BG Adem Mohamed Ethiopia Defense chief- Photo FBC

ዋዜማ ራዲዮ- ቀደም ሲል የነበሩትን የመከላከያ ሰራዊት ስትራቴጂክ ስነዶች ያሻሻለውና ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስትራቴጂ ተቋሙ የምድር፣ የአየር፣ የባህርና የሳይበር ክፍሎች እንዲኖሩት ተደርጎ መዋቀሩን ያወሳል።


አምስት ክፍሎች ባሉት በዚህ ሰነድ የመከላከያ ሰራዊት ራሱን ከዘመኑ ጋር ከሚሄድ ቴክኖሎጂ እንዲያስተዋውቅ፣ በዓላማው ላይ ግልፅነት እንዲኖርና በውስን ሀብት ውጤታማ መሆን የሚችልበት ስልት ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም ሰራዊቱ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ እንደተፃፉ የሚነገርላቸው “የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ” እና “የኢፌዲሪ ስራዊት ዶክትሪን” የሚል ርዕስ ያላቸው ሁለት አብይ ሰነዶችን የስትራቴጂክ መመሪያው አድርጎ ይጠቀም ነበር። “የውጪ ጉዳይ ፖሊሲና ደህንነት ስትራቴጂ” የተባለ ገዥው ፓርቲ ያሰናዳው ሰነድም ለረጅም አመታት ማጣቃሻ ሆኖ ሲሰራበት ቆይቷል።
እነዚህ ሰነዶች ከጊዜው ጋር መራመድ ባለመቻላቸውና አንዳንዶቹም ከህገመንግስቱ ጋር የሚፃረሩ በመሆናቸው በአዲስ መተካት ማስፈለጉን 49 ገፅ ያለው ይህ ሰነድ ዘርዝሯል።


የሰራዊቱ አላማና ግብ በተብራራበት ክፍል ላይ ሰራዊቱ በፖለቲካ ፓርቲ ርዕዮተ አለም የተቃኘ እንዳይሆንና ተጠሪነቱ በህዝብ ለተመረጡ ወኪሎች የሚመራውም ህገመንግስቱን ብቻ መሰረት አድርጎ እንደሆነ ያወሳል።

ስለዚህ የመከላከያ ዋና ተልእኮ በሕዝቦች ሉዐላዊነት መጠበቅ ዙሪያ ነው። ስለሆንም ሠራዊት ከፖለቲካ ስልጣን ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ንክኪ ሊኖረው አይገባም።


የኢፌዴሪ ሠራዊት ዋና ዓላማ ሕብረ፡ብሔራዊ አንድነቷ የፀና፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ሕገ፡መንግስታዊ ሥርዓት፣ የሀገረ፡መንግስቱ እና የሀገረ፡መንግስቱን ግዛታዊ ሉዐላዊነትና አንድነት እንዲሁም የሕዝብ ደህንነት ከማንኛውም ዓይነት የውስጥና የውጭ ጥቃት መከላከል ነው። ይላል


ስራዊቱ ከውጪ ሀይሎች ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን መመከት ላይ አፅናዖት ሰጥቶ ያብራራና በሀገር ውስጥም ህገመንግስቱንና ሀገረ መንግስቱን ሊገዳደሩ የሚሞክሩና የህዝብን ሉዓላዊነት የሚጥሱ ጉልበተኞችን ይፋለማል ይላል ዋዜማ የተመለከተችው ስነድ።

ሠራዊቱ የሕዝቦችን ሉዐላዊነት እና የሉዐላዊነታቸው መገለጫ የሆነውን ሕገ፡መንግስታዊ ስርአቱን ከወራሪዎች፣ ከአመፃዎች እና ጉልበትን ከሚጠቀሙ ማናቸውም ኃይሎች መከላከል የመጨረሻው ተልዕኮው ነው። ጉልበትን መሰረት ያደረጉ ውጫዊና ውስጣዊ የሉዐላዊነት እና የሕገ፡መንግስት ጥሰቶች የመከላከል የመጨረሻ ጫፍ መከላከያ ሠራዊት ነው።

ስነዱ በመጨረሻ ክፍሉ ላይ


ከታሪካችን እንደምንማረው ጠላቶቻችን ሠራዊታችንን ለመበትን እና ሀገራችንን ለማጥቃት ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች አንደኛው ብዝሀነታችንን እንደ ክፍተት ከማየት የመነጨ ነው። ከብዝሀነት ጋር በተያያዘ ሠራዊቱ ከውስጥም ከውጭም ፈተና ሊገጥመው ይችላል።

የሰራዊታችን ግንባታ የውጭ ስጋትና የውስጥ ስጋት ኃይሎች በተናጠል ወይም በጋራ የሚደቅኑትን ስጋት በተገቢው ሁኔታ ማክሸፍና ማምከን ይሆናል።

የዓባይ ውሀ

ስነዱ የዓባይ ውሀን ውዝግብና ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች ጋር ያለውን አለመግባባት ምናልባትም ሊከሰት የሚችል ጦርነትን ሀገራችን እንዴት ልትወጣው እንደተሰናዳች ፍንጭ ሰጥቷል።
በዚህ የፖሊሲ እይታ የሚቃኘው በአባይ ውሀ አጠቃቀም ዙሪያ የምናካሂደው ድርድርና ውይይት ሉዓላዊ መብታችንንና የሀገራችንን ልማት በማይጎዳ መልኩ የአባይ ወንዝ ላይ የምናካሂደው የልማት ስራ ይጎዳናል የሚሉ የታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች አሉን የሚሏቸውን ቅሬታዎች እንዲያነሱና ጉዳዩን በውይይትና በድርድር ለመፍታት በሙሉ ቁርጠኝነት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንገኛለን።
የሠራዊቱ ዋና ትኩረት ጦርነትን ማስቀረት ይሆናል። ሁሉም የግጭትና አለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች ተሟጠው ጦርነት አይቀሬ ሲሆን ብቻ በሚደረገው ፍልሚያ የመከላከያ ኃይላችን ጦርነቱን በአጭር ጊዜና ባነሰ ዋጋ በአሸናፊነት እንድናጠናቅቅ የሚያስችለን ብቃትና ዝግጁነት እንዲኖረው ይደረጋል።

ስነዱ በመግቢያው ላይም
በመሆኑም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችንን የመጠቀም ሕጋዊና ሉዐላዊ መብታችንን ለመገደብ የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት የጥምዘዛ ስልቶችን ለመመከት የሚያስችሉ የዲፕሎማሲና ወታደራዊ አቅም፣ ዝግጁነት እንዲሁም ቁርጠኝነት መኖሩን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም። ሲል ዋስትና ለመስጠት ሞክሯል።

ተጠባባቂ ጦር

የሰው ሀይል ልማትን፣ የሰራዊት ምልመላን በተመለከተም ሀገራችን ያላትን ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ና የወጣት ቁጥር ታሳቢ ያደረገ ግንባታ ይከናወናል። ሀገሪቱ ተጠባባቂ ጦርም ይኖራታል።

ቴክኖሎጂ
ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ማህበረዊ የተስስር አውዶች ያላቸውን በጎ ድርሻ ዕውቅና የሰጠው ሰነዱ እነዚህ የማህበራዊ ት ስ ስር መድረኮች የጥቃት መሳሪያ ሆነው የሀገር ደህንነትንና ሉዓላዊነትን ሊፈታተኑ ስለሚችሉ በዘርፉ ዘመኑን የሚመጥን ዝግጅት መድረግ እንደሚገባ ያብራራል።


የተጋረጠብን አደጋ በሚል ሲያብራራም

ዓለም አቀፉ የሳይበር መረጃ ትስስር መረብ ሀገራዊ የፖለቲካ ቅራኔዎችን በማጦዝ ብሔርና ሀይማኖትን መሰረት የሚያደርጉ የእርስ በእርስ ግጭቶችን ለመፍጠር ለሚፈልጉ የጥፋት ኃይሎች አስቻይ መሳሪያ ሆኗል። ብዝሃነታችንንና ፌደራላዊ ሥርዓታችንን ወደ ተጋላጭነት መቀየር ለሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ዓይነተኛ የመረጃ ጦርነት አቅም የፈጠረው የመረጃ ቴክኖሎጂ የትርምስ አጀንዳቸውን መቀስቀሻና ማስፈፀሚያ መሳሪያ በቀላሉና በነጻ እንዲያገኙ አስችሏል

[ዋዜማ ራዲዮ]

To reach Wazema Radio Editors – wazemaradio@gmail.com