“የአሁኒቷ ኢትዮጵያ መቆሚያ ባላ አድዋ እና አብዮቱ ናቸው” ይለናል ይህ በዋዜማ አዘጋጆች የተሰናዳ የአብዮቱ ዝክር ማመላከቻ ፅሁፍ። አስቲ አንብቡት

ዋዜማ- ወሩ የካቲት ነው፤ የደም ወር። ይሄ ታላቅ ወር፣ የኢትዮጵያ ታላላቅ የታሪክ ዕጥፋቶች እና ውልቃቶች ተጠረቃቅመው የታጨቁበት ነው፡፡ ይህች መከረኛ አገር፣ በዚህ ወር ውስጥ የሆነችውን እና ያደረገችውን ስንመለከት፣ ወሩን እንደ አቻዎቹ ሌሎች ወራት ሁሉ እንዲያው ቆጥራ ማለፏ ግራ የሚያጋባ ነውም ይባልለታል፡፡ ከተጠራጠራችሁ ወደ አድዋ ተመልከቱ፤ ከፈላስፋችን አንዱም፣ “የኢትዮጵያውን አድዋ ላይ ማሸነፍ፣ በእግዜሩ የተመረጠ ሕዝብነትን ከእስራኤል ወስደናል ብለው እንደማመናቸው፣ እዛች ተራራ ላይ ያለቁት ይህንን ሰማያዊ ዕውነት ለማስረገጥ ነው” ይለናል፡፡ የሲያድ ባሬ ጎማም ካራማራ ላይ የተነፈሰው እንዲሁ በዚህ ወር ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ‘አካፋው ሚካኤል’ ብላ የጠራችው እና ከገብረ ሕይወት ትውልድ በኋላ የመጣውን አንድ ልሂቅ ጨምሮ ሠላሳ ሺ ኢትዮጵያውያንን ግራዚያኒ የጨፈጨውም በያዝነው ወር ነው። ከአድዋ በመለስ ኢትዮጵያ ትኮራበት ዘንድ አቻ የለውም ከተባለ፣ ከየካቲቱ አብዮት በላይ ያለ አይመስለንም፡፡ ረገጥ ባለ አነጋገር፣ የአሁኒቷ ኢትዮጵያ መቆሚያ ባላ አድዋ እና አብዮቱ ናቸው። 

አዎን! በዚያ ብሉይ አብዮት መቀስቀስ ማግስት፣ የየራሳቸውን እውነት ዘላለማዊ አድርገው ያመኑት የትውልዱ አባላት፣ ተዋድቀው ወድቀዋል፤ ስላንቺ ከፍታ አነሳነው ባሉት አብዮት፣ በደም ባህር ተዘፍቀው፣ አገራቸውንም እስከ አሁን ማገገም ባቃታት ምሁራዊ ድቀት ውስጥ ጥለዋት አልፈዋል። እኛም፣ የጨነገፈ ሕልማቸው፣ የከሸፈ ተስፋቸው ኗሪዎች ሆነናል። የዛሬው ሐሳባዊ ዳሰሳችንም ከአብዮቱ ርዕሰ-ጉዳዮች ሦስቱን በወፍ በረር ማየት ነው። ወደ አብዮቱ መነሾች፣ ሂደቶች እና የክሽፈት ተረኮች ከመሻገራችን በፊት፣ የአብዮቱ ቀዳሚ አዋላጅ የሆነውን የተማሪዎች ንቅናቄ ዳሰስ አድርጎ፣ የማርክሲዝምን ድንገቴ መጥቶ ሄያጂነት ጠቅሶ፣ የዘመኑ ምልክት የሆነውን የዋለልኝን ሃቲት ከየት መጤነት ነካክቶ ማለፍ፣ የዚህኛው ሳምንት ጨዋታችን ሆኗል። 

         አብዮት ልጆቿን በላች!

ተነሡተነሡእንሂድተባባሉ

መንገዱንሲጀምሩ

እርዝማኔውን አያውቁም ነበር።

 እንገስግስ

የሚጠፋ ጊዜ የለንም።

ሕይወት አጭር ናት

ቶሎ ቶሎ እንሂድ

የሚጠብቀን ታላቅና ብሩህ ኅላፊነት

ሳይፈፀምበፊትማረፍየለብንም” (ኃይሌፊዳ-1960 ዓ.ም.)

ያ ትውልድ በተነሳበት ዘመን የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ልክ በሌሎች ብሉይ አብዮቶች በተቀሰቀሰባቸው አገራት የነበሩትን ወደ ሥር-ነቀልተኝነት ሊገፋፉ የሚችሉ ማኀበረ-ፖለቲካዊ ገፊ ምክንያቶችን ተሸክማ ነበር፡፡ በነዚያ አገራት የነበሩ አብዮተኞች ጉዟቸውን ከየዩንቨርሲቲዎቻቸው እንደጀመሩት ሁሉ፣ የኛዎቹም በአንፃራዊነት ነፃ ሊባል ከሚችለው ኃይለ ሥላሴ ዩንቨርሲቲ ጀመሩ፡፡ የአፄው መንግሥት መወርዛት እና ራሱን ለማሻሻል አለመጣር፣ ወጣቶቹን ለግፉዓኑ እንዲቆሙ ገፋቸው፡፡ ከብዙ ትግል በኋላ ያገኙት፣ ጹሑፎችን የመበተን እና በየዓመቱ ይካሄድ እንደነበረው ‘የኮሌጅ ቀን ግጥሞች’ መሰል ከፊል ነፃ ሁነቶች፣ ሰለሞናዊው ሥርዓት ቆምኩበት የሚለውን ትውፊታዊ እሴቶች ከስሩ ለመንደል የሚጥሩ፤ አልፎም አገሪቷ አለኝ ብላ በብካሬ የያዘቻቸውን ትዕምርቶች አበክረው የሚያጠይቁም ነበሩ(ከኢብሳ ጉተማ “ማነው ኢትዮጵያዊ?” እስከ ዮሐንስ አድማሱ ‘እስኪ ተጠየቁ?’ ያሉትን ግጥሞች ልብ ይሏል)። የትውልዱን ዘገባ በማስቀመጥ ቀዳሚ ሥራ ያወጣችው ራንዲ ባልሼቪክ፣ “Halie sellassie’s Students: The Intellectual and Social Background To Revolution” ባለችው መጽሐፏ ይህን ዘመን በስፋት አትታዋለች። ራንዲ እንደምትጠቅሰው፣ እኒኽ መሰሎቹ ግጥሞች እና መጣጥፎች ሥር-ነቀል ሐሳቦች እንዲሰርፁ፣ በመጨረሻም የዚሁ ሐሳብ አፍታቾች መድረኩን ጠቅልለው እንዲይዙት አስችሏል። ሆኖም፣ ተማሪዎቹ ለምን ሥር-ነቀል ሆኑ? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ መላምቶች ሲቀርቡ ከርሟል። በብዙ መጻሕፍት እና ጥናታዊ ወረቀቶች የቀረቡልንን ሰብሰብ እናድርጋቸው ካልን፣ በሁለት ሃቲቶች መጭመቅ የሚቻል ይመስለናል። (ፅሁፉ ከታች ይቀጥላል)

 የመጀመሪያው ሃቲት ‘ዝግመታዊ’ ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ሙግት፣ መዋቅራዊነትን ይዞ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኅልዮትን ይንተራሳል። ሐሳቡን በተደጋጋሚ በመግፋት የሚጠቀሰው ባህሩ ዘውዴ፣ በዋናነት በአፄው ሥርዓት የተከሰተው የኢኮኖሚ ድቀት እና ተያይዞ የመጣው የተማሪዎቹ የሥራ ዕድል እያጡ መሄድ አባባሽ መግፍዔ መሆኑን ይጠቅሳል። ከዚሁ ኢኮኖሚያዊ ተለዋጭ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጭብጥ፣ የአጠቃላይ አገራዊ ሥርዓት ማሻሻያ ዕጦት ነው።

የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያሳየን፣ አስቀድሞ በምንሊክ፣ ለጥቆም በአልጋ ወራሽ ተፈሪ ዘመናት፣ ለዘመናዊ ትምህርት እና ተያይዞ ለሚመጣው የዝመና እሴት የተጋለጡት ቀዳሚዎቹ ዘመናዊ ልሂቃን፣ መጀመሪያ ከኢያሱ ከዚያም ከተፈሪ ጋር በማበር አገሪቷ የጃፓንን ፍኖት ትከተል ዘንድ ታትረዋል። እዚህ ለማውሳት በሚበዙ ምክንያቶች፣ የአፄው “ከተራማጅነት ወደ ወግ አጥባቂነት” መሻገር፣ ሥርዓታዊ ማሻሻያ ለአገሪቷ እንደማይመጥናት እንዲታመን አደረገ፤ አልያም በባህሩ ዘውዴ አገላለፅ “ጊዜው እየነጎደ ሲሄድ፣ ለህመሙ የሚታዘዘው ኪኒን ምሬትም እየጨመረ መጣ”፣ የሚለው የዚህ ሀቲት እና የሃሳቡ ተሟጋቾች ጥቅል መደምደሚያ ነው። 

   የዚህ መላ ምት ግድፈት፣ የ1950ዎቹን እና 60ዎቹን ተጨባጭ ሁነቶች አለመገንዘብ ይመስላል በሚል ጠበቅ ያለ ትችት የሚቀነቀነው ሁለተኛው ሃቲት፣ ‘ጥቅል’ የሚል ስያሜ ልንሰጠው የምንችለው መሟገቻ ነው። ወጣቶቹን ወደ ሥር-ነቀልተኝነት የመራቸው፣ የአገራቸውን ችግር በግራ ዘመሙ ርዕዮት ብቻ ለመተንተን እና ኅልዮቱ የሚለውን መውጫ መንገድ ብቻ ለመከተል ካለ ሃይማኖታዊ መሰል መታመን ነው የሚለው የክርክሩ መሽከርከሪያ ነው። ይህን ሃቲት አብዝቶ የሚይዘው መሳይ ከበደ፣ በተለይም ““Radicalism And Cultural Dislocation In Ethiopia” በሚለው ብዙ አካዳሚያዊ ውዳሴ በተቸረው ድርሳኑ፣ ዘመነኞቹ፣ የአገሪቷ ውጥንቅጥ ቅርፁን ቢቀይርም፣ እነርሱ ግን መፍትሄውን ከፖለቲካዊ ማሻሻያ ወደ አብዮት እንደመሩት ይከራከራል።

የሥር-ነቀልተኝነታቸው መነሾ፣ የችግሮቻችን ጥልቀት ሳይሆን፣ ለአማላዩ ርዕዮት የነበራቸው ቅጣ ያጣ አፍቅሮት ነው የሚለው ተጠቃሹ መደምደሚያ ነው። ሌላይኛው የ’ዝግመታዊው’ ሃቲት ዝንጋዔ፣ የአውራዎቹን አብዮተኞች መደባዊ ከየት መጤነትን ወደ ጎን መግፋቱ ነው። አብዛኛዎቹ አብዮተኞች በጊዜው መካከለኛ መደብ ከሚባለው ማኅበራዊ ክፍል ከመምጣታቸው ባለፈ፣ ከመካከላቸውም በወቅቱ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የትምህርት ደረጃም የነበራቸው እንደሆኑ መዘንጋቱም ሃቲቱን ጉልበት ሳያሳጣው አልቀረም።  

የሆነውም ሆኖ፣ ከላይ በተጠቀሰው ሥራዋ ባልሼቪክ እንደምታነሳው፣ በወቅቱ ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው አዲስ አበባ በደረሱት አፍሪካውያን ተማሪዎች ጭምር ፍዞች ሲባሉ የነበሩት ተማሪዎች፣ እንዲያ ከከሰሷቸው ተማሪዎች በላይ አንድ ዐሥርት እንኳን ሳይሞላ እንዴት የባሰባቸው ሥር ነቀል ሆኖ የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ አሟልተን ለመመለስ ስንሻ፣ ራሱን ‘ክሮኮዳይል’ ብሎ ወደሚጠራው ህቡዕ ቡድን ለመመልከት እንገደዳለን። በእርግጥ ራሳቸው ተማሪዎቹም፣ ያ ፖለቲካዊ ፍዝነት አሳስቧቸው እንደነበረ የሚያሳዩ ምንጮች አሉ። ለማሳያ ያህልም፣ የሰሜን አሜሪካ ተማሪዎች መጽሔት በነበረው ቻሌንጅ ላይ፣ ከአብዮቱ ጥቂት ዓመታት በፊት እንደሚከተለው ፅፈው ነበር፥

      የኢትዮጵያ የተማሩ ወጣቶች በሌሎች አገራት እንዳሉት አቻዎቻቸው ማኅበረሰባዊ ጉዳዮችን አያሰላስሉም፤ታሪካቸው ለኢትዮጵያ መጨነቃቸውን አይናገርም፤ ከዚህይልቅ፣ ራስወዳድነት፣ ጨለምተኝነት እና የንዋይ ፍቅር ዋንኞቹ መገለጫዎቻቸው ሆነዋል።

የአብዮቱ አዋላጅ የሆነውን የተማሪዎቹን ንቅናቄ በቅጡ ያጠኑ እንደሚሉት፣ እነዚያ በ’ክሮኮዳይል’ ሥር ተሰባስበው የነበሩት ተማሪዎች ንቅናቄውን ወደ ጠርዘኝነት ለመግፋት ግዙፍ ድርሻ ነበራቸው። ፕሮፌሰር ባህሩ፣ “The Quest For Socialist Ethiopia” በሚለው የንቅናቄውን ታሪክ እጅጉን በስፋት በተረከበት መጽሐፉ፣ “እንኳንም በሕይወት የሌሉት፣ ያሉትም የማይናገሩለት” ያለው እጅጉን ሚስጥራዊው ቡድን፣ ስንት አባላት እንደነበሩትም ሆነ በቅጡ ምን ሲሰራ እንደነበር፣ ዛሬ በአብዮቱ ሃምሳኛ ዓመት እንኳን ልናውቀው አልተቻለንም። ሆኖም፣ ብርሃነ መስቀል ረዳ እና ዘሩ ክኽሸን እንደዘወሩት ሲነገር ኖሯል።

እንኳንስ በአፍሪካ ደረጃ፣ በዘመኑ ከነበሩ ሥር ነቀልተኛ ንቅናቄዎች አኳያ ከኢራናውያኑ አብዮተኞች ተማሪዎች ጋር ብቻ ይተያያል የሚባልለት የተማሪዎቹ ንቅናቄ፣ ራሳቸውን ሌኒን ለሚለው “የሙሉ ጊዜ አብዮተኝነት” ያስገዙት እኒህ የክሮኮዳይሎቹ ወጣቶች በዘመኑ ባይከሰቱ ኖሮ፣ ምናልባትም ቢያንስ ማርክሲዚም-ሌኒኒዝም ከመጣበት ጊዜ በላይ ሊዘገይ ይችል ነበር የሚለው ደግ መደምደሚያ ይመስላል። ስለምን ቢሉ፣ የእነርሱ መምጣት ኒዊስ ኤንድ ቪዊስ በተሰኘው በአንዱ የተማሪዎቹ ልሳን ከታወጀ በኋላ፣ ዋንኛ ግባቸው ቀሪውን ተማሪ በአዕማድ አፍራሽነት ሥነ-ልቦና የሚገሩ ሕትመቶች የተማሪውን አደባባይ መሙላታቸው ነው። እነሆ በእነዚህ ሕትመቶችም፣ አብዮት ‘የ’ራት ግብዣ’ እንዳልሆነ እና ፊውዳል ያሉትን ሥርዓት ለማውደም አገሪቷን በደም ባህር መዝፈቅ የትውልዱ ጥሪ መሆኑን የሚሰብኩ ብዕሮች የፅሕፈት ተዋስዖውን ሞሉት፤ እንደተሰበከውም ሆነ። (ፅሁፉ ከታች ይቀጥላል)

                        

“ማርክስን የማያውቁት ማርክሲስቶች”?

    የዚያ ዘመኗ ኢትዮጵያ ብሩኽ ልጆች የነበሩት እነዚያ ደመ ሞቃት ወጣቶች፣ ራሳቸውን ጭምር “ፍዝ” ካሉበት አዕምሯዊ ውቅር ወደርየለሽ ወደተሰኙበት ሥር-ነቀልተኝነት ሲሻገሩ፣ ሂደቱን ፈጣን ባቡር ያደረገው ማርክሲዝም መሆኑ ብዙ የተባለበት ነው። ‘አብዮት የደም ግብር ነውን?’ ወዳሰኘው አገራዊ እብደት ሲጣደፉም፣ ከዘመነኞቻቸው ተዉ ባይ እንዴት አልነበረም የምትል፣ በወጋዊዉም ሆነ በኢ-ወጋዊ አብዮቱ ተኮር ጨዋታዎች በለሆሳስ ተንስታ የምታልፍ ርዕሰ-ጉዳይ ዛሬም ትደመጣለች።

በእርግጥ ዘመኑ ‘ዳገት ላይ ሰው ጠፋ’ የሚያስብል እንዳይሆን፣ አንድ ሰው እና አንዲት ነጠላ መጣጥፉ ብቅ ይሉብናል። ሰውየው፣ ከመኢሶን መስራቾች አንዱ ነበር፤ ድርጅቱ በተመሠረተበት ዓመት ጭምር የፕሮፌሰርነት አካዳሚያዊ ማዕረግ የነበረው ባለ ስል ብዕር አብዮተኛ—ሃጎስ ገብረ ኢየሱስ። “በእውነት ለመናገር ጹሑፏ በአብዛኛው ሹሙጣዊ ነች፤ እንደ እኔ ላለ ለለውጥ ላረጀ፣ አዲስ ክርብርብቶሽ መማር እጅጉን ከባድ ነው” በሚል የሚከፍታትን ይችን ጹሑፍ፣ ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዳትደርስ መዳፈን ዕጣዋ የነበረ መምሰሉ፣ የራሳቸው ወቃሽ አልነበራቸውም አስብሏል።

ገና ቀይ እና ነጭ ሽብር እንኳን በወጉ ሳይሸናነፉ፣ በኢትዮጵያ ጥናት መድረክ ላይ ቆሞ፣ “ኢሕአፓ እና መኢሶን፣ ወደ ብሄራዊ ጨለምተኝነት በተቀየረ ብሄራዊ ራስ ጠልነት የተወረሱ ናቸው፤ ለእነርሱ ከማርክሲዝም-ሌኒኒዝም በላይ እንግዳ፣ ከራሷ ከኢትዮጵያ በላይ የሚጠላ ነገር የለም፤ እናም ፀረ-አብዮት እንደሆኑት ሁሉ ፀረ-ኢትዮጵያም ናቸው” ሲል፣ “THE BANKRUPTCY OF THE ETHIOPIAN “LEFT”; MEISON-EPRP, A TWO HEADED HYDRA. A COMMENTARY ON THE IDELOGY AND POLITICS OF NATIONAL NIHILISM” ብሎ በሰየማት ይችው ጹሑፍ እኒህን ሃይለ ቃላት ጽፏል።

የተማሪዎቹን ንቅናቄም ሆነ አብዮቱን አስመልክቶ፣ ላለፉት አምስት ዐሥርታት በወጡት መጻሕፍትም ሆነ ጹሑፎች፣ እጅግ በጥቂቶቹ ብቻ ሊያውም በዋቢ ማጣቀሻ ገጾች ላይ ብቻ ተወስና በቆየችው በዚህች ጹሑፍ፣ “እርስ በእርስ መገዳደላቸው ሳያበቃ፣ አገሪቷንም ሊያጠፏት ሻቱ” ስላላቸው የቀድሞ ጓዶቹ ግራ ዘመምነት እውቀት ሲያነሳም፣ “በእርግጥም ለዓመታት ማርክሳዊ መፈክሮች ቢነበነቡም፣ ንቅናቄው የግራውን ፖለቲካ በቅጡ የማያውቅ፣ ማርክሲዝም-ሌኒኒዝምን እንደ አብዮታዊ ኅልዮት እና የአብዮታዊ ግብር መመሪያነት ቆዳውን ዘልቆ ያልገባበት ነው” የሚል ከበድ ያሉ ሐረጋትን ወርውሯል።

እዚኽች ነጥብ ላይ፣ ከድህረ-አብዮቱ ተጠቃሽ ምሁራኖቻችን መካከል አንዱ የሆነው ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡ ያነሳትን አንዲት ነጥብ እናክልባት። “ማርክሲዝም፣ ቆዳውን ዘልቆ ባልገባበት አገር፣ እንዴት በዛ መልክ ቁጥራቸው የበዛ ማርክሲስት ድርጅቶች ሊኖሩ ቻሉ?” ሲል የታሪከ-ፍልስፍና መምህሩ ይጠይቃል። ከዚህች ጥያቄ ባለፈም፣ የአብዮቱን ግማሽ ክፍለ-ዘመን ስናከብር፣ ለውይይት ማጫሪያ ትሆን ዘንድ አያይዘን ልናክላት የምንችላትን ጥያቄም፣ ደምሴ ፋንታዬ እና ሳሙኤል እንድሪያስ በቅርቡ በጻፏት ኮርኳሪ መጣጥፍ አቀብለውናል። “Marxsim In Ethiopia: Initial Notes and Puzzles” በምትለው ይህች ጹሑፋቸው፣ ምንም እንኳን ማርክሲዝም ከዩንቨርስቲዎቹ ተነስቶ ወደ ሠራተኛም እና መምህራን ማኅበሮቹ መሰል ስብስቦች ቢሻገርም፣ በጥቂት ዐሥርታት ውስጥ፣ እንደ አንድ የማኅበረ-ፖለቲካ መተንተኛ ኅልዮትነት ከኢትዮጵያ ጥናት ውስጥ ብን ብሎ መጥፋቱ፣ መሰል ሂደቶችን ካለፉ ማኅበረሰቦች አኳያ እጅጉን እንግዳ ሁነት ነው ይሉናል።

በ1950ዎቹ አጋማሽ፣ ሉላዊዉን የሥር ነቀልተኝነት ሞገድ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ የዘለቀው ማርክሲዝም፣ በ1960ዎቹ ብቸኛ ገዢ መንፈስ ሆኖ፣ በ1970ዎቹ መጨረሻ ሲሳሳ፣ ከ1970ዎቹ መገባደጂያ ጀምሮ ደግሞ ያልነበረ ያህል ብን ብሎ ጠፍቷል። “Modernity, Eurocentrism, and Radical politics in Ethiopia, 1961-1991” ባለው መጣጥፉ፣ “የኢትዮጵያው ማርክሲዝም ቅፅበታዊ ነው፤ ሲመጣም ሲሄድም በድንገት ነበር” የሚለው ተሻለ፣ አመጣጡ ቅፅበታዊ ቢሆንም፣ አወጣጡም እንዴት እንዲያ ሆነ ለሚለው ጥያቄ ሁለት ምክንያቶችን ያቀብለናል፤ አንደኛው፣ ጊዜ ከወጣቶቹ ጋር አለመኖሩ ነበር፤ የተማሪው ንቅናቄ ማርክሲዝምን በማይጠየቅ ቅድስና ሲቀበል እና አብዮቱ በፈነዳበት መካከል ያለው ጊዜ 10 ዓመት እንኳን አይሞላምም ነበር። በሁለተኝነት ተሻለ የሚያነሳው ደግሞ፣ አገር ቤት የነበረውን የማርክሲዝም ሥነ ጹሑፉ ዕጥረት ነው። 

                            ሐሳቡ የማን ነው? 

በመታደልም ይሁን ባለመታደል፣ አብዮቱ ለዝክርም-ለውዳሴም ሲነሳ፣ ስሙን አለማንሳት ያልተቻለ ሰው ብቅ ይላል-ዋለልኝ መኮንን። ከወጣቱ የግል ሕይወት ማዶ፣ ያች ባለ አምስት ገፅ ጹሑፉ፣ እርሱም እንደፈራው ከአውድ ውጪ ተወስዳ የአሁኗን ኢትዮጵያ በሆነ ልክ ማበጀቷ ላይ የማይስማማ አጥኚ ብዙም የለንም። ለማልኮም ኤክስ ቆመው ያጨበጨቡት እነዋለልኝ፣ የዘመኑ ስመ ጥር አፍሪካዊ ምሁር የነበረውን አሊ ማዙሪን ያደምጡ ዘንድ ዩንቨርሲቲው ፈቀደ። ፕሮፌሰር ማዙሪ ወደ ራስ መኮንን አዳራሽ ሲገቡ፣ በዚያ የነበረውን አብዮታዊ አውድ አያሌው ይማም አቆይቶልናል። በአንዱ የአዳራሹ ጥግ ላይ ግድግዳ ተደግፈው የነበሩት ዋለልኝ እና ማርታ መብራቱ፣ የምስባኩ አስተዋዋቂ ስለ ማዙሪ ሊቅነት መናገር ሲጀምር፣ በፍጥነት ከአስተዋዋቂው ማይክራፎን የነጠቀው ዋለልኝ፣ “ማዙሪ እዚህ የመጣው ሊያስተምረንም፣ ከእኛም ሊማር ነውና፤ የዩንቨርሲቲው ማኅበረሰብ በዚህ ጉዳይ አያገባውም” ሲል አዳራሹ በጭበጨባ እና በፉጨት መነቃነቁን፣ “Yankee, Go Home!” በሚለው የትውስታ ወትዝታ ድርሳኑ አያሌው በኩራት የጠቀሳት ሁነት፣ ብዙም ባትጠቀስም፣ ስለ ሃያ ሰባት ዓመቱ ወጣት ቀጣይ መንገድ ትጠቁመናለች።  

    የዋለልኝ “ON THE QUESTION OF NATIONALITIES IN ETHIOPIA” የተሰኘችው ጹሑፍ በወጣችበት ታገል መጽሔት ላይ፣ የኋላው አዲስ ሕይወት፣ በዋና ስሙ አብርሃም ገብረ እግዚአብሔር፣ “ሕዝብ ወይስ አሕዛብ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ከዋለልኝ ጹሑፍ የማይተናነስ አፄውን አስበርጋጊ መጣጥፍ አውጥቶ ነበር፤ በወቅቱ በፈር ቀዳጅነት ለግራው ሥነ-ጽሑፍ ንባበ ቃላት የአማርኛ ፍቺ ያስቀመጠው አብርሃም፣ “ሕብረተ-ሱታፌ አይሎ በመገኘቱ ለትግላችን መልክ ሆነ። ዱርም መግቢያው ሰዓት ደረሰ። ጥያቄው ይመለስ፤ ያበጠው ይፈንዳ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሎ ነገር የለም።” የሚለውን ሐረግ በእጅ መንሻነት ጠቅሰንለት እንለፍ፤ ግና ታሪክ የፈቀደው የዋለልኝን ነውና ስለጹሑፏ ለዛሬ ዋጋ ያላቸውን ነጥቦች አጣቅሰን እንሻገር።

  የዋለልኝ ጹሑፍ ከወጣች ከአጭር ጊዜያት በኋላ፣ ከአልጄሪያው ቡድን መሪዎች በኩል በዋናነት በብርሃነ መስቀል አማካኝነት ‘ጥላሁን ታከለ’ እና ከሰሜን አሜሪካ ተማሪዎች በኩል ደግሞ እንድሪያስ እሸቴ ‘ቱሙቱ ሌንጮ’ በሚሉ የብዕር ስሞች፣ የብሄር ጥያቄን አስመልክቶ ከዋለልኝ የሰፉ ጹሑፎች ቢወጡም፣ ሊጠቀሱ በሚችሉ እና ግራ በሚያጋቡ ምክንያቶች የዋለልኟ ገዢ ሆና ለዚህ ትውልድ ደርሳለች።

የሆነስ ሆነና፣ ሐሳቡን በብቸኝነት ለ’ርሱ መስጠት የማይሹ ብዙዎች፣ ሐሳቡ ግን የማን ነው? ብለው ሲጠይቁ አምስት ዐሥርት ሞላ። በጓዳም በአደባባይም ለዚህ ጥያቄ ከሚሰጡት ምላሾች መካከል ሁለቱ እስከዛሬ አደባባዩ ላይ ይሽከረከራሉ። አንዱ እና በተለይም በብሄረተኛው ልሂቅ በኩል የሚገፋው፣ ዋለልኝ የብሄር ጭቆናን አሰቃቂ ግዝፈት የተረዳው በአንድ የእስር ቤት ክራሞቱ ነው የሚል ነው። ፒያሳ፣ ሲኒማ አምፒር ፊት ለፊት የነበረውን እና ደርግ ያፈረሰውን የአፄውን ከአንገት በላይ ሃውልት ቀይ ቀለም በመቀባቱ፣ ከተማሪ ጓደኞቹ ጋር የታሰረው አብዱል ሞሃመድ፣ ይህን ነጥብ ያነሳዋል። በዚያ ዕስሩም፣ ከፀሎት ህዝቂያስ እስከ ዘሩ ክኽሸን፣ ከብርሃነ መስቀል ረዳ እስከ ዋለልኝ መኮንን ያሉትን አይነኬ የተማሪዎች ንቅናቄ ስብዕናዎችን ማግኘቱን የሚጠቅስልን አብዱ፣ ለብሄር ጥያቄ “ዋጋ ነበራቸው” ያላቸውን ታደሰ ብሩን እና ማሞ መዘምርንም ማግኘቱን ያስታውሰናል። “እናም…..” ይላል አብዱ፣

ባህሩ ዘውዴ በአርታዒነት ባወጣት “Documenting the Ethiopian student Movement: An Exercise in Oral History” በተሰኘችው አነስተኛ መድበል ውስጥ ባቀረባት ማስታወሻ፣ “እናም፣ ከሜጫ-ቱለማ እና ከባሌ እና ከኤርትራ የመጡት እኒያ እስረኞች፣ የድህረ-ዕስሩ ዋለልኝ ላይ ከባድ ተፅዕኖ አድርገዋል ብዬ አምናለሁ”። “አብዝቶ ይረብሸን ነበር” ስለሚለው የኤርትራ ጥያቄም በስፋት መወያያታቸውን መጥቀሱም፣ ኤርትራውያን ከጀርባው አሉ ሲባል ለከረመው የአደባባይ ሃሜት ከፊል ድጋፍ ከማቀበሉ ባሻገር፣ ሳይንቴው ላይ ቢያንስ አሻራ አላሳረፈም ማለት ሁኔታውን ማቃለል ይመስላል። እንዲህ ቢባልም ቅሉ፣ “ለኦሮሞ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የራስ-ክብርን ያጎናፀፈ” ያለውን የእነ ታደሰ ብሩን የሥዒረ-መንግሥት ሙከራ በዚህችው ጹሑፉ ተጠራጥሮት ማለፉ፣ የወሳጅነት ሙግቱ ገና ተጨማሪ ምንጮች እንደሚፈልግ ይጠቁማል።

ሁለተኛውን የከየት መጤነት ምናልባት ቀድሞ የቀደሰው ዓለም እሸቴ ሳይሆን አልቀረም። ፕሮፌሰር ዓለም፣ “WALELEGN AS ROMAN PROCHAZKA” ባላት የአጭር አጭር መጣጥፍ፣ የተማሪዎቹ ንቅናቄ አብሪ ኮከቡ ከፀረ-ኢትዮጵያዊው ፋሺስት ጸሐፊ ፕሮችስካ፣ “Abyssinia the Powder Barrel” መውሰዱ የቀን ያህል እውነት ሆኖለታል። “ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች፣ ባህሎች እና ቋንቋዎች ያሏቸው ማኅበረሰቦች በአቢሲኒያው ገዢ መደብ በጉልበት ተያዙ እንጂ አንድም የጋርዮሽ ነገር የላቸውም” የሚለውን፣ ዋንኛውን የፕሮችስካን የኋላው የኢጣሊያ ወረራ የቅኝ-ግዛት ዕቅድ መሽከርከሪያ ሐሳብ ወስዶ፣ አስብላታለሁ ላላት አገር አውሏል የሚለው የዓለም እሸቴ ክስ ዛሬም በሌሎች ባለፍ ገደም ሲነሳ ይስተዋላል። እናስ፣ ይህን የሐሳብ ባለቤትነት አታካሮ በቅጡ መፍታት፣ ገፋ ሲል የብሄር ጥያቄውን ራሱን ለማጠየቅ እና የቆመባቸውን አዕማድ ዳግም ለመፈተሽ፤ አለፍ ሲልም፣ የሃምሳ ዓመታት ጉዟችንን ለመገምገም አንዳች ረብ አይኖረው ይሆን?

ይችን መጣጥፍ አስመልክቶ ሁለት መምህራን የነገሩንን ጠቅሰን እንውረድ። መሳይ ከበደ፣  የዋለልኝን ሃቲት የወቅቱ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ይሰማቸው ነበር ከሚለው፣ የቋንቋ ዝምድና ካላቸው ጨቋኙ ገዢ መደብ ጋር በተገናኘ፣ ነበረባቸው ከሚለው የጥፋተኝነት ስሜት ጋር ያያይዘዋል፤ ይህን ርዕሰ ጉዳይ በስፋት በተነተነባቸው ከላይ በጠቀስነው የመጽሐፉ ገጾችም፣ ለዚያ መደብ ብካይ ሲል ዋለልኝ ያደረገው ምንም ሳይሆን ንስሐ ነው ይለናል።

ዋለልኝን፣ ከፀረ-ባርነት ተሟጓቹ ጋር አስተያይቶ ጆን ብራውን ብሎ የሚጠራው ተሻለ በበኩሉ፣ ያችን ጹሑፍ አስመልክቶ ሁለት ዋጋ ያላቸውን ጥያቄዎች ወርውሮልናል፤ እንደ ብሄር ዘለል ጀግና አማራ ያልሆኑትን እንደራሱ አይቶ ለፍትሕ እና ርትዕ ጮኸ? ወይስ የወቅቱን የአማራ ገዢ መደብ ጭቆና፣ በዚሁ ገዢ መደብ እና በሰፊው ተጨቋኝ የአማራ ገበሬ መካከል ያለው የተጨቋኝ-ጨቋኝ ግንኙነት ቅጥያ፣ በተራዛሚውም የአንዱ ነፃነት ካለአንደኛው ነፃነት ትግሉ ሁሉ ከንቱ እንደሆነ አድርጎ ተረዳው ይሆን? የሚሉት ኮርኳሪ ጥያቄዎች፣ ለአብዮቱ የወርቅ ኢዮቤሊዮ ዝክር መተከዢያ ቢሆኑ አንዳች ዋጋ ሳይኖራቸው አይቀርም።     

ከግማሽ ዐሥርት በኋላ ያችን አጭር መጣጥፍ መለስ ብሎ ለተመለከተ፣ ኢትዮጵያ የብሄር ጭቆና አንገቷን አንቆ ሊገድላት ደርሳ የነበረች ብትሆንም ቅሉ፣ “የትኛውም ብሄር በኢኮኖሚም ሆነ በባህል የትኛውንም ብሄር የማይጫንበት” ያለውን፣ ኹሉን አካታች ‘ሶሻሊስት’ አገረ-መንግሥት ይህን ጭቆና ማቆሚያ ብቸኛ መንገድ ነው የሚለው አንዱ ወዲኽ የሚመዘዝ ሐሳብ መሆኑን ልብ ሊል ይችላል። ‘የትኞቹም ነፃ አውጪ ነን ባይ ንቅናቄዎች ሶሻሊስት ነን ስላሉ መደገፍ፣ ተገንጣይም ነን ብለው ስላወጁ መራገም አይስፈልግም’ የሚለውም፣ ለአሁን እንዲሆነን አናጥቀን ልንወስደው የምንችለው የመጣጥፉ ሁለተኛው ፍሬ ነገር ሳይሆን አልቀረም። 

                           “Salute”

 ማርክሳዊ ባይሆንም ቅሉ፣ ከሁለቱ የግራ ንቅናቄዎቹ አዕማድ አንዱ የነበረው የመሬት ላራሹ ጥያቄ፣ ‘ሃዲዱን የሳተ ባቡር’ ለመሆኑ፣ ገበሬው ከባላባት ጭሰኝነት ወደ መንግሥታዊ ጭሰኝነት መሻገሩ ህልው ምስክር ነው። የቅራኔው ቅድምና የመደብ ወይስ የብሄር የሚለው በቅጡ እንኳን ሳይፈታ፤ የብሄር የተባለውን ቅራኔ አስመልክቶ፣ ጥያቄው የቅኝ ግዛት ወይስ በኢትዮጵያ አገረ-መንግሥት ስር የሚፈታ የብሄር ጭቆና ወደሚሉ ክፍልፋዮች ተከፋፈለ።

ከዚያ ባለፈም ጥያቄው፣ ‘መገንጠልን መደገፍ በራሱ የመገንጠል እንቅስቃሴዎችን ያረግባል’ ከሚለው የእነ ‘ጥላሁን ታከለ’ ርዕይ አፈንግጦ እየሄድንበት መሆናችንን፣ የዚሁ ትውልድ አባላት መመስከራቸውም የትውልዱን ጥልቅ ሽንፈት ከመመስከር የሚዘል አይመስልም፡፡

በአንዱ መጽሔታቸው ላይ፣ “አገራችንን ከረዥም እንቅልፏ መቀስቀስ እና ሕዝቧን ከጠንካራው የፊውዳል ሸምቀቆ ማላቀቅ ትከሻችን ላይ የተጣለ ሸክም ነው”ብለው የፃፉት እነዚህ አብዮተኞች፣ በአፍሪካ ብቸኛ ተብሎ የተወደሰውን ማኀበራዊ አብዮት ቀሰቀሱ፤ የሆነውም ሆነ፡፡ መሬት ላራሹ እና የብሄሮች እኩልነት ይረጋገጥ መሰል ውብ ሐሳቦችን ያነገበው ትውልድ፣ እነዚህን ዕሴቶች እውን ለማድረግ በሄደበት መንገድ ራሱንም፣ አገሩንም አወደመ፤ ረዥሙ ጉዞም በአጭር ተቀጨ።

ከትውልዱ አንፀባራቂ ኮከቦች መካከል አንዱ የሆነው እሸቱ ጮሌ፣ ከአብዮቱ ሃያ ዓመታት በኋላ “ጩኸት” በሚል ርዕስ ለወጣው የወዳጁ ፈቃደ አዘዘ የግጥም መድበል(በዚያች አነስተኛ መድበል ውስጥ፣ “ኝ!ኝ!ኝ!-ለአብዮተኛ ምሁራን” የምትል ሸንቋጭ ግጥሙንም ያስታውሷል) መግቢያ ሲፅፍ፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ትውልድ ነበረ፣ ውብ ህልም ያለመ፤ ታሪክ ሳይፈቅድ ቀረና ያ ህልም ወደ አስከፊ ቅዠት ተቀየረ፡፡ ያም ትውልድ በአመዛኙ የመስዋዕትነት፣ እንዲሁም የትራጄዲ ታሪክ ፅፎ ተነነ፡፡ እርስ በእርሱ ተላለቀ፤ ራሱንም ለኢትዮጵያ አጥፊዎች አመቻችቶ ሰጠ፤ መስዋዕትነቱም ከፍሬ-አልባነት አልፎ እጅግ መራራ ፍሬ አበቀለ” ያለበት አንቀፅ ሙሉ ታሪኩን ይጠቀልልናል፡፡

 ጅማሯችንን በአንደኛው ግዙፍ አብዮተኛ እንዳደረግነው ሁሉ፤ ስንብታችንንም፣ ራሳቸው ራሳቸውን ይሰናበቱ ዘንድ፣ ጥቂት ስንኞቹ እንጂ ስሙ ባልደረሰን ሌላ አብዮተኛ እንሰናበታቸው፤

“Salute the dead 

Because they died; 

Salute the dead 

For they made living possible; 

Salute the ones, 

Who have given life to the future, 

By becoming the past.” 

Surely, salute to you comrades! Salute!

***(ተጠቃሾቹ በአንቱታ ያልተጠሩት ፣ ‘አንቱታ የፊውዳል ነውና አብዮተኛ በአንተ ነው የሚጠራው’ በሚለው ብሂላቸው ምሪት ነው) 

*ክቡራት/ን የዋዜማ ሰዎች የማምሻ ዕድሜውን በካናዳዋ በረዷማ ከተማ ብትህውና መሰል ሕይወቱን ስለገፋው ሃጎስ ገ/ኢየሱስ ዘርዘር ያለ ሁነኛ መረጃዎች ያሏችሁ በዚህ አድራሻችን ብታቀብሉን ምስጋናችን ብዙ ነው። wazemaradio@gmail.com