Abiy and Erdogan August 2021 in Ankara- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የህዘብ ተወካዮች ምክርቤት ግንቦት  9 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ጉባኤ በኢትዮጵያ እና በቱርክ መንግስታት መካከል የተደረጉ ሶስት ወታደራዊ ስምምነቶችን አጸደቀ፡፡

የዋዜማ ሪፖርተር እንደዘገበችው በፓርላማው የጸደቁት ሶስቱ ስምምነቶች የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት፣ የወታደራዊ ፋይናንስ ትብብር ስምምነት፣ እንዲሁም የፋይናንስ ድጋፍ ማስፈጸሚያ ፕሮቶኮል ናቸው ፡፡

የመጀመሪያው የወታደራዊ ስምምነት ነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያና በቱርክ መንግስታት መካካል በቱርክ ዋና ከተማ በአንካራ የተደረገ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ እንደሆነ በአዋጁ ተብራርቷል፡፡

ሁለቱ አገራት በትምህርትና ስልጠና በተናጥል ወይንም በጋራ በሚያዘጋጁት ወታደራዊ ልምምዶች ለመካፈል፣ በመከላከያ ኢንዳሰትሪ፣በመከላከያ መረጃ ልውውጥ፣ በመከላከያ መረጃ ሎጅስቲክ፣በመከላከያ ጤና አገልግሎት፣ በኮሚዩኒኬሽን፣አሌክትሮኒክስ፣የመረጃ ስርዓትና የሳይበር ጥቃት መከላከል፣ ከመደበኛ ጦርነት ውጭ እንደ ሰላም ማሰከበር፣ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የባህር ላይ ውንብድና መከላከል ላይ በሚደረጉ ዘመቻዎች ለመተባበር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በማብራሪያው ተቀምጧል፡፡

በተጨማሪም በዚሁ ስምምነት ውስጥ በመከላከያ ከፍተኛ ሃላፊዎች ወይንም በምክትሎቻቸው መካከል የሚደረግ ስብሰባ ወይንም ውይይት እንዲሁም በባለሙያዎች መካከል የሚደረግ የልምድ ልውውጥ፣ የፈንጅና ተቀጣጣይ ቁሳቁሶችን የማምከን ስልጠና እና ሌሎች ጉዳዮች የተካተቱበት ሲሆን አፈጻጸሙ በእንካ-ለእንካ መርህ መሰረት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

ሁለተኛው ስምምነት የወታደራዊ ትብበር ለማድረግ የሚያስችል የወታደራዊ ትብበር ፋይናን ስ ስምምነት ሲሆን በዚህ ስምምነት መሰረት ነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በአንካራ በተደረገ ስምምት ከቱርክ መንግስት ለኢትዮጵያ  የአንድ መቶ ሚሊዮን የቱርክ ሊሬ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የአሜሪካ ዶላር ለኢትዮጵያ መንግስት የተደረገ ድጋፍ ነው፡፡

በዚህ ድጋፍ  የኢትዮጵያ መንግስት በቱርክ ከሚገኙ ኩባንያዎች ስሪታቸው ሙሉ በሙሉ በቱርክ አገር የሆኑ የመከላከያ መሳሪያዎችና አገልግሎቶችን በአምስት አመት ውስጥ እንዲገዛ የሚያደርግ ሲሆን ስምምነቱ እንዲጸድቅ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሮጀክት ፕሮፖዛል በማዘጋጀትና ዝርዝር ቴክኒካል መግለጫዎችንና የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከሚፈልገው የመሳሪያ አይነትና ከፎቶ ጋር በማያያዝ  ለቱርክ መንግስት እንዲያቀርብ ያስገድዳል፡፡

በቱርክ መካላከያ ሚንስቴር አስተባባሪነት ተመድበው የሚገዙ መሳሪያዎችን ያለቱርክ መንግስት የጹህፍ ፈቃድ ለሌላ ሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ ወይንም ጥቅም ላይ እንደማይውሉ ተደንግጓል፡፡

ሶስተኛው የስምምነት ነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በአንካራ የተደረገ ሲሆን በዚህም ከቱርክ መንግስት ለተገኘው የፋይናንስ ድጋፍ ማስፈጸሚያ የሚውልና ለአምስት አመት የሚቆይ ከአምስት ሚሊዮን የቱርክ ሊሬ ተመጣጣኘ የሆነ የአሜሪካን ዶላር ሲሆን በዚህ የድጋፍ ገንዘብ  በቱርክ መከላከያ ስር በሚገኙ የማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ስልጠና ለሚከታተሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል  አባላት የትራስፖርት፣ ማረፊያና በቱርክ መከላከያ ሃይል ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቁ ተብለው ከተለዩ ስልጠናዎች በስተቀር የስልጠና ወጭን ለመሸፈን እንደሚውል ተገልጿል፡፡

በሶስቱም ስምምነቱ መሰረት ሁለቱ አገራት መካከል በስጦታም ይሁን በክፍያ ከአንዱ ወገን ወደ ሌላው ወገን የተሰጡና የተላኩ መረጃዎች ወይንም መሳሪያዎች ወይንም በጋራ የተሰሩ ሰነዶችም ይሁን መሳሪዎች ለሌላ ሶተኛ ወገን ያለ ሁለቱ አገራት ይሁንታ መተላለፍ እንደማይችሉ ተቀምጧል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]