Photo Credit- EthioTube
Photo Credit- EthioTube

በመስፍን ነጋሽ- ዋዜማ ራዲዮ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ (ጠ/ሚሩ) ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ በርካታ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። በየዕለቱ የሚደረጉ ነጠላ እርምጃዎች አገሪቱ በሆነ አይነት የለውጥ ሒደት ውስጥ እያለፈች መሆኑን በማያጠራጥር መልኩ ይናገራሉ። ይሁንና እነዚህ ነጠላ ለውጦችና ክስተቶች በራሳቸው ካላቸው ትርጉምና ክብደት አልፎ በአጠቃላዩ ሒደት ውስጥ ያላቸውን ስፍራ በምልአት ለመረዳት አይቻልም፤ መገመት እና መመኘት እንጂ። ነጠላዎቹ ክስተቶች በምን እና እንዴት እንደሚያያዙ፣ ተደጋግፈውም ይሁን ተቃርነው ወደየትኛው የለውጥ ወንዝ እንዲፈሱ እንደታቀደ፤ ይህ ሒደት ምን ያህል ዋጋ እና ጊዜ እንደሚፈልግ፤ የትኞቹ አካሎች መቼና እንዴት የሒደቱ ባለቤቶችና ተስታፊዎች እንደሚሆኑ ወዘተ ማስረዳት ቀርቶ ሊጠቁሙን የሚሞክሩ ዝርዝር ፍኖተ ካርታዎች የሉም። በነጠላ ክስተቶቹ ከመደመም፣ ከመደነቅ፣ ከመደንገጥ፣ ምናልባት ከማዘን አልፎ የለውጡን ጎርፍ ምንነት በቅጡ ለመረዳት ገና ትግል ላይ ነን።  ሙሉ ሰነዱን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ (PDF)

**************************
አሁን ያለው የለውጥ መንፈስና ጅምርም ይሁን ነጠላ ድርጊቶች ሊቀለበሱ፣ ሊከሽፉ ወይም ሊጠለፉ እንደሚችሉ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። ነጠላ ድርጊቶችን/እርምጃዎችን መደገፍ አጠቃላይ ሒደትን ከመረዳትና ከመደገፍ በእጅጉ የተለየ ነው። ምክንያቱም በአጠቃላይ ሒደቱና በታሰበው ግብ ላይ የተስማማ ወገን፣ በነጠላ ድርጊቶች ባይስማማ እንኳን ትችቱን እያቀረበ ለሒደቱ ታማኝ ደጋፊ ሆኖ ይቀጥላል። በነጠላ እርምጃዎች ላይ የተመሠረተ አጋርነት ጊዜያዊ ከመሆን አያልፍም፤ ይህ አይነቱ ደጋፊ የማይስማማበት ነጠላ እርምጃ ሲወሰድ (አውቆም ይሁን ሳያውቀው) የአጠቃላይ ሒደቱ ተቃዋሚ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ድጋፉ የፋሽን፣ ጥርጣሬው የልማድ ጉዳይ የሚሆንበት አይጠፋ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ፣ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት ብቻውን ለለውጡ ስኬትና ዘላቂነት ማረጋገጫ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም።
**********************
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ በአነስተኛ ዋጋ ልናካሒድ የምንችለው ለውጥ በቅደም ተከተል ውጫዊ ግፊት፣ የኢሕአዴግ ተሐድሶ (Reform)፣ አገራዊ ተሐድሶ፣ አገራዊ ሽግግር (Transition)፣ እና አገራዊ የዴሞክራሲ ግንባታ (Consolidation) ሙከራ ነው እላለሁ። በአነስተኛ ዋጋ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግ እጅግ ቀናው መንገድ ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ/ቡድን ውስጣዊ ተሐድሶ (ሪፎርም) በማድረግ የለውጡ አካል የሚሆንበት መንገድ ነው። ይህም ገዢውን ፓርቲ የለውጡ አንድ ማዕከል/ምኅዳር እና ወሳኝ ተዋናይ ያደርገዋል፤ የመንግሥት መፍረስ አደጋን በእጅጉ ይቀንሳል። እኛ አገር እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፤ ከዘለቀ። አሁን ባለው ሁኔታ ኢሕአዴግ ከነውስጣዊ ቀውሱ አንዱ ቁልፍ ተዋናይ፤ የድርጅቱ ውስጣዊ መስተጋብር የለውጡ አንድ ወሳኝ ምኅዳር ነው።

ጥገናዊ ለውጥ ወይስ ስር ነቀል ለውጥ? የሽግግር መንግሥት ወይስ ምርጫ?

በኢሕአዴግ ውስጥ እየሆነ ያለውን፣ በመንግሥትና ከዚያም ውጭ ካለው አገራዊ ተሐድሶ ለይቶ መመልከት እጅግ አስፈላጊ ነው። ተዋናዮቹን በየምኅዳሮቻቸው መረዳትና መተንተን ካልቻልን፣ ድጋፋችንም ይሁን ትችታችን ብልቶቹን ከመላው አካል ለይቶ የሚያይ ካልሆነ፣ የዕለት ሁኔታውን ከዜና መዋዕሉ ካምታታነው ራሳችንን ለብስጭት ማዘጋጀት ይኖርብናል። በተመሳሳይ መልኩ፣ አገራዊ ተሐድሶውን እና ሽግግሩን በአነስተኛ ዋጋ ልናሳካ የምንችልባቸውን የመፍትሔ አማራጮች ስናሰላስል፣ የተለመዱት ሐሳቦች እስረኛ አለዚያም የሌሎችን የመገልበጥ ሱሰኛ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል።
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የጀመሩት ተስፋ ሰጪ እርምጃ እንዲቀጥል ማበረታታት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አገራዊ የፖለቲካ ተሐድሶ እና ሽግግር ፍኖተ ካርታቸውን እንዲያሳውቁ መወትወት ይገባል። ተቃዋሚዎች እና ሲቪል ማኅበራትም በበኩላቸው የየራሳቸውን አማራጭ ፍኖተ ካርታዎች ለማዘጋጀት እንዲታትሩ መቀስቀስና መርዳት ያስፈለጋል።

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ  (pdf) በርከት ያሉ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያሻቸው ወይም የተዘለሉ ወይም የተረሱ ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ። መነበብን የሚከለክሉ ግን አይመስለኝም። ይህ ሁሉ ዳርዳርታ፣ በትችትም ይሁን በድጋፍ መልኩ፣ በዜናዎች ዙሪያ ከሚሽከረከር እሰጥ አገባ ወጥተን በዘላቂ ጭብጦች ላይ ወደመከራከር እንድንሸጋገር ለመጋበዝ ነው። ግብዣ ነው። ጥሪ ነው። ጠሪ አክባሪ!
በኢትዮጵያ ተስፋ አንቆርጥም። በጭራሽ!  ሙሉ ሰነዱን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ  (PDF)