከብ ከጫፍ ደርሰዋል ከተባሉ ግለሰቦች ያገኘቸው መረጃ እንደሚያሳየውም ተነሽ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው ነገ ማክሰኞ መስከረም 27 ቀን 2012 አ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ የትኛው ሳይት ምን አይነት ቤት እንደደረሳቸው ይገለጽላቸዋል ተብሏል።ቀደም ብሎም የእጣ ቁጥር እንደተሰጣቸውም ታውቋል።


     ነገ ለሚከናወነው ስነስርአትም ሲባል ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተመረጡት የጋራ መኖርያ ቤቱ ተጠቃሚዎች ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ የሚወስዳቸው ትራንስፖርት ተዘጋጅቷል። ጉዳዩንም የቤቱ ተጠቃሚዎች በከፍተኛ ሚስጥር እንዲይዙት የተነገራቸው መሆኑን ፣ መረጃው ከወጣም ለሂደቱ እንቅፋት ይሆናል በሚል ተነግሯቸው እንደነበር ገልጸውልናል።


     ለአባወራ አርሶ አደር ባለ ሶስት መኝታ ቤት ኮንደሚኒየም የሚሰጥ ሲሆን 18 አመት ለሞላቸው ለእያንዳንዱ ልጆቻቸው ደግሞ በእጣ ባለ አንድም ባለ ሁለት ክፍል ኮንደሚኒየም ይሰጣቸዋል ተብሏል። ቀሪ 106 ቤቶችም ለተጠባባቂ ሰዎች መያዙንም ሰምተናል።


     ለአርሶአደር የልማት ተነሺዎች ከሚተላለፉት የጋራ መኖርያ ቤቶች ውስጥም በካራ ቆሬ በረከት ሳይት ከተገነቡት ውስጥ 3,500 ቤቶች እንዲሁም ኮዬ ፈጬ የተገነቡት ይገኙበታል። በዚህ ጉዳይ ላይ ልናናግራቸው የሞከርን ሀላፊዎች ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። የተወሰኑት ደግሞ ጉዳዩን እንደማያውቁትም ነው የገለጹልን።


     የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ባለፈው አመት የካቲት ወር መጨረሻ የ40 /60 እና የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤት እጣ ማውጣት ስነ ስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር መንግስት በአዲስ አበባ በልማት ምክንያት ለተነሱ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው የጋራ መኖርያ ቤት እንደሚሰጣቸው መግለጻቸው ይታወሳል።


የእጣ እድለኞች የሆኑ ቆጣቢዎች በኦሮሞ መብት ተከራካሪ ግለሰቦች አስተባባሪነት በተነሳ የወሰንና የአርሶ አደሮች የካሳ ያንሳቸዋል አመጽ የቆጠቡበትና እድለኛ የሆኑበት ቤት የወሰን ጥያቄ ኮሚቴ ተቋቁሞ ይታያል በመባሉ እስካሁን አልተላለፈላቸውም። ነገር ግን የልማት ተነሽ የተባሉ አርሶ አደሮችንና ልጆቻቸውን የመመዝገብ ስራ በሰፊው ሲሰራ መቆየቱን ከዚህ ቀደም ዋዜማ ራዲዮ መዘገቧም የሚታወስ ነው። በዚህም መሰረት የቤት ተጠቃሚ የሚሆኑት ሰዎች ቁጥር 22, 915 መሆኑን ለማወቅ ችለናል።
እነዚህ የልማት ተነሽ እንደሆኑ የተነገረላቸው የቤት ተረካቢዎች ለሚሰጣቸው የጋራ መኖርያ ቤትም ምንም አይነት ክፍያ አይከፍሉም።ሂደቱም ከፍተኛ የህጋዊነትና የፍትሀዊነት ጥያቄን አስነስቷል።


 በመጀመርያ አሁን የጋራ መኖርያ ቤት እንዲያገኙ የሚደረጉት የልማት ተነሽ የተባሉት አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው ቁጥራቸው ተጋኗል የሚል ነው። የልማት ተነሽ ያልነበሩ ግለሰቦችም በሰፊው ገብተውበታል ; ማንነት ላይ የተመሰረተ ምልመላም ተደርጎበታል የሚል ስሞታ በሰፊው እየቀረበ ነው።


 አሁን የጋራ መኖርያ ባለቤት ይሆናሉ ከተባሉት ውስጥ የዛሬ አምስት አመት አካባቢ ከካራ ቆሬ ለልማት ተብለው የተነሱት አርሶ አደሮች ይገኙበታል። በወቅቱ ከዚህ ስፍራ የተነሱ አርሶ አደር ያልሆኑ ቤተሰቦችም ነበሩ። ይሁን እንጂ የቱንም ያክል ይዞታ የነበራቸው ቢሆንም የተሰጣቸው ግን 75 ካሬ ሜትር ልዋጭ መሬት ብቻ ነው። ልዋጭ መሬቱም ለአባ ወራ ብቻ እንጂ ልጆችን አላካተተም። ቤት መስሪያ ተብሎ የተሰጣቸው ብርም በዛ ቢባል ስምንት ሺህ ብር ነበር።


    አርሶ አደር ለነበሩት ተነሺዎች ግን እስከ 500 ሺህ ብር በጥሬ ተሰጥቷቸዋል። ምትክ ቦታም ለአባወራ 500 ካሬ ሜትር ለልጆቻቸው ደግሞ ለእያንዳንዳቸው 250 ካሬ ሜትር ተሰጥቷቸዋል። ከነዚህ ተነሽ አርሷ አደሮች ውስጥ አሁን ላይ በጥሩ ኑሮ ደረጃ ላይ ያሉት አሁንም ያለ ምንም ክፍያ የጋራ መኖርያ ተጠቃሚ ይሆናሉ።


በተመሳሳይ ጊዜ በዚሁ ካራ ቆሬ 73 አርሶ አደር ያልሆኑ አባወራዎች ህገ ወጥ ናችሁ በሚል ያለ ምንም ካሳ ቤታቸው ፈርሶ እስካሁን ችግር ውስጥ ያሉ አሉ። ከዚህ ቀደም ከመሀል አዲስ አበባ ለልማት ተብለው የተነሱ ነዋሪዎች ኮንደሚኒየም ሲሰጣቸው ክፍያ ይጠየቁ እንደነበር ይታወሳል።


     እንዲሁም መንግስት ከቆጣቢ ዜጎች የሰበሰበውን ገንዘብ ጨምሮ የሰራውን የጋራ መኖርያ ቤት የ20/80 ባለእድለኛ ለሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዳይተላለፍ የተደረገውን እገዳ ለማንሳት ጥረት ባልተደረገበት ሁኔታ 23 ሺህ የሚደርሱ የጋራ መኖርያ ቤቶችን ለማስተላለፍ መወሰኑ የፍትሀዊነት ጥያቄን አስነስቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]