ዋዜማ ራዲዮ- የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ተፈጽሟል ባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስቸኳይ እንዲወያይ እና አቋም እንዲይዝ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

አብን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥታቸው ለምን የአማራ ብሄር ተወላጆችን ጭፍጨፋ ማስቆም እና ጭፍጨፋውን ተከትሎ ለተፈናቀሉ በርካታ ነዋሪዎች ድጋፍ ማድረስ እንዳልቻለ ለምክር ቤቱ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ ምክር ቤቱ እንዲጠራቸው ጭምር ጠይቋል።

አብን ከዚህ በተጨማሪ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ በተለያዩ ክልሎች ሲፈጸሙ ቆይተዋል ያላቸው የዘር ፍጅቶች እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ወደለየለት አጠቃላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከመሸጋገራቸው በፊት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገሪቱ የዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል ብሄራዊ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና አሠራር ተግባር ላይ በማዋል ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አድርጓል።

አብን በዚሁ መግለጫው የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ የአብን ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ ምክር ቤቱ እንዲይዝላቸው ከቀናት በፊት በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ያቀረቡትን “የአማራ ብሄር የዘር ማጥፋት ወንጀል” የሚመለከት አጣዳፊ አጀንዳ ውድቅ ማድረጋቸው፣ የምክር ቤቱን ሕግ እና ደንብ የጣሰ ውሳኔ ነው በማለት ኮንኖታል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራር እና ስነ ምግባር ደንብ መሠረት፣ አፈ ጉባዔው ቀደም ብሎ በአጀንዳነት ያልተያዘ አስቸኳይ እና አጣዳፊ አጀንዳ ከአንድ የምክር ቤት አባል ወይም አባላት ጥያቄ ሲቀርብላቸው፣ የምክር ቤቱ የዕለት መወያያ አጀንዳ እንዲሆን የመፍቀድ ሙሉ ሥልጣን እንዳላቸው አብን አብራርቷል።

አብን ጨምሮም ተወካዩ ደሳለኝ ጫኔ ለምክር ቤቱ ያቀረቡትን አጣዳፊ አጀንዳ አፈ ጉባዔ ታገሠ ውድቅ ካደረጉት በኋላ ምክር ቤቱ በሰጠው መግለጫ፣ የአብንን የአጀንዳ ይያዝልኝ ጥያቄ “የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ” ብሎ በመግለጽ በአማራ ብሄር ጅምላ ጭፍጨፋ ላይ ተሳልቋል ሲል ከሷል።

አብን በዚሁ መግለጫው አፈ ጉባዔ ታገሠ “የዘር ማጥፋት ወንጀሉን” ከሌሎች በመንግሥት የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ከተነሱ ቅሬታዎች ጋር የምክር ቤቱ የማኅበራዊ፣ ጤና፣ ባሕል እና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ እንዲያጣራው የሰጡት ትዕዛዝ፣ ቀነ ገደብ ያልተቀመጠለት፣ እጅግ የዘገየ እና የተፈጸመውን ወንጀሉዞል ፈጽሞ የማይመጥን ነው በማለት ተችቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]