Ahmed-Jebel

  • “አስቸኳይ ህክምና ለአህመዲን ጀበል አሁኑኑ” በሚል የፌስቡክና የትዊተር ዘመቻ ይካሄዳል

ዋዜማ ራዲዮ- ሀያ ሁለት ዓመታት እስር ተፈርዶበት ወህኒ የሚገኘው ኡስታዝ አህመዲን ጀበል የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ህክምና እንዲፈቀድለት ቤተሰቦቹ እየወተወቱ ነው።
ያለፉትን አምስት አመታት በእስር ላይ ያለውና ተወዳጅ የታሪክና የሀይማኖት መምህር የሆነው ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ለእስር የተዳረገው የሙስሊሙ ማህበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ህዝብ ግንኙነት ሆኖ በሚሰራበት ወቅት ነበር።
መንግስት በአህመዲንና በሌሎች ተከሳሾች ላይ በሽብር ወንጀል ክስ ከአስራ አምስት እስከ ሀያ ሁለት ዓመታት እስር የፈረደ ሲሆን የተወሰኑት ተከሳሾች በይቅርታ እንዲፈቱ ተደርጓል።
ኡስታዝ አህመዲን በደረሰበት ከፍተኛ የኩላሊት ህመም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለሁለት ወራት ህክምና ተደርጎለትና በኩላሊቱና በፊኛው መካከል የብረት ቧንቧ ተገጥሞለት ህመሙን ለጊዜው ቢያስታግስም አሁን ህመሙ ተባብሶ በመቀጠሉ ህክምና እንዲያገኝ ቤተሰቦቹ ተማፅኖ አቅርበዋል።
“መቆምም ሆነ መተኛት ከብዶታል፣ ውህኒ ሊጠይቁት የሚሄዱ ሰዎችን እንኳን ቆሞ ማነጋገር አልቻለም”  ይላል እንድ የቅርብ ወዳጁ ለዋዜማ ሲናገር።
የወህኒ ቤቶች አስተዳደር አህመዲን ተጨማሪ ህክምና እንዲያገኝ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ በማድረጉ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ከሰሞኑ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑን ወዳጆቹ ነግረውናል።