ዋዜማ ራዲዮ- በውሀ ስራዎች ኮንስትራክሽን ሀላፊዎች ላይ አቃቤ ህግ በሙሰና አዋጅ ላይ በሌለ አንቀፅ መክሰሱን ተከትሎ ክሱን እንዲያሻሽል ብይን ተሰጠ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቀድሞ የውሀ ስራዎች ኮንስትራክሽን መስሪያ ቤት ሀላፊዎች ላይ ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓም የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቶ ነበር፡፡

ክሱን ለማቋቋምም ተላለፏቸው ያላቸውን ድንጋጌዎችም ከወንጀል ህጉ እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ ከወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 በማጣቀስ አቅርቦ ነበር፡፡

ሆኖም ተከሰሾች የመጀመርያ ደረጃ መቃወምያቸውን በተናጠል ባቀረቡበት ወቅት ድንጋጌው እና ክሱ ካለመጣጣሙ ባለፈ ንዑስ አንቀፆቹ በአዋጁ ላይ ስላለመገኘታቸው ገልፀው ነበር፡፡

በክሱ የውሀ ስራዎች ኮንስትራክሽን የቀድሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አታክልቲ ተካ፣የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘውዱ ጌታቸው፣ የግዥ ንዑስ ስራ ሂደት ሀላፊው አቶ አንተነህ እንቻለው፣ እንዲሁም የኮርፖሬት ፋይናንስ ሀላፊው ታከለ ጉተታ ናቸው የተካተቱት፡፡

አቃቤ ህገ በዚህ መዝገብ 2 ክሶች ሲሆን መሰረተው የመጀመርያው በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ነው፡፡

ተከሳሾቹ የማይገባ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የኢትዮጵያ ኮንትራክሽን ስራዎች ድርጅት ቀድሞ የውሀ ስራዎች ኮንስትራክሽንነ ድርጅት በነበረበት ወቅት

ረብ፣ መገጭ፣ከሰም፣ተንዳሆ እና ጊዳቦ ለተባሉ የግድብ እና መስኖ ግንባታ ስራዎች እንዲሁም ለሞጆ ደረቅ ወደብ ግንባታ የግዥ ፍላጎት ሳይቀርብ የአርማታ ብረቶች እንዲገዙ አድርገዋል ሲል ነበር አቃቤ ህግ በክሶቹ ያብራራው፡፡

የተለያዩ መጠን ያላቸው እንዚህ ብረቶች እንደ ጉና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ካሉ የተለያዩ የሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ነበር የተገዙት፡፡

ነገር ግን በተለይ የመገጭ እና የጊዳባ ግድቦች ላይ የሚሰሩ አማካሪዎች በዲዛይን ብልሽት ምክኒያት ግንባታው ላይቀጥል እንደሚችል ስጋት እንዳለባቸው በደብዳቤ መግለፃቸው እየታወቀ ግዥዎቹ እንደፀደቁ አቃቤ ህግ ጠቅሷል፡፡

በተለይ በመጀመርያው ክስ የግዥ ፍላጎት ላልቀረበባቸው ለእነዚህ ብረቶች ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ ተከፍሎ ግዥ ተፈፅሟል ብሏል፡፡

አክሎም እነዚህ ብረቶች በ2008 ዓም የንብረት ቆጠራ ሲደረግ ያለ አገልግሎት ተከማችተው በመገኘታቸው በመንግስት ላይ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል ብሎ ነበር አቃቤ ህግ፡፡

እነዚህን ክሶች ለማጠናከርም በመጀመርያው ክስ በ1996 ዓም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 1(ሀ) እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 11(1) ሐ እና 2 ስር የተመለከተውን ተላልፈዋል ሲል ነው ያጣቀሰው ፡፡

ሆኖም ግን የሙስና ወንጀል አዋጁ ላይ የተጠቀሰው አንቀፅ 11 ንዑስ ቁጥር 1 ሐ የለውም ልክ እንደዚሁ በሁለተኛውም ክስ የአዋጁ አንቀፅ 407 የጠቀሰ ቢሆንም አዋጁ ላይ 407 የሚል አንቀፅ የለም፡፡

እናም ይህን ምክኒያት በመግለፅ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ትክክለኛዎቹን ድንጋጌዎች ጠቅሰህ አሻሽል ሲል አቃቤ ህግን አዟል፡፡

አቃቤ ህግ በኮምፒውተር ፅሁፍ ስህተት የተከሰተ መሆኑን ለዳኞች ለማስረዳት የሞከረ ሲሆን እዚሁ በችሎት ላስተካክል ቢልም ችሎቱ የህግ ድንጋጌ ስህተት በእንዲህ አግባብ የሚስተካከል አይደለም ብሏል፡፡

እናም በብይኑ መሰረት ከ1 ሳምንት በኋላ ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡