ዋዜማ ራዲዮ- የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ቀን በባህር ዳር በተከበረው የአድዋ ድል በዓል ላይ “የውጭ ሃይሎች በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባታቸውን ማቆም አለባቸው” በማለት ምእራባውያን ያሏቸው አገሮች በቅርቡ የፌደራሉን መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ልዩ ሃይልን በማስመለከት ያወጡትን መግለጫ ከአድዋ ዘመን ጋራ በማነጻጸር አጣጥለውታል።

ንግግሩ ህወሃትን ከቀድሞ የጣልያን ወራሪ ሃይል ጋር በማነጻጸር የኮነኑበት ነው። አከራካሪ የሆኑትን የአማራና የትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎችን አስመልክተውም “በወልቃይት ጠገዴ የተደርገው ውጊያ የተቀማነውን ማንነታችንን ለማረጋገጥ እንጂ መሬት ለመውረር አይደለም። እኛ ከዚህ በኋላ ነጻ ወጥተናል። ነጻ የወጣ ህዝብ ወደ ባርነት ተመልሶ አይገባም” ብለዋል።

በንግግራቸው ያነሷቸው ዋና ዋና ጭብጦችን እንደሚከተለው አሳጥረን አቅርበነዋል።

  • በማይካድራ ጭፍጨፋ ተካሂዶ፣ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ አስነዋሪ ጥቃት በሕወሓት ተፈፅሞ፣ ምዕራባውያን የአማራ ክልል ወረራ እንደፈፀመ አድርገው ለማቅረብ መሞከራቸው ፍትሐዊነት የጎደለው ነው ብለዋል።
  • ምዕራባውያንን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አንገታችንን ሊያስደፉ ይፈልጋሉ። ሰሞኑን የሆነውም ይኸው ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከዚህ በኋላ ማንም ሃይል የአማራ ክልልንና የአማራ ህዝብን አንገት የማስደፋት ሙከራ ቢያደርግ ራሳችንን ለመከላከል እንገደዳለን ሲሉ ተናግረዋል።
  • “እኛ ከትግራይ ህዝብ ጋር ጠብ የለንም ፣ ጉዳያችን በአማራነታችን ሲያሳድደን ከነበረው ሀይል ጋር ነው ………” ” …….አንድነታችን ለመሸርሸር የሚታገሉ ሀይሎች እንታገላቸዋለን ፣ አማራም ቢሆን” ብለዋል።
  • ” የውጭ ሃይሎች በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባት ማቆም አለባቸው፣በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ትክክለኛውን ነገር ለአለም ለማስረዳት ጊዜው አሁን ነው ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
  • “ወያኔ የፈፀመውን ግፍ ማጋለጥ መቻል አለባቸው።….. በጊዜያዊ ችግር መንበርከክ የለብንም ” በማለት ሀገሪቱ የገጠማት ችግር በዓድዋ ወቅት ከነበረው ፈተና ጋር ይመሳሰላል ብለዋል።

የአዘጋጁ ማስታወሻ— ይህ ዘገባ መጀመሪያ ታትሞ ከወጣ በኋላ ማስተካከያና አርታዖት ተደርጎበታል።