Minster of Trade and Industry Melaku Alebel- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ያለፈውን አንድ ዓመት ሀገራችን ከትግራዩ ጦርነትና ተያይዞ ከተከሰተው ቀስ ጋር ስትታገል ቆይታለች። የኮሮና ወረርሽኝም ትልቅ ሀገራዊና ዓለማቀፍ ፈተና እንደሆነ ቀጥሏል። በዚህ ሁሉ መሀል ሀገሪቱ ከሌላው ዓመት 21 በመቶ ከፍ ያለ የውጪ ንግድ ገቢ አግኝታለች። ለመሆኑ ይህ እድገት እንዴት መጣ ? የኢኮኖሚውን ስኬትስ ያንፀባርቃል? ይህ ዘገባ ጉዳዩን ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ በ2013 በጀት ዓመት 3.6 ቢሊየን ዶላር ከሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ አግኝታለች። ይህ ከ2012 በጀት ዓመት ከተገኘው 2.9 ቢሊየን ዶላር የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ አንጻር ሲታይ የ21.1 በመቶ ዕድገት ያሳያል። ሆኖም ይህን ከላዕላይ ገጹ ብቻ ሲታይ መልካም የሚባል አፈጻጸምን በሙያዊ መነጽር ጠለቅ ብሎ መፈተሽም ግን ተገቢ ነው። ይህም ለመሆኑ የዚህ የወጪ ምርቶች የገቢ ዕድገት ምንጭ ምንድነው? ከየትስ መጣ የሚለው ማየት እጅግ ተገቢ ነው።

ለዚህ ዕድገት መንስኤ አንዱ የአትኩሮት ነጥብ ሊሆን የሚገባዉ በነጠላ የወጪ ምርት ዕድገት ላይ መንጠልጠሉ ነዉ፡፡ ለአብነትም በ2013 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ለዓመታት ሲታይ የነበረውን የማሽቆልቆል ጉዞን ለመግታቷ አጋዥ በመሆን በበጀት ዓመቱ ዕድገት ካስመዘገበችባቸው የወጪ ንግድ ምርቶች አንዱ ስጋና የስጋ ውጤቶች ይገኝበታል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 14 ሺህ 600 ሜትሪክ ቶን ስጋና የስጋ ውጤቶች ወደ ውጭ በመላክ 75.3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቷ ሲሆን ለማነጻጸርም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከስጋና የስጋ ውጤቶች የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ በ2012 በጀት ዓመት ከተገኘው የ67.7 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የ7.9 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለው ታውቋል። ይህም አፈጻጸም በ2013 በጀት ዓመት የተመዘገበ መልካም አፈጻጸም የሚባል ነው።

ሆኖም ይህ ዕድገት በጥልቀት ሊታይ የሚገባዉ እንጂ አደላድሎ የሚያስቀምጥ አይደለም፡፡በ2013 በጀት ዓመት ከስጋ የስጋ ውጤቶች የተገኘው ገቢ ወደ ውጭ የሚላከከው ሸቀጥ መጠን በ17.4 በመቶ በመቀነስ በአንጻሩ የአለም የስጋ የስጋ ውጤቶች ዋጋ በ35.3 በመቶ በመጨመሩ የመጣ ነው።

በእርግጥ ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ ዘርፍ የምታገኘው ገቢ ከፍተኛ መሻሻል እንዲያሳይ ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸው በመንግስት በኩል ይገለጻል፡፡ ይህም መንግስት በወሰዳቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎችና በተግባር የተተረጎሙ ስራዎች አማካኝነት የተገኘ ውጤት እንደሆነ ባለስልጣናቱ ያብራራሉ። ከነዚህ ስራዎች መካከል የውል ምዝገባና አስተዳደር መመሪያ ስርዓት መዘርጋት፣ በህገ ወጥ ንግዱ ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች፣ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር የተፈጠሩ ቋሚ መድረኮች በዘርፉ የተሻለ ስኬት እንዲመዘገብ ማስቻሉን መንግስት ይገልጻል፡፡ ይህ የሚያሳየዉ ዕድገቱ የመጣዉ በዉስጠ-በቅ የምርትና ምርታማነት ማጎልበት መንስኤ ሳይሆን ዘላቂ ባልሆኑ አስተዳደራዊ ቁጥጥሮች መሆኑ ነዉ፡፡

ለዚህ ማስረገጫ የሚሆኑ ተግባራዊ ተሞክሮዎች እንደሚያመለክቱት የሸቀጦች የወጪ ንግድ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ሶስት ቁልፍ ምክንያቶች ዕድገት ሊያሳይ ይችላል።

በሀገር ውስጥ በሚፈጠር የምርትና ምርታማነት ዕድገት ምክንያት ወደውጭ የሚላኩ ሸቀጦች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ ሲያሳይ፣ የአለም የሸቀጦች የወጪ ንግድ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ ሲያሳይ፣ እንዲሁም ሁለቱም በተመሳሳይ ጊዜ ጭማሪ ሲያሳዩ ነዉ፡፡

ለአንድ ሀገር የሸቀጦችን የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ ዋነኛዉ መንገድ ሙሉ በሙሉ በራስ ቁጥጥር ስር ያለዉ ዉስጠ-በቅ አማራጭ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሚገኝ ወደውጭ የሚላኩ የሸቀጦችን መጠን የማሳደግ አማራጭ ነው።

በተቃራኒዉ እንደኢትዮጵያ ያሉ የወጪ ንግዳቸዉ በቀዳሚ የግብርና ምርቶች ላይ የተመሠረተ፣ በዉጭ ንግዳቸዉ ምጣኔ በአለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይም ሆነ በዓለም አቀፉ ገበያ የሸቀጦች የወጪ ንግድ የዋጋ ምጥጥን ሁኔታ ላይ እዚህ ግባ የሚባል ወይም ምንም አይነት ተጽዕኖ ማሳደር ለማይችሉ የዝቅተኛ ምጣኔ-ሃብት ሀገራት የአለም የሸቀጦች ዋጋ ሁኔታን ለማረቅ መሞከር ከቁጥጥር ውጭ ያለና ፍጹም እንደ አማራጭ የማይወሰድ ነው።

የኢትዮጵያ የ2013 በጀት ዓመት የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ አፈጻጸም ሲመረመር በአጠቃላይ ደረጃ የ21.1 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ዕውን ቢሆንም በወቅቱ ወደውጭ የተላከው የሸቀጦች የወጪ ንግድ መጠን በአማካይ በ5.2 በመቶ ቅናሽ አለው። ለአብነት ያህል በ2013 በጀት ዓመት የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የጥራጥሬ እና የስጋና ስጋ ውጤቶች ወጪ ንግድ መጠን በቅደም ተከተል በ59 በመቶ፣ በ39.4 በመቶ እና በ17.4 በመቶ ቅናሽ አሳይተዋል።

በተመሳሳይ ወቅት የአለም የሸቀጦች የወጪ ንግድ ዋጋ በአማካይ በ27.7 በመቶ ዕድገት አሳይተዋል። ለአብነት ያህል በ2013 በጀት ዓመት የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የጥራጥሬ እና የስጋና ስጋ ውጤቶች ወጪ ንግድ መጠን በቅደም ተከተል በ23.6 በመቶ፣ በ64.2 በመቶ እና በ35.3 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል።

የማዕድን ዘርፍ ባለፈው የበጀት ዓመት ባለ በሌለ አቅሙ ተንቀሳቅሶ 682 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር  ለማስገባት የቻለ ዘርፍ ነበር።

ይህም የሚያሳየው በ2012 በጀት ዓመት ወደ ውጭ የተላከውን የሸቀጦች መጠን ማስቀጠል ቢቻል ብቻ ከ2013 በጀት ዓመት ከተመዘገበው የ3.6 ቢሊየን ዶላር የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ በላይ ወይም ወደ 3.9 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ማግኘት ይቻል ነበር።

የ2013 በጀት ዓመት የተመዘገበው የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ ዕድገት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ወደ ውጭ የምንልከውን ምርት መጠን አሳድገን ያመጣነው አፈጻጸም ሳይሆን ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ባለ በዕድል ላይ የተመሰረተ የአለም የሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ መሆኑን ነው።

በአጠቃላይ የ2013 የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ አፈጻጸም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ በማሳደግ ረገድ ልዩ ትርጉም ያለው ቢሆንም ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ያልሆነ አማራጭ እና እንደ ተሟላ እንደስኬት አብነት መሆን የሚችል አይደለም። በወጪ ንግዱ ላይ በመሠረታዊነት ዘላቂ ዕድገት የሚመጣው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ብቻ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]