Sheik Mohammed – FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የረጅም ዘመን የሚድሮክ ኩባንያዎች አንዱ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አብነት ገብረመስቀል 13 ሚሊየን ብር ደሞዝ ያለአግባብ ወስደዋል በሚል በሼህ መሀመድ አላሙዲን ክስ ቀርቦባቸው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ። 

የዋዜማ ሪፖርተር እንደዘገበችው አቶ አብነት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ከውል ውጪ ያሉ ጉዳዩች ችሎት ቀርበው በቀረበባቸው ክስ ዙሪያ ምላሽ ሰጥተዋል። 

በተከሰሱበት መዝገብ የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡት አቶ አብነት ገ/ መስቀል  ከከሳሽ ጋር ዝምድና ወይም ፀብ እንዳላቸው በችሎት ተጠይቀው ዝምድና እንደሌላቸው ገልፀው አሁን ላይ ግን የተከሰተ ፀብ አለ ሲሉ አስመዝግበዋል።

በህገ ወጥ መንገድ ደሞዜን እንደወሰድኩ ተደርጎ ለተመሰረተብኝ ክስ ምስክርነት ለመስጠት ነው የመጣሁት ያሉት አቶ አብነት 13 ሚሊዩን ብር የአንድ አመት  ደሞዝ እንዲከፈለኝ ለሂሳብ ክፍል ደብዳቤ ፅፌ ባስገባሁት መሰረት ደሞዜ  ነው የተከፈለኝ ሲሉ ለችሎቱ ተናግረዋል ። 

“ለብዙ አመታት ደሞዝ ሳይከፈለኝ ነበር የምሰራው”  ያሉት አቶ አብነት “ደሞዜ ስንት እንደሆነ የምናውቀው እኔ እና ሼክ መሀመድ አላሙዲን ነን” 

“ሜድሮክ በ 1993 ስራ ሲጀምር እኔ እና አንተ ደሞዝ አንነጋገርም ደሞዝህን እራስህን ወስን ያሉኝ ሼክ አላሙዲን ናቸው። በዚህ መሰረት የራሴን ደሞዝ የወሰንኩት እራሴ ነኝ”  ብለዋል። 

ስለደሞዙ ክፍያ ስምምነት በወረቀት ላይ የተፃፈ የሰነድ ስምምነት ስለመኖሩ የተጠየቁት አቶ አብነት ከ40 ዓመታት ባልንጀራቸው ጋር ስምምነቱ በቃል እንደነበርና እርሳቸውን ሼህ አላሙዲን ብቻ የሚያውቁት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

“የደሞዝ ክፍያውን መጠን የወሰንኩት አስተዳድራቸው የነበሩ 10 ኩባንያዎች የሚሰሩትን ስራ ታሳቢ በማድረግ ነበር። ለረጅም ጊዜ ድርጅቶቹ ስኬታማ እንዲሆኑ ያለደሞዝ በነፃ ሳገለግልም ነበር”  ብለዋል አቶ አብነት።

ለ27 ዓመታት የሚድሮክ አማካሪ የነበሩትና አሁንም ድርጅቱን እያገለገሉ ያሉት አቶ ተክሌ ዳኘው በጉዳዩ ላይ ምስክር ሆነው የቀረቡ ሲሆን አቶ አብነት ባቀረቡትና ሚሊየን ብር እንዲከፈላቸው የሚጠይቀውን ደብዳቤ ለምን ይከፈላቸው ብለው እንደፈረሙ ተጠይቀዋል። አቶ ተክሌ ደብዳቤውን የፈረሙት አቶ አብነትን በማመን እንደሆነ ለችሎቱ ተናግረዋል። 

አቶ ዳኘው ደብዳቤውን እንዲፈርሙ ከሌላ አካል ፈቃድ አግኝተው እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አብነትን በማመን ብቻ ክፍያውን እንዳፀደቁ መስክረዋል።

በጠበቆቻቸው አማካይነት መጥሪያ እንዲደርሳቸው የተደረገው ሼህ መሀመድ አላሙዲን በችሎቱ አልቀረቡም።  

ችሎቱ ጉዳዩን ተመንክቶ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ተጠናቋል። [ዋዜማ ራዲዮ]