Diriba Kuma, Addis Ababa Mayor
Diriba Kuma, Addis Ababa Mayor

በኮልፌ ቀራንዮ የሊዝ ጨረታ ለአንድካሬ 41ሺ ብር ቀረበ

ዋዜማ ራዲዮ- ትናንት ረቡዕና ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ፒያሳ ጊዮርጊስ በሚገኘው ማዘጋጃ ቤት ለመሬት በሚቀርብ ዋጋ ደምቆ ዉሏል፡፡፣ የቴአትርና ባሕል አዳራሽ ሎቢ ዉስጥ የሊዝ ጉድ መሰማት የጀመረው ገና ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ ነበር፡፡ የማክሰኞና የረቡዕ ባለተራ የነበረው ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ሲሆን ለሊዝ ያቀረባቸው 70 ቦታዎች ሁሉንም በዉድ ዋጋ ቸብችቦ 24ኛውን ዙር በኩራት አጠናቋል፡፡

በቁጥር 70 የሚሆኑት ቦታዎች ለጨረታ የቀረቡ ሲሆን ሁሉም ይዞታዎች የሚገኙት በወረዳ 7 እና ወረዳ 3 ዉስጥ ነው፡፡ ወረዳ 7 ለጨረታ የቀረቡት ይዞታዎች በተለምዶ ቤቴል አንፎና አልፋ ሩም የሚባል አካባቢ እንዲሁም ዓለም ባንክ ሰፈር የሚገኙ ኪስ ቦታዎች ነበሩ፡፡

ወረዳ 3 የወጡት ቦታዎች ደግሞ ግራር ሲልጤ ሰፈር አካባቢ በሚል በይበልጥ የታወቃሉ፡፡

ለጨረታ ከቀረቡት 70 ቦታዎች ዉስጥ 27ቱ ብቻ ለመኖርያ ቤት በሚል የቀረቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ለቅይጥ አገልግሎት እንዲዉሉ የታሰቡ ናቸው፡፡ የቦታዎቹ ስፋት በተመለከተም ትንሹ ካሬ 131 ስኩዌር ካሬ ሲሆን የዙሩ ሰፊው ካሬ 417 ስኩዌር የሚሰፋ ነበር፡፡

የዙሩን የዋጋ ክብረወሰን የሰበሩት አቶ ይታያል ዳምጤ የተባሉ ግለሰብ ናቸው፡፡ በኮድ ቁጥር LDR-KOL-MIX-00012057 ለቅይጥ አገልግሎት የቀረበና 152 ስኩዌር ካሬ የሚሰፋን ቦታ ለአንድ ካሬ 41ሺ 167 በመስጠት ቦታዉን በድምሩ በ6 ሚሊዮን 257ሺ 384 ብር የግላቸው አድርገውታል፡፡ ይዞታው የሚገኘው በወረዳ 7 ከከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ሰፈር ዉስጥ ነው፡፡

አቶ ይታያል ይህን ከፍተኛ የተባለን ዋጋ ያቅርቡ እንጂ ጥቂት የማይባሉ ተጫራቾች ያሸነፈበት ዋጋ ከርሳቸው ዋጋ እምብዛምም የራቀ አልነበረም፡፡ እንደ አብነት በዚሁ ቦታ 2ኛ የወጡት ግለሰብ ያቀረቡትን ዋጋ ማየት በቂ ነው፡፡ አቶ እንድሪስ መሐመድ ይባላሉ፡፡ ለቦታው የሰጡት ዋጋም 35ሺ 250 ብር ነበር፡፡ ምናልባት አቶ ይበልጣል ቦታዉን ለመውሰድ ቢያቅማሙ ለጨረታ ማስከበሪያ ያስያዙት ገንዘብ ለመስተዳደሩ ገቢ ሆኖ ለቦታው ሁለተኛውን ትልቁን ዋጋ ያስገቡት አቶ እንድሪስ ቦታዉን አቶ ይበልጣል ባቀረቡት ዋጋ እንዲወስዱ ይጋበዛሉ፡፡ እርሳቸው ቦታዉን ለመውሰድ ፍላጎት ካላሳደሩ ግን ይዞታው ለሌላ ዙር ጨረታ ይቀርባል፡፡ በአዲስ አበባ የመሬት ሊዝ ማስተላልፍ ስርዓት መሠረት አሸናፊዎች ቦታዉን የማይወስዱ ከሆነ 2ኛውን ከፍተኛ ዋጋ ያቀረበ ተወዳዳሪ ቦታውን መውሰድ ይችላል፡፡ ኾኖም ቦታውን መረከብ የሚችለው ባቀረበው ዋጋ ሳይሆን 1ኛ የወጣው ግለሰብ ወይም ድርጅት ባቀረበው ከፍተኛ ዋጋ ነው፡፡

በዚህ ዙር ከቀረቡት ቦታዎች ዘጠኝ የሚሆኑት ለካሬ የቀረበላቸው ዋጋ ከ30ሺ ብር በላይ መሆኑ የአዲስ አበባ መሬት ዋጋ እንደሁልጊዜው እየናረ ለመሆኑ በቂ ማሳያ ሆኗል፡፡ በዚሁ ክፍለ ከተማ 60 የሚሆኑ ይዞታዎች ለካሬ የቀረበላቸው ዋጋ ከ20ሺ እስከ 30ሺ ብር የሚደርስ ነው፡፡ በዙሩ ዝቅተኛ ዋጋ ኾኖ የተመዘገበው አቶ መክብብ ገረመው የተባሉ ግለሰብ በኮድ ቁጥር LDR-KOL-MIX-00012094 ተመዝግቦ ያለ፣ ወረዳ 3 ልዩ ስልጤ ሰፈር የሚገኝ ስፋቱ 265 የሆነ ቦታ ነው፡፡ ለካሬ ያቀረቡት ዋጋም 8ሺ 670 ብር ነው፡፡ አቶ መክብብ በዙሩ ከ10ሺ ብር በታች ዋጋ አቅርበው ያሸነፉ ብቸኛው ተወዳዳሪ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡

የ24ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ ዉጤት መርሐግብር ነገ ነገና ከነገ በስቲያ ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን ነገ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በአቃቂ ቃሊቲ የቀረቡ 20 ቦታዎች ዉጤት ይገለጻል፡፡ ቀጥሎም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የቀረቡ 14 ቦታዎች ዉጤት ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከነገ በስቲያ የሚገለጹ ቦታዎች በጉጉት የሚጠበቁ ናቸው፡፡ በአዲስ ከተማ፣ በልደታና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ለሊዝ የቀረቡ ጥቂት ቦታዎች ዉጤት የፊታችን አርብ ከሰዓት የሚሰማ ሲሆን ምናልባትም በከተማዋ የመሬት ሊዝ ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ ዋጋ ሊቀርብ ይችላል ተብሎ ተፈርቷል፡፡

ይህም ሊሆን የሚችለው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር 6 ቦታዎች ለጨረታ በመቅረባቸው ነው፡፡ ነጋዴው ማኅበረሰብ እነዚህን ቦታዎች በግልም ይሁን ከባለእንጀራ ጋር ጥምረት በመፍጠር የራሱ ሊያደርጋቸው ከፍተኛ ጉጉት እንዳለው በጉብኝት ወቅት የተስተዋለ ጉዳይ ነው፡፡