PM Abiy and President Al Sisi-FILE

ዋዜማ – በግብፅና በኢትዮጵያን ግንኙነት ላይ አዲስ አቅጣጫ ሊፈጥር የሚችል የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር ድርድር እየተካሄደ ነው። የዚህ ድርድር ስኬትም ሆነ መፋረስ በግብፅ መንግስት ትልቅ ትርጉም ተሰጥቶታል። 

ግብፅ በዚህ ድርድር ህጋዊ አስገዳጅነት ያለው ስምምነት እንዲደረስ  በእጅጉ አሰላስላ የተዘጋጀችበትን አቋም ይዛ መጥታለች። ግብፅ ባለፉት ስምንት ዓመታት ድርድር ማሳካት የፈለገቻቸውን ጥቅሞቿን ማሳካት አልቻለችም። በዚህም ሳቢያ የግብፅ መንግስት የበረታ የህዝብ ግፊት አለበት። 

ግብፅ ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ (የዓባይ ወንዝ) አጠቃቀም ዙሪያ በቅርቡ በአዲስ መልክ የጀመሩትን ድርድር ሁለተኛ ዙር ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄዱ ነው። 

የመጀመሪያው ድርድር በግብፅ ካይሮ ከሶስት ሳምንታት በፊት ተካሂዶ ነበር። 

በማናቸውም መንገድ የግብፅ ጥቅሞች እንዲከበሩ ካይሮ የአረብ ሊግና የምዕራቡ ዓለም ወዳጆቿን ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲያደርጉ ስትወተውት ቆይታለች። 

በቅርቡ በአሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳማህ ሽኩሪ የህዳሴው ግድብን ያህል የደህንነትና የህልውና አደጋ የደቀነብን ጉዳይ የለም ሲሉ ለአሜሪካው አቻቸው ተናግረዋል። 

ሽኩሪ ቅዳሜ ዕለት በተባበሩት መንግስታት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግርም ኢትዮጵያ የመቶ ሚሊየን ግብፃውያንን የመኖር ህልውና እንድትወስን ሊፈቀድላት አይገባም ብለዋል።

የግብፅ ወታደራዊና የደህንነት ባለስልጣናትም የፕሬዝዳንት አብዱልፈታ ኤልሲሲ አስተዳደር የግድቡን ጉዳይ የያዘበት መንገድ ጉድለቶች ነበሩበት፣ አሁን የበለጠ የተወሳሰበ ሆኗል የሚል ግምገማ እንዳላቸው የግብፅ ጋዜጦች ፅፈዋል። 

የኢትዮጵያ የሱዳንና የግብፅ መሪዎች ከመጋረጃ ጀርባ በተባበሪት አረብ ዔምሬትስ አመቻችነት ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ሙከራዎች ሲደረጉ ነበር። አሁንም ግብፅ የምትፈልገውን ዝቅተኛ ግብ እንኳን ማሳካት አልቻለችም። 

የድርድሩ ወሳኝ ምዕራፍ ፤ ግብፅ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም አጥብቃ ትሻለች።

ይህ አስገዳጅ ስምምነት ማለት  ለኢትዮጵያስ  ምን ማለት ነው? 

ግብጽ ከድርድሩ የምትፈልገው የህዳሴው ግድብ በቀጣይ ሲሞላ እና በረጅም ጊዜ ግድቡ ስራውን ሲያከናውን ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ ቢከሰት እንኳ ለግብጽ የሚለቀቅ ቋሚ መጠን ያለው ውሀ በአስገዳጅነት እንዲለቀቅላት ስምምነት እንዲፈረምላት ነው። 

ኢትዮጵያ ግን እንዲህ አይነቱን ስምምነት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳትሆን ቆይታለች። ያለመቀበሏ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በቁጥር በተቀመጠ መጠን ድርቅ ሲከሰት ውሀ እለቃለሁ ብሎ አስገዳጅ ውል መፈረም ለግብጽ ውሀ ድርሻ አለምአቀፍ እውቅናን እንደመስጠት ያስቆጥራል የሚል አቋምን ስለያዘች ነው።

ድርቅ ሲከሰት አስገዳጅ የውሀ መልቀቅ ስምምነትን መፈረም በተዘዋዋሪ መንገድ ግብጽ እና ሱዳን በ1959 ለፈረሙት ስምምነት እውቅና እንደመስጠት ይቆጠራል። ይህም ብቻ ሳይሆን ድርቅ ሲከሰት እንዲለቀቅ የሚጠበቀው ውሀ አስገዳጅ ስምምነት ከተፈረመበት ድርቅ የማይኖር ከሆነ ኢትዮጵያ የምትለቀው ውሀ ድርቅ አጋጥሟት ከነበረው ጊዜም በላይ እንዲሆን ይጠበቃል።

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በድርቅ ጊዜ ኢትዮጵያ የምትለቀው ውሀ ላይ አስገዳጅ ስምምነት “ትፈርም?”  ወይንስ “አትፈርም?”  የሚለው ጉዳይ ላይ ግራ አጋቢ አቋሞች እየታዩ መሆኑ ተሰምቷል። ዋዜማ እንደሰማችው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል አስገዳጅ ስምምነቱን ከመፈረም አንጻር ሰጥቶ መቀበል በሚል መነሻ ጉዳዩን አለሳልሶ የማየት አዝማሚያ በፖለቲካ አመራሩ በኩል መታየቱን ከቅርብ ምንጮች ስምተናል።። 

እንደሰማነው ከሆነ ለጥቂት አመታት ተግባራዊ የሚሆን ስምምነት ቢፈረም የሚል አስተያየት ያላቸው የመንግስት አካላት አሉ።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ድርቅ እንኳ ቢከሰትባት ለአስር አመታት ተግባራዊ የሚሆን በመጠን የተገለጸ ውሀን ለግብጽ ለመልቀቅ ለመፈረም ፍላጎት ነበራት። ሆኖም ግብጾች የሚፈረምላቸው ስምምነት ያለጊዜ ገደብ እንዲሆን ፈለጉ። አሁን ግን ኢትዮጵያ ግድቡን እውን እያደረገችው መምጣቷ ግልጽ በመሆኑ ግብጾች ለአስር አመታት አይደለም ለጥቂት ወራት የሚቆይ ስምምነትም ቢያገኙ ከመፈረም ወደኋላ አይሉም ሲሉ ተናግረዋል አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ምንጫችን ። 

በቀጣይ አመታት ወደ ህዳሴው ግድቡ የሚገባ ውሀን ታሳቢ ባላደረገ ሁኔታ አስገዳጅ ስምምነት ውስጥ መግባትም ኪሳራው ከፍ ይላል ያሉን ምንጫችን ፣ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት ውስጥ ገብታ የከፋ ድርቅ ገጥሟት እንኳ ውል የገባችውን የውሀ መጠን መልቀቅ ባትችል ለዲፕሎማሲያዊ ጫና ብሎም ለቅጣት ነው የምትዳረገው ብለውናል።

የኢትዮጵያ መንግስት አቋሙን እንዲያለሳልስ በአለማቀፍ አበዳሪ ተቋማትና በምዕራባውያን ሀገራት አሁንም ይፋዊ ባልሆነ መንገድ በብርቱ ጫና ውስጥ ይገኛል። በሀገሪቱ እየተባባሰ የመጣው ግጭት የሀገሪቱ ተጋላጭነትን ከፍ ማድረጉም ኢትዮጵያ አቋሟን ታለሳልስ ይሆናል የሚል ግምት አሳድሯል።

ስለድርድሩ ሂደትና ይዘት ከጠየቅናቸው የድርድር ቡድኑ አባላት አንዱ እንደነገሩን ግን “በኢትዮጵያ በኩል የአቋም ለውጥ የለም ወደፊትም አይኖርም”  ብለውናል። በድርድሩ ጉዳይ ምንም አይነት መግለጫ ለመስጠት ዝግጁ እንዳልሆኑም ነግረውናል። [ዋዜማ]