ዋዜማ~ በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል የጠረፍ ነጋዴዎች የሚያስወጡትና የሚያስገቡት የምርት መጠንና አይነት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሺ የአሜሪካ ዶላር ወይንም ተመጣጣኝ የኢትዮጵያ ብር አልያም ተመጣጣኝ የጅቡቲ ፍራንክ መብለጥ የለበትም ሲል የንግድና ቀጠናዊ ትስስር አስታወቀ ።  

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር  ይህን ያለው በሁለቱ አገራት መካከል በጠረፍ አከባቢዎች በሚከናወን የንግድ ልውውጥ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በመበራከቱና በምጣኔ ሀብቱ ላይ  ያሳደረው አሉታዊ ተፅእኖ ምክንያት ነው።

አዲስ በመጣው የጠረፍ ንግድ የህግ መመርያ መሠረት ” አንድ የጠረፍ ነጋዴ ከአገር ውስጥ ይዞት የወጣውን የወጪ ምርት መጠን ልክ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ግዴታ የተጣለበት” መሆኑን  በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገ/መስቀል ጫላ ተፈርሞ ከወጣ መመርያ ሰነድ ተመልክተናል ።

መመርያው በጠረፍ ንግድ ላይ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን የሚመለከት ሲሆን ፣ ነጋዴዎቹ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ  ከአንድ ሺ የአሜሪካ ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ሸቀጦች ከሸጡ በዚያው ልክ  መንግስት የሚያስፈልጉት ምርቶችን ማስገባት እንደሚጠበቅባቸው ሰነዱ ያመለክታል።

መመርያው እንዲወጣ የተላለፈው ውሳኔ በሁለቱም አገራት በድንበር አከባቢ የሚስተዋለውን ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ለመግታት ያለመ መሆኑን ዋዜማ ካገኘችው መረጃ ተረድታለች ።

በሌላ በኩል የመመርያ ሰነዱ ማውጣት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ኢትዮጵያና ጅቡቲ በሚዋሰኑባቸው አከባቢዎች ያሉ ህዝቦች ከመሀል አገር በቀላሉ ማግኘት የማይችሏቸው መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በጠረፍ ንግድ በኩል እንዲቀርቡላቸው ለማስቻል ነው ።

መመሪያው በኢኮኖሚው ላይ የተጋረጠውን ጫና ከማርገብ ባሻገር በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ያለውን የዋጋ ንረት ከጎረቤት ሀገራት በሚገኝ አማራጭ ጥሬዕቃና ምርት ማረጋጋት የሚቻልበትን ዕድል ለመፍጠር ፍላጎት አለው።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ “የጠረፍ ንግድ ፕሮቶኮል” ስምምነት ተፈራርመው ተግባራዊ ለማድረግ በገቡት ቃል መሠረት፤ በጠረፍ ንግድ ፕሮቶኮል ስምምነት በተቀመጠው አንቀፅ ስድስት መሠረት ተፈራራሚ አገራቱ የጠረፍ ንግድ ማስፈፀምያ “መመርያ” በማውጣት መተግበር እንዳለባቸው ይደነግጋል ።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ” በንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ ቁጥር 395/2009 አንቀፅ 52 በተሰጠው ስልጣን በኩል መመርያውን ተፈፃሚ እንዲሆን ከጅቡቲ መንግስት ጋር  በደረሰው ስምምነት መሠረት የጠረፍ ንግድ ስርአት በአዲሱ በጀት አመት ተግባራዊ አደርጋለሁ” ብሏል።

በአገራቱ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ እንዲላኩ ፍቃድ የተሰጣቸው የምርት አይነቶች ሰባት መሆናቸውን ከመመርያ ሰነዱ መመልከት ችለናል። ከጅቡቲ ወደ አገር ወስጥ እንዲገቡ ፍቃድ ያገኙ ምርቶች ደግሞ ሀያ አምስት የምርት አይነቶች መሆናቸውን አውቀናል።

በጠረፍ ንግድ መመርያ መሠረት ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ  እንዲላኩ ፍቃድ ከተሰጣቸው መካከል የቁም እንስሳትን ጨምሮ የግብርና ውጤት ምርቶችና በድንበር አከባቢዎች የሚመረቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች መሆናቸውን በሰነዱ ተጠቅሷል።

ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ፍቃድ ያገኙ የጠረፍ ንግድ ምርቶች ደግሞ ውስን የግብርና ምርቶች፣ የፋብሪካና ኢንዱስትሪ ውጤት ምርቶች ናቸው ። 

የጠረፍ ነጋዴዎች የጠረፍ ንግድ ምርቶችን ማስወጣትና ማስገባት የሚችሉት በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አገልግሎት የሚሰጥባቸው የድንበር በሮች ሲሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ዱብቲ፣ አፋምቦ፣ ኢሳይታ፣ ኢሊዳኢር፣ አፍዴራ፣ ቆሬ፣ ቢዲ ደንበል፣ ቢዩጉርጉር እና አይሻ የድንበር በሮች መሆናቸውን ተመልክተናል።

በጂቡቲ በኩል የጠረፍ ንግድ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ከጋላፊ እሰከ ዮቦኪ፣ ከጋሊሌ እስከ ኤልሳቤህ፣ ከባልሆ እስከ ዶራ፣ ከቦንዳራ እስከ ዲኪሂል ያሉ አከባቢዎች መሆናቸውን ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር  ሚኒስቴር የወጣ መረጃ ያመለክታል ፡፡

የድንበር ጉምሩክ ኮሚሽን ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የወጪና ገቢ ምርቶች ላይ ስታትስቲክስ ( አሀዛዊ)  ሪፓርት ለኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሚያቀርብ ሲሆን ፣ ኮሚሽኑ ሪፓርቱን መርምሮ ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ለማእከላዊ ባንክ  በማመሰካከርያነት እንደሚቀርብ ዋዜማ ከመመርያው መረዳት ችላለች።[ዋዜማ ]