Photo-FILE
Photo-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የሥርዓቱን መፍረክረክ ተከትሎ በተፈጠረ የአሠራር ክፍተትና ቸልተኝነት በከተማዋ የሚገኙ የገዥው ፓርቲ ታማኝ ካድሬዎች በአዲስ አበባ የማስፋፊያ መንደሮች ቦታ እየተቀራመቱ እንደሚገኝ ዋዜማ ከሁለት ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ባለሞያዎች የደረሳት መረጃ ያሳያል፡፡
ካድሬዎቹ መሬት እየታደላቸው ያለው በዋናነት በተፈናቃይ አርሶ አደር ስም ራሳቸውን በቤተሰብ መልክ እያደራጁ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ በከተማዋ ማስፋፊያ ቦታዎች የልማት ተፈናቃይ አርሶ አደር ስለመሆናቸው የሚያስረዳ የምስክር ወረቀት ያቀረቡ ካድሬዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምትክ መሬት ያለምንም ውጣ ውረድ እያገኙ ነው ተብሏል፡፡ ከወረዳና ከአርሶ አደር ኮሚቴ በሚመጠ ብጣሽ ወረቀቶች 500 ካሬ ስፋት ያለው ቦታ እየተሰጣቸውና ካርታም እየታተመላቸው እንደሆነ የነገሩን ባለሞያዎች ጉዳዩ የአሠራር ክፍተትን ተጠቅሞ የሚካሄድ በአይነቱ ልዩ የሆነ ከፍተኛ የመሬት ቅርምት እንደሆነም አብራርተውልናል፡፡
ቀደም ባለው አሠራር ምትክ ቦታ ማግኘት የሚቻለው የአርሶ አደር ይዞታው በአየር ካርታ ስለመኖሩ ተጣርቶ፣ በልማት ወይም በከተማ መስፋፋት ምክንያት ይዞታውን ማጣቱ ተመሳክሮ፣ በወረዳ ደረጃ የተዋቀረ ኮሚቴ ምስክርነቱን ሰጥቶ፣ በራሳቸው በአርሶ አደሮች የተቋቋመ ማኅበር ማረጋገጫ ሲልክ እንደነበር የሚናገሩት ባለሞያዎች፣ አሁን ያለምንም ማጣራት ከወረዳ በሚመጣ ብጣሽ ወረቀት መሬት እንደልብ እየታደለ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

‹‹እኛ ስለሁኔታው ለማዕከል አሳውቀናል፡፡…ነገር ግን አርሶ አደር እያስቀየማችሁ ሁከት አትፍጠሩብን፣ አስተናግዷቸው ነው የተባልነው›› ይላል የቦሌ ክፍለ ከተማ አንድ የመሬት ባለሞያ፣ ለዋዜማ፡፡ ይህ ትእዛዝ ከየትኛው ሹም እንደመጣ ለመናገር ፍቃደኛ ባይሆንም በአብዛኛው በቃል (በስልክ) የሚሰጥ ትዕዛዝ እንደሆነ ይናገራል፡፡

እኔ ብቻ በአንድ ሳምንት ‹‹በአስቸኳይ ምትክ ቦታ ይሰጣቸው›› የሚል ወረቀት ይዘው ለመጡ አስራ አንድ ‹‹አርሶ አደሮች›› ልኬት ሠርቻለሁ›› የሚለው ይህ ባለሞያ አንዳንዶቹን በስም እንደሚያውቃቸውና በወረዳ ደረጃ በተለያየ ኃላፊነት በካድሬነት የሚሠሩ ቤተሰቦች እንደሆኑ እንደሚያውቅም ጨምሮ አስረድቷል፡፡
‹‹..አዲስ ነገር አይደለም…በአርሶ አደር ስም የሚደረገው ዘረፋ ዓመት አልፎታል፡፡…ቦታ ከወሰዱ በኋላ በግምገማ ተደርሶባቸው በይቅርታ የመለሱ ካድሬዎች አሉ፡፡ እንደ ሰሞኑ ግን ሞቅ ብሎ አያውቅም›› ያለው ደግሞ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባልደረባ የሆነ ወጣት ነው፡፡

ይህ የመሬት ልማት ባለሞያ አሁን ያለው ሁኔታ በ97 ማግስት ከነበረው ክስተት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ይመሰክራል፡፡ ‹‹አንዱ መሬት አገኘ ሲባል ሌላውም ይከተላል፡፡ ኃላፊዎች እያወቁ ዝም ሲሉ የተፈቀደ ነው የሚመስለው፡፡ ዞሮ ዞሮ ነገሩ ሲረጋጋ መታሰራቸው አይቀርም›› ይላል፡፡

እንደ ሁለቱም ባለሞያዎች ትዝብት ከሆነ ‹‹አርሶ አደር አታስከፉ›› መባል የተጀመረው ማስተር ፕላኑን ተከትሎ በኦሮሚያ ከፍተኛ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰበት ማግስት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የካሳና የምትክ ቦታ አሰጣጥ መጠኑ እንደሰሞኑ ባይሆንም ለከፍተኛ ምዝበራ መጋለጡን ይናገራሉ፡፡
በተለይም የኦሮምኛ ተናጋሪ አርሶ አደሮች የከተማ መለጠጥን ተከትሎ ከእርሻቸው መፈናቀላቸው ፖለቲካዊ ጥያቄና አመጽ ከቀሰቀሰ በኋላ ባሉት አመታት ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን መንከባከብና ለሚያነሱት ጥያቄ ፈጣን መፍትሄ መስጠት እንደ አቅጣጫ ተይዞ ቆይቷል፡፡
በዚህም መሠረት ቀደም ሲል ለማሳ፣ ለግጦሽ መሬት፣ ለባሕር ዛፍ፣ ለደረሰ ሰብል፣ ለጓሮ ተክል ወዘተ ከሚሰጠው ካሳ በተጨማሪ ለይዞታ በካሬ 3 ብር ብቻ ይከፈል የነበረው አሁን በካሬ ወደ 51 ብር እንዲያድግላቸው ተወስኗል፡፡ ለአርሶ አደር ቤት በምትክ ከፍተኛው ክፍያ ሁለት መቶ ሺ ብር የነበረው ከተቃውሞ በኋላ ዝቅተኛው ክፍያ ወደ 581ሺህ ብር ከፍ መደረጉንም ባለሞያዎቹ ያወሳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር አርሶ አደሩ ቀደም ሲል በነበረው የቤተሰብ ልክ እየታየ ከ200 እስከ 300 ካሬ ቦታ ምትክ ይሰጠው የነበረው፣ አሁን ትንሹ የምትክ ቤት መሥሪያ ቦታ 500 ካሬ እንዲሆን እንደተደረገና ይህም ተቃውሞው ተከትሎ የመጣ የካቢኔ አስቸኳይ ውሳኔ መሆኑን ያወሳሉ፡፡
ከዚህም አልፎ ተርፎ ከአመጹ በፊት የአርሶ አደር ልጅ መሬት ያገኝ የነበረው እድሜው ከ18 ዓመት በላይ ከሆነና ባለትዳር መሆኑን የሚመሰክር መረጃ ሲያቀርብ፣ እንዲሁም ከወላጆቹ ጋር አብሮ መኖሩ በወረዳ ሲረጋገጥ ብቻ እንደነበር፤ ኾኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለየትኛውም አባወራ አርሶ አደር ‹‹ልጆቼ ለሚላቸው በሙሉ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ እስከሆነ ድረስ ለእያንዳንዳቸው 150 ካሬ በተናጥል ስጡ›› ተብለናል ይላል የኮልፌ ቀራንዮ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ባልደረባ፡፡ እነዚህን የአሰራር ክፍተቶች ተከትሎ ምዝበራ እንደተጀመረና ይህም በኢህአዴግ የክፍለ ከተማ ግምገማ ሳይነሳ የቀረበት ጊዜ እንዳልነበረም ያብራራል፡፡

በተለይም ምትክ ለመስጠት የአየር ካርታ ማመሳከር ከቀረ ወዲህ በርካታ ካድሬዎች ‹‹አርሶ አደር ነን›› እያሉ የአርሶ አደር ደብዳቤና የምስክር ወረቀት እያሰሩ በራሳቸውና በልጆቻቸው ስም መሬት እንደጉድ እየተቀራመቱ መሆኑንም ያብራራል፡፡ ‹‹አንዳንዶቹ በግምገማ ቢደረስባቸውም በይቅርታ ይታለፋሉ፡፡ ካርታቸው እንዲመክን የሚደረገው ግን ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው›› ይላል ይኸው ባለሞያ፡፡ ‹‹ታስረው የተፈቱም አሉ፤ አሁንም የታሰሩ አሉ፡፡ ግን አሁንም ብዙ ካድሬ በአርሶ አደር ስም መሬት መውሰዱን አላቆመም፡፡ ይሄ በማዕከልም የሚታወቅ ነገር ነው››

ዋዜማ ከሁለቱም ባለሞያዎች ያገኘችው  መረጃ እንደሚያሳያው ካድሬዎች የሥርዓቱን መነቃነቅ ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት መሬት መቀራመት ብቻም ሳይሆን ለአርሶ አደር የተዘጋጀውን ልዩ ልዩ የካሳ ገንዘብ ክፍያም ይቀበላሉ፡፡ ይህም የባሕር ዛፍ፣ የሰብል፣ የግጦሽ፣ የንብረት ማጓጓዣ፣ የአንድ ዓመት የቤት ኪራይ የካሳ አበልን ሳይጨምር በልማት ፈረሰብን ለሚሉት መሬት ከብር 500ሺህ ብር ጀምሮ በጥሬ ገንዘብ ይከፈላቸዋል፡፡
ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ወቅት በደረሰን ተያያዥ መረጃ ከያዝነው ሳምንት መጀመርያ ጀምሮ በችግሩ ስፋትና መጠን ዙርያ በክፍለ ከተማ ካቢኔ ደረጃ ውይይት ተደርጎበት አንዳንድ ክፍለ ከተሞች ለተነሺ አርሶ አደሮች የሚሰጠውን ምትክ ቦታም ሆነ የካሳ ክፍያ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲያቆሙ ተደውሎ ተነግሯቸዋል፡፡ ኾኖም ከአስሩ ክፍለ ከተሞች ግማሾቹ ‹‹ በደብዳቤ አልተገለጸልንም›› በሚል አሁንም መሬት በማደል ላይ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል በልማት ምክንያት ከቀያቸው በመፈናቀላቸው የሕይወት ምስቅልቅል ውስጥ የገቡ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ቤተሰቦችን መልሶ ለማቋቋምና ለመታደግ በሚል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‹‹የልማት ተነሺ አርሶአደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት›› የሚባል ጽሕፈት ቤት በአዋጅ አቋቁሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ጽሕፈት ቤት የተቋቋመው አዋጅ 361/95ን መነሻ በማድረግ በጥቅምት ወር በ2009 በይፋ ሥራ መጀመሩም ይታወቃል፡፡ የዚሁ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱራዛቅ ያሲን በአንድ ወቅት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሠጡት ቃለ ምልልስ አርሶ አደሮችን ደረጃ በደረጃ ወደ ኢንቨስትመንት ሥራዎች በማስገባት ባለሐብት ለማድረግ እንደተወጠነ ተናግረው ነበር፡፡
በተፈናቃይ አርሶ አደሮች ዙርያ የተደረጉ ልዩ ልዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በልማት ስም ከሚነሱት አርሶ አደሮች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ለአስከፊ ድህነት እንደሚጋለጡ ይወሳል፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ጥናቶች እንዳሳዩት ደግሞ ተነሺ አርሶ አደሮች ቀደም ሲል ይኖሩት ከነበሩት ሕይወት እጅግ ባነሰ ሁኔታ ኑሯቸውን እንደሚገፉ፤ ወንድ ልጆቻቸው ለጉልበት ሥራ፣ ሴቶች በሴተኛ አዳሪነት እንደሚሰማሩም ታውቋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ሁኔታ እየተለወጠና የካሳ ክፍያውም እየተሻሻለ የነበረ ቢኾንም በአርሶ አደሮች ስም የመሬት ምዝበራ በከተማው በከፍተኛ ሁኔታ መንሰራፋቱን ተከትሎ አዲስ የአሰራር አቅጣጫ እስኪሰጠን በሚል የተወሰኑ ክፍለ ከተሞች መሬት ማደሉን ጋብ አድርገውት ቆይተዋል፡፡
ከመሬት ቅርምቱ ባሻገር በአዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥ ባሉ የገዥው ግንባር አባላት መካከል እያደገ የመጣ ቁርቁስና አልታዘዝ ባይነት የመስተዳድሩን ስራዎች እያስተጓጎለ መሆኑን ስራተኞች ይናገራሉ።
ስብሰባዎች ስልጠናና የመስክ ጉዞ ማድረግ እጅጉን አስቸጋሪ ሲሆን በአለቆቻቸው ላይ ያመፁ የበታች ሹማምንት በብሄር ተቧድነው አልታዘዝ ባይ መሆናቸውንም ስምተናል። ችግሩን ለመፍታትም አንዳች ሙከራ የሚያደርግ አካል እስካሁን አልታየም። [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ተያይዟል]

https://youtu.be/LqN-lo8NzkM