የኢትዮጵያ መንግስት የወደብ አጠቃቀምን ጨምሮ ሌሎች የሁለትዮሽ የትብብር ሰነዶችን ለኤርትራ መንግስት ቢልክም ለወራት ከአስመራ ምላሽ አልተገኘም።

ዋዜማ ራዲዮ- ባለፈው አመት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ “ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ዘላቂ ሰላም እንዲኖራት በሚል የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ቅድመ ሁኔታ ትተገብራለች” ካለ በሁዋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ አስመራ አቅንተው ፤ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ወደ አዲስ አበባ መጥተው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትም ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩ ተበስሯል።


አሁን ግን በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለው ወዳጅነትና ተራርቀው በነበሩት በሁለቱ ሀገር ህዝቦች መካከል መቀራረብ ቢኖርም የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት በታሰበው ፍጥነት ህጋዊና ተቋማዊ መልክ ማስያዝ ፈታኝ ሆኖ ብቅ ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከአምስት ወር በፊትም ከኤርትራ ጋር በኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ የተጠናከረ ግንኙነትን ማዳበር የሚያስችሉ ሰነዶች እንዲዘጋጁ በማድረግ ለኤርትራ መንግስት ልኳል። ሰነዶቹም የወደብ አጠቃቀም ፣ የሀገራቱ የመንገድ ትስስርና የጋራ መገበያያ ቦታዎችን የተመለከቱ ስምምነቶች ምን መሆን እንዳለባቸው በኢትዮጵያ በኩል ያሉ የስምምነት ፍላጎቶችን የሚያሳዩ ናቸው።

ሰነዶቹ የመላካቸው አላማም የኤርትራ መንግስት ያለውን አስተያየትና የሚጨምራቸው ጉዳዮች ካሉም አክሎበት ወደ ስምምነት ተገብቶ የኢኮኖሚ ትስስሮች እንዲፈጠሩ ነው። ሆኖም ሰነዶቹ ከተላኩ አምስት ወራት በኋላ ከኤርትራ መንግስት በኩል ምንም አይነት ምላሽ እስካሁን ሊገኝ አልቻለም። ይህም በኤርትራ በኩል ለኢኮኖሚ ትስስር ባለው አቋም ላይ ጥርጣሬን በመጫር በኢትዮጵያ በኩል ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ደስተኛ አላደረጋቸውም።

በሌላ በኩል በተለይ ከወደብ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የኤርትራ ባለስልጣናት የደበቁት ሚስጥር ሊኖር እንደሚችል በኢትዮጵያ በኩል ያሉ ባለስልጣናት ለዋዜማ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
ኢትዮጵያ የሚያዋጣት ከኤርትራ ወደቦች አሰብን ብትጠቀም እንደሆነ ቢታወቅም ከኤርትራ ባለስልጣናት በኩል ኢትዮጵያ ምጽዋን እንድትጠቀም የሚገፋፉ ንግግሮች እንደሚደመጡ ነው የሰማነው። የኢትዮጵያን ፍላጎት እያወቁ የኤርትራ ባለስልጣናት ይህን ግፊት የሚያደርጉት ፣ ምናልባት በአሰብ ወደብ ዙርያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ከዚህ ቀደም ደርሰውታል የተባለው ስምምነት የሚያመጣባቸው ነገር ሊኖር ስለሚችል ነው የሚል ግምትን አስወስዷል።


በዚህ ጊዜ የኢኮኖሚ ትስስር ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር መደረጉ አስመራ በአዲስ አበባ እንድትዋጥ ያደርጋታል የሚል ስጋት ከኤርትራ ባለስልጣናት በኩል አለም ይባላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ ወግ በተሰኘው የርሳቸውን አንደኛ አመት በዘከረው የሁለት ቀን የምክክር መድረክ ማጠናቀቂያ ላይ ተገኝቸው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት የመሪዎች ሆነ እንጂ የተቋም ቅርጽ አልያዘም በሚል ተነስቶ ለነበረ ጥያቄ በስጨት ብለው ምላሽ የሰጡትም በዚህ ምክንያት ነው የሚሉ አስተያየቶች አሉ።
ከአስመራ ወገን ባደረግነው ማጣራት፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የሚመለከት የራሷ ሰነድ አዘጋጅታለች። ሰነዱ ከጥቂት የሀገሪቱ ባለስልጣናት በቀር ለማንም ይፋ ሳይደረግ ተይዟል።


የኤርትራው ሰነድ በሁለቱ ሀገሮች መካከል አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ የመፍጠር ዓላማ ያለው ሲሆን ለብዙ ዝርዝር ጉዳዮች ግን ምላሽ መስጠት የማይችል የፖለቲካ ሰነድ ነው።
ሰነዱ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ከውህደት በመለስ ሰፊ ፍላጎቶች የተንፀባረቁበት ሲሆን አስመራ በአዲስ አበባ ልትዋጥ ትችላለች የሚል ስጋት ያላቸው የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪዎች በሰነዱ ላይ ትችት አቅርበውበታል።
ስለ ሰነዱ የሰሙ ኤርትራውያን “ኢሳያስ ሀገራችንን ሊሸጥ ነው” በሚል ቅሬታ ማሰማት ከጀመሩም ሰነባብተዋል።


ከሶስት ወራት በፊት ሐዳስ ኤርትራ ጋዜጣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የታደሙበትን አንድ የውይይት መድረክ ጠቅሶ እንደዘገበው በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ግንኙነትን መንግስታቸው ለሁለቱም ሀገሮች ወደሚበጅ ደረጃ ለማድረስ ኢሳያስ እቅድ መንደፋቸውን አስነብቧል። የዋዜማን ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ

https://youtu.be/dMurc-DUSe4