EHRC Head, Daniel Bekele -FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሰሜን ኢትዮጵያ ከተከሰተው ጦርነትና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በብሄር ማንነት፣ ራስን በራስ ከማስተዳደርና የአካባቢ አስተዳድር ወሰን እንዲሁም አልፎ አልፎ በሃይማኖት ሳቢያ በሚያገረሹ ግጭቶች መጠነ ሰፊ የሆነ የመብት ጥሰት አሁንም መቀጠሉን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ (ዶ/ር) የኮሚሽኑን የአስር ወራት እቅድ አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት  የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግንቦት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ግጭቶች ሳቢያ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ  እጅግ በርካታ ሰዎች ለሞት፣ ለአካልና ለስነ-ልቦና ጉዳት መፈናቀልና ለንብረት ውድመት መዳረጋቸውን፣በመሰረተ ልማት ላይ በደረሰ ውድመትም መሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን በመግለጽ በአጠቃላይ ባለፉት አስር ወራት ከፍተኛና መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አስታውቀዋል፡፡

እጅግ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸመው በግጭትና የጦርነት አውድ ውስጥ በመሆኑ ለሁሉም ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግና በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሰዎችን ሁሉ ደህንነተ የመጠበቅና የማስጠበቅ ግባር ቀደም ሃላፊነት የመንግስት እንደሆነ በመግለጽ ፍትህና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ዋና ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ የሚፈናቀሉና ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኙ በተራዘመ የመፈናቀል (protracted dsiplacemnet) ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ ብዙ ስቃይ እንዳስከተለ ተናግረዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ያማከለ ጥበቃ በመስጠትና ዘላቂ መፍትሄ በማመቻቸት ለችግሩ በአገር አቀፍ ደረጃ በቂ ትኩረት እንዲሰጠውና ብቃት ያለው የህግና ተቋማዊ ማዕቀፍ እንዲበጅለት ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ዋና ኮሚሽነር ዶ.ር ዳንዔል ተጠያቂነትን በማረጋገጥና የህግ የበላይነትን በማስከበር የሰብዓዊ መብቶች ላይ ያለው ቁርጠኝነት እንዲታደስ ምክርቤቱን ጠይቀዋል፡፡ 

ኮሚሽኑ ባለፉት ወራት ባከናወናቸው የክትትልና የምርመራ ስራዎች ላይ ከተስተዋሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ በተለይም በመንግስት የጸጥታ አካላት ከፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያ ፣ ከመጠን ያለፈ የሃይል አጠቃቀም ፣ ከፍርድቤት ትዕዛዝ ውጭ የሚፈጸም የዘፈቀደ እስር ፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስር ፣ በአንዳንድ ቦታዎች ህጻናትን በህገወጥ መንገድ ማሰር፣ ጋዜጠኖች ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች ላይ ያነጣጠረ እስርና አስገድዶ መሰወር፣ በምርጫ ወቅት የተገደሉ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መኖርን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሰብዓዊ መብት መርሆችን ያልተከተለና በተወሰነ መጠን በብሄር ማንነት ላይ ያነጣጠረ የተስፋፋ እስር መፈጸሙን፣ የፍርድቤት ትዕዛዝ  አለመከበርና የዋስትና መብት የተፈቀደላቸውን ሰዎች ጭምር በእስር እንዲቆዩ መዳረጋቸውን፣ በአንዳድ የእስርቤት ቦታዎች ታሳሪዎችን መደብደብና ኢሰብዓዊ የእስርቤተ አያያዝ ሁኔታ በየጊዜው እጅግ  አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን  አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም መንግስትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በሙሉ ለሰብኣዊ መብት መጠበቅና መከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደገና በድጋሜ እንዲያድሱና እንዲተገብሩ ልዩ ትኩረትና ክትትል  እንደሚያሰፈልግ  ዋና ኮሚሽነር ዶ.ር ዳንዔል አስታውቀዋል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትን ትኩረት ይሻል በሚል ያቀረቡት ሌላኛው ጉዳይ በግጭትና ጦርነት ሳቢያ ከተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅና በሀሉም ክልሎች የሚታየው የጸጥታ መደፍረስ ሁኔታ በረካታ ምርታማ የነበሩ አካባቢዎችን መጉዳቱንና የመሰረተ ልማቶች በጦርነቱ መውደማቸውን፣ ከውጭ ምንዛሬ ዕጥረትና በዓለማቀፍ ደረጃ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የአቅርቦት ዕጥረትና የዋጋ ግሽበት መከሰቱ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም በእነዚህ ችግሮች ሳቢያ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች በከፍተኛ መጠን አደጋ ላይ እንደወደቁ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ መንግስት የአገሪቱን አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚ ለማረጋጋትና ለማስተዳደር የሚወስዳቸው ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች እንደተጠበቁ ሆነው እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት  ከዚህ የባሰ እንዳይከፋና በየደረጃው እየተሻሻለ እንዲመጣ ልዩ ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም በማህራዊና ኢኮኖሚያዊ የህዝብ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ዘርፍ ከቀበሌ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ማውጣት ጀምሮ ትምህርትና የጤና አገልግሎት ማግኘት ወይንም የስራ ፈቃድ ማውጣት ወይንም ልዩ ልዩ የመንግስት አገልግሎቶችን ማግኘት በሚያሳዝን ብልሹ አሰራርና በሙስና በመታወኩ እያደገ የመጣ የህዝብ ዕሮሮ እየተሰማ መሆኑንም ለምክርቤት አባላቱ አስረድተዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]