ዋዜማ ሬዲዮ -የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162 አንቀጽ 8 ስለ ማሟያ ምርጫ ያትታል። በዚህ አንቀጽ ከተካተቱት ሁለት የማሟያ ምርጫ ማድረጊያ መንገዶች አንዱ በማንኛውም ምክንያት ተመራጩ በቦታው አለመገኘት ሲሆን ሁለተኛው በመራጩ ህዝብ በኩል አመኔታን ማጣት እንደሆነ ያብራራል።
በዚህ አንቀጽ መሰረት ኢትዮጵያን ወክለው ወደ ተለያዩ ሃገራት በአምባሳደርነት የተሾሙ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ አንድን በተጻረረ መንገድ ኢትዮጵያ ማሟያ ምርጫ አድርጋ አታውቅም።
በቅርቡ በአሜሪካ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት የቀድሞው የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር ሚንስትር በኋላም በሚንስትር ማዕረግ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪ እና አማካሪ የነበሩት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የ2013 ዓም ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ የቦሌ ክፍለ ከተማ ምርጫ ጣቢያ 17 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ሆነው ተወዳድረዋል። በአብላጫ ድምጽም የገዥው ፓርቲ ብልጽግናን በመወከል ፓርላማ ወንበር አግኝተዋል።
አምባሰደር ስለሺ በቀለ(ዶ/ር) የብልጽግና እጩ ሆነው በተወዳደሩበት የቦሌ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 17 የኢዜማው አንዱዓለም አራጌ የህብር ኢትዮጵያው ዘለቀ ረዲ እና የባልደራሱ በቃሉ አጥናፉ(ዶ/ር) እጩ ሆነው መቅረባቸው አይዘነጋም።
የፓርላማ አባላት የተወከሉበትን ወንበር ጥለው በአምባሳደርነት ሲሾሙ ስለሺ በቀለ(ዶ/ር) የመጀመሪያው አይደሉም። ከዚህ በፊትም የቀድሞው የህወሃት አባላት አምባሳደር ስዩም መስፍን፣ የአሁኑ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እንዲሁም ጅማን ወክለው በስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ ፓርላማ ገብተው የነበሩትና በቅርቡ ወደ ለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዲፕሎማትነት ያቀኑት ሱልጣን ኢብራሂም አባጊሳ ይታወሳሉ።
ዋዜማ ሬዲዮ ከምርጫ ቦርድ በኩል ስለጉዳዩ ጠይቃ እንደ ተረዳችው ቦርዱ እንደ አንድ አስፈጻሚ አካል በጎደለ የምክር ቤት አባል ቦታ የማሟያ ምርጫ ጥያቄ ሲቀርብለት በስድስት ወር ውስጥ ምርጫ እንደሚያካሂድ መረዳት ተችሏል። እስካሁን ግን ከተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ አባሉ ከጎደለበት የብልጽግና ፓርቲ የማሟያ ምርጫ ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ አለመቅረቡን ዋዜማ ተረድታለች።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የፓርላማ አባላትም እንዲህ ያለ ጉዳይ ሲያጋጥም ማሟያ ምርጫ ሳይደረግ ቦታው ክፍት ሆኖ እንደሚቀር መስክረዋል። [ዋዜማ ሬዲዮ]