ዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ40 /60 የመኖሪያ ቤት መርሀ ግብር ከጀመረበት ከ2005 ዓ ም ጀምሮ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአንደኛ እና ሁለተኛ ወለል ላይ የሚገኙ ቤቶች ለንግድ ተብለው ተለይተው እና ለንግድ በሚሆን የግንባታ መንገድ ተዘጋጅተው ለከተማዋ ነዋሪዎች በጨረታ ሲቀርቡ ቆይተዋል።
ከሰሞኑ ግን የከተማ አስተዳደሩ በአንዳንድ ሳይቶች የሚገኙ የ40/60 የጋራ የመኖሪያ መንደሮች ውስጥ ለንግድ የተዘጋጁ እና ለጨረታ እንደሚቀርቡ ሲጠበቁ የነበሩ የንግድ ቤቶችን እያፈረሰ በመገንባት ቅርፃቸውን በአፋጣኝ ወደ መኖሪያ ቤት የመቀየር ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ዋዜማ አረጋግጣለች።
በመሪ ሎቄ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መንደር ይህ የንግድ ቤቶችን በፍጥነት ወደ መኖሪያ ቤትነት የመቀየር የግንባታ ሂደት እሁድን ጨምሮ በከፍተኛ ፍጥነት ሲከናወን የዋዜማ ዘጋቢ በስፍራው ተገኝታ ታዝባለች። የመሪ ሎቄ የ40/60 የመኖሪያ መንደር የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በያኔው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር በነበሩት አቶ ጃንጥራር ዓባይና በአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ በነበሩት ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በይፋ ዕጣ ከወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል አንዱ ነው።
ይህ የመኖሪያ መንደር እያንዳንዳቸው 13 ወለል ያላቸው 14 ብሎኮችን ያካተተ ነው። በ2011 የካቲት ወር እጣ የደረሳቸው የዚሁ መንደር የቤት እድለኞች በዘንደሮ አመት የቤታቸውን ቁልፍ ተረክበው ኑሮ ለመጀመር አስፈላጊውን የግንባታ የመጨረሻ ምእራፍ (ፊኒሺንግ) ስራም እያከናወኑ ነው።
በዚሁ መንደር ከሚገኙት ብሎኮች መካከል ለንግድ ስራ የተዘጋጁት ቤቶች በአሁኑ ወቅት ከውስጥ እየተከናወነ በሚገኝ ግንባታ ወደ መኖሪያ ቤት አገልግሎት እየተቀየሩ ስለመሆኑ ነው ዋዜማ ያረጋገጠችው። በዚህ ስራው በሚከናወንባቸው ብሎኮች በአጠቃላይ አስከ 80 የሚደርሱ መኖሪያ ቤቶች ከንግድ ቤት ወደ መኖሪያ ቤትነት እየተቀየሩ ነው። ንግድ ቤቶቹን ወደ መኖሪያ ቤትነት ለመቀየር እየተከናወነ ባለው ስራም ቀድሞ ለንግድ አገልገሎት ታስቦ የተሰራውን ግንባታ በማፍረስ እንደ አዲስ ከህንፃው ውስጠኛ ክፍል ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል።
ንግድ ቤቶቹን ወደ መኖሪያ ቤት የመቀየር አጣዳፊ ስራ በሌሎች የከተማዋ የጋራ መኖሪያ መንደሮች አካባቢዎችም።
በነዚህ የጋራ መኖሪያ መንደሮች የሚገኙ ቤቶች እጣ ከወጣባቸው ከ2 ዓመታት በላይ ተቀጥሮ እያለ እና ቤቶቹ በግልፅ ለንግድ አገልግሎት እንዲውሎ ተደርገው ተሰርተው ሳለ በአፈጣኝ ወደ መኖሪያ ቤትነት የመቀየር ስራው ለምን እንዳስፈለገ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የአዲስ አበባ መስተዳድር ህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎች ምላሽ ለመስጠት አልፈቀዱም። [ዋዜማ ራዲዮ]