ዋዜማ ራዲዮ- ከተከዜ የኀይል ማመንጫና አላማጣ ከሚገኘው ኀይል ማሰራጫ ኤሌክትሪክ ሲያገኙ የነበሩ የአማራና አፋር ክልል ከተሞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሃይል ለማቅረብ አስቸጋሪ እንደሆነ የኤሌክትሪክ ኀይልና አግልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ገለጹ፡፡

ከሃምሌ 2013 ዓ.ም  ጀምሮ የህወሓት ታጠቂዎች ተቆጣጥረዋቸው በነበሩ የአማራና የአፋር ክልሎች የሚገኙ በርካታ አካባቢዎች የፌደራል መንግስቱ ሃይሎች ከታህሳስ 2014 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማድረስ ቢቻልም አሁንም በርካታ ከተሞች አገልግሎቱን ማግኘት አልቻሉም፡፡

ሁለቱ ክልሎች የኤሌክትሪክ ሃይል ምንጫቸው በህወሃት ቁጥጥር ስር ካሉት የተከዜ ሃይል ማመንጫና የአላማጣ ማሰራጫ ጣቢያ በመሆኑ ነጻ ለወጡት በርካታ አካባቢዎች  አገልግሎቱን ማቅረብ እንዳልተቻለ የሁለቱ ተቋማት የኮሚዩንኬሽን ሃላፊዎች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ 

ለአብነትም በዋግህምራ ዞን የዞኑን ዋና ከተማ ሰቆጣን ጨምሮ፣ አምደወርቅ፣ኑራቅ፣ ዝቋላና ሌሎች ከተሞቸ ላይ የሚገኙ አራት የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ከግማሽ አመት በላይ አገልገሎት እንዳላገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚኒዩኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታየ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የሰሜን ወሎ የተወሰኑ አካባቢዎች በተለይም ላሊባለ ፣አይና ቡግና፣ከፊል ቆቦ፣ ሮቢት ሙሉ በሙሉና አፋር የተወሰኑ አካባቢዎች አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆኑ  አክለው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ላሊበላ ከተማ በየአመቱ የሚከበረውን የገና በዓል ያለኤሌክትሪክ እንዳይከበር በሚል በዲዝል ጀኔሬተር  በከተማው ለሚገኙ ወደ 60 ሽህ ለሚጠጉ ነዋሪዎች አገልግሎት እያገኙ የነበረ ቢሆንም ከጥቂት ቀናት በፊት መቋረጡን የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚኒዩኬሽን ዳይሬክተር እንዳሉት የሰቆጣ ከተማን መልሶ ለማገናኘት ከተከዜ የሃይል ማመንጫ እንዲሁም የላሊበላና የአይና ቡግና ከተሞችን ከአላማጣ ማሰራጫ የሚያገኙ በመሆኑ እነዚህን ከተሞች መልሶ ለማገናኘት አሁን ካለው  የጸጥታ ሁኔታ  ጋር በተገናኘ አግልግሎቱን ለማቅረብ እንደማይፈቅድላቸው አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠትም አስቸጋሪ እንደሆነና ጊዜዊ መፍትሄ ይሰጥ ተብሎ ከሌላ መስመር በማገናኘት ማሰራጫ መገንባት ቢታሰብ እንኳ ትልቅ ሃብትና ጊዜ የሚጠይቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አሁን ባለው ሁኔታ የተወሰኑ ቦታዎችን ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት አገልገሎቱን ማቅረብ እንዳልተቻለና በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አገልግሎቱ እንዲመለስ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በላሊበላ ከተማ አገልግሎት እየሰጠ የነበረው የዲዝል ጀኔሬተር ጊዜዊ መፍትሄ ለመስጠት ከገናሌ ዳዋ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ተነቅሎ ወደ ላሊባላ እንደተዛወረ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ኤሌክትሪከ አገልግሎት የማያገኙ አካባቢዎች የነበሩ ማሰራጫዎች ላይ የነበሩ መሳሪያዎች ሙሉ በሙሉ ተነቅለው መወሰዳቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡ 

የላሊባላ ከተማ ምክትል ከንቲባ ለዋዜማ እንደገለጹት ከታህሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለህዘቡ በየአስር ቀኑ እስከ 25 ሽህ ሊትር ነዳጅ ወይንም በወር እስከ ሶስት ሚሊዮን ብር በክልሉ እየተደጎመ አገልግሎት እየቀረበ እንደነበር ነገር ግን አሁን ላይ ድጎማው በመቅረቱ አገልገሎቱ ተቋርጧል፡፡

የከተማው ህዝብ በዲዝል ጀኔሬተር ያለምንም ክፍያ በነጻ ኤሌክትሪከ ከሞላ ጎደል በፈረቃ እየገኘ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ የፋይናንስ እጥረቱ ጋር ተዳምሮ ወደ ከተማው የሚላከው የነዳጅ አቅርቦት ውስን መሆን ችግሩን እንዳባበሰው አቶ ማንደፍሮ ተናግረዋል፡፡

ከኤሌሌክትሪክ አቅርቦቱ በተጨማሪ የከተማው የውሃ አቅርቦት በኤሌክትሪክ ሃይል ተስቦ የሚቀርብ በመሆኑ አሁን ላይ ውሃ በቦቲ በመጫን እየተከፋፈል እንደሆነና በትንሸ አቅማቸው አገልግሎት እየሰጡ የነበሩ ሆቴሎችና የእህል ወፍጮ ቤቶችም ችግር ላይ መውደቃቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ችግሩ በቋሚነት ከአላማጣ ውጭ ባሉ ሌሎች አማራጮች እንዲቀርብ ወይንም ክልሉ ድጎማ አድርጎ ለሚያቀርበው አገልግሎት ህዝቡ ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲከፍል የሚሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለክልሉ የበላይ ሃላፊዎች አቅርበው መልስ እየተጠባበቁ መሆኑን ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በመሰረተ ልማቶቹ ላይ በህወሃት ታጣቂዎች የደረሰ ዘረፋና ውደመትን በተመለከተ ያካሄደውን ጥናት የካቲት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ለጋዜጠኖች ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም በአማራና አፋር ክልሎች ተቋሙ የደረሰበት ጉዳትና ኪሳራ  ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚገመትና በሁለቱ ክልሎቹ ከሚገኙት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ውስጥ 53 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው ጉዳት እንዳደረሱብት ተገልጿል፡፡

እሰካሁን መሠረተ ልማቶችን በመጠገን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ በአስቸኳይ እንዲቀጥል ለማድረግ የወጣው የማቴሪያል ወጪ ብቻ ከ 29 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መድረሱንና  መሰረተ ልማቱ ሙሉ  ለሙሉ  በመልሶ ጥገና አስተካክሎ በአስተማማኝ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከ23 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የፋይናንስ ወጪ እንደሚጠይቅ አቶ ሞገስ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በመሰረተ ልማት ጉዳት ሳቢያ 147 ነጥብ 19 ሚሊዮን ኪሎ ዋት በሰዓት ኤሌክትሪክ በገንዘብ ሲተመን 231 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር  ተቋሙን ለኪሳራ  ማደረጉን አመላክተዋል፡፡ 

በተጨማሪም ከወልዲያ ተነቅሎ የተወሰደው ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ከሁለት መቶ ሚሊየን ብር በላይ እንደሚገመት፣ በቢሮዎች፣ በማከፋፈያ ጣቢያዎችና በሰራተኞች መኖሪያ ቤቶች የደረሰው የንብረት ውድመትና ዝርፊያ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑንና ከሰሜን ምስራቅ ሪጅን የተወደሱት ተሸከርካሪዎች 12 ሚሊየን ብር እንደሚገመቱ አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]