PHOTO-FILE

ዋዜማ- ለሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ የነበረችው ትግራይ በጦርነቱ ማግስት ከገጠሟት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አንዱ የወጣቶች በገፍ ክልሉን እየለቀቁ መሰደድ ነው። 

በትግራይ ስደት ከጦርነቱ በፊትም የነበረ ቢሆንም ከጦርነቱ በኋላ ግን እጅግ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ እንደጨመረ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር የወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ሓይሽ ሱባጋድስ  ለዋዜማ ተናግረዋል።

እድሜያቸው ከ 15 እስከ 18 የሚሆኑ ታዳጊዎች ትምሕርታቸውን አቋርጠው ከአገር እየወጡ እንደሆነ፣ አብዛኞቹ በየመን እና ሳውዲ አረቢያ እስር ቤት ወስጥ ቀሪዎቹ ደግሞ በሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች እጅ እንዳሉና በርካታ ወጣቶችም በመንገድ ላይ እና በበረሃ እየሞቱ እንደሆነ መረጃዎች ይደርሱናል ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።

ከወራት በፊት የመንን አቋርጠው ወደ ሳውዲ አረቢያ ሊገቡ ሲሉ በሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች ከተገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና፣ ጅቡቲ ላይ በጀልባ መስጠም አደጋ ሕይወታቸውን ካጡት መካክል፣ አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች መሆናቸውን ኃላፊው ለዋዜማ አረጋግጠዋል።

ይህ አስደንጋጭ ክስተት እየታየ እንኳን በቀሪዎቹ ወጣቶች ላይ የመሰደድ ፍላጎት ሲቀንስ አለመታየቱ በትግራይ ክልል ያለው ችግር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያሳያል ይላሉ ሓይሽ።

እንደ አይ ኦ ኤም ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያወጡት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በዚህ ውቅት እንደ አገር ያለው የስደት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የሚያሳይ ሲሆን ፣ በትግራይ ያለው ግን ከዚያ የተለየና ለመቆጣጠርም አዳጋች የሆነ ነው።

ትግራይ ውስጥ ባሉ የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከ 500 ሺሕ በላይ ተፈናቃይ ወጣቶች አሉ፣ በመጠለያ ጣቢያው በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ ባለመኖሩና ምንም አይነት ለነገ የሚሉት ተስፋ የሚታያቸው ባለመሆኑ ወጣቶቹ ስደትን ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገዋል ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ወጣቶቹ በብዛት እየተሰደዱ ያሉት ከምሥራቅ እና ደቡብዊ ዞኖች፣ከሰሜን ምዕራብ እና ሰሜናዊ የትግራይ አካባቢዎች፣ከመቀሌ ከተማ እና አካባቢዋ በተወሰነ መልኩ እንደሆነ ኃላፊው ሓይሽ ተናግረዋል።

ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት እንዲሁም የሕገ ወጥ ደላሎች ማታለያ ለመሰደዳቸው ሌላው ምክንያት እንደሆነ ሓይሽ ያስረዳሉ።

ዋዜማ በዚሁ ጉዳይ ላይ የትግራይ ክልል ወጣቶች ማኅበርን ያነጋገረች ሲሆን ማኅበሩ በክልሉ ያለው ሥራ አጥነት ያስከተለው የወጣቶች ስደት እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ ደርሷል ሲል ገልጿል።

የክልሉ ወጣቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ሠናይ ከሓሳይ ለዋዜማ እንደተናገሩት ማኅበሩ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመተባበር በ 10 ወርዳዎች፣ በ 30 ቀበሌዎችና በ1 ሺህ 200 መቶ ወጣቶች ላይ ፈጣን የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን ገልጸዋል።

የጥናቱም ፍለጋ ከጦርነቱ በኋላ የወጣቱ መተዳደሪያ ምንድነው?፣ትምሕርት ጤና እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ከማግኘት አንጻር ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል የሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ያካተተ እንደሆነ ለዋዜማ አስረድተዋል። 

ከላይ የተጠቀሱት አገልግሎቶች ባለመኖራቸውና በክልሉ አሁን ባለው ሁኔታ ምንም የሚጨበጥ ተስፋ ባለመኖሩ ምክንያት ካሉት ወጣቶች መካከል ግማሽ ያህሉ የመሰደድ ሃሳብ ያላቸው እንደሆኑ በተደረገው ጥናት መሰረት ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።

ጥናቱ እንደሚያመለክትው በዚህ ወቅት ትግራይ ውስጥ ካሉ ወጣቶች መካከል 81 በመቶ የሚሆኑት ሥራ አጥ መሆናቸውን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ እነዚህ ወጣቶች አብዛኞቹ ከጦርነቱ በፊት የራሳቸው ተቋም የነበራቸው፣ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ፣ መልካም የሚባል ሕይወት ሲመሩ የነበሩ መሆናቸውና ከጦርነቱ በኋላ ግን ያላቸውን ጥሪት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ያጡ ናቸው ሲሉ።

ከትምህርት ፍላጎት ጋር ተያይዞ በወጣቶቹ ላይ በተደረገው ጥናት ካሉት ወጣቶች መካከል 78 በመቶ የሚሆኑት ምንም አይነት የመማር ፍላጎት የሌላቸው ናቸው የሚሉት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት በጦርነቱ ምክንያት ቤተሰቦቻቸን ያላቸውን ነገር በሙሉ ስላጡ እኛን የሚያስተምሩበት አቅም የላቸውም የሚል እንደሆነ አብራርተዋል።

ከሥራ ፈጠራ አንጻር፣ 31 በመቶ የሚሆኑት የራሳችን ሥራ ፈጥረን እንሰራለን የሚሉ እንደሆኑ 29 በመቶዎቹ ደግሞ በተለያዩ መንግሥታዊና የግል ተቋማት ተቀጥረን መስራት አለብን የሚል ሃሳብ ያላቸው፣ ቀሪዎቹ ግን የመሰደድ ፍላጎት ያላቸው ናቸው ብለዋል

ከነዚህ የመሰድድ ፍላጎት ካላቸው ውስጥ 53 በመቶዎቹ እድሜያቸው ከ 26 እስከ 35 ባለው መካከል የሚገኝ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ግን ከ 15 እስከ 25 ባለው መካከል እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በክልሉ ካሉ ወጣቶች 78 በመቶ የሚሆኑት ምንም አይነት የበይነ መረብ አገልግሎት እንደማያገኙ 97 በመቶ የሚሆኑት የኮምፒዩተር አገልግሎት፣ 29 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የስልክ አገልግሎት የሌላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ሥራ ለመፈለግና የሚወጡ የሥራ እድሎችን እንዲሁም ማስታወቂያዎችን ለማየት አስቻይ ሁኔታ የላቸውም በማለት ተናግረዋል።

ከማኅበራዊ ሕይወታቸው ጋር ተያይዞ 89 በመቶ የሚሆኑት የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ትዳር የመያዝ፣ ኃላፊነት የመውሰድና ቤተሰብ የመመስረት ፍላጎት እንደሌላቸው ባደረጉት ጥናት ማረጋገጣቸውን ተናገረዋል።

በሌላ በኩል ትግራይ ከጦርነቱ መገባደድ በኋላ የዝናብ እጥረት ያስከተለው ድርቅ፣ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ተደማምረው የደቀቀው ምጣኔ ሀብቷ ለወጣቱ መሰደድ ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል።

ዋዜማም በሕገወጥ መንገደ ተሰደው በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙትን የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች በስልክ አነጋግራለች።

ሕሉፍ ዓባይ ተወልዶ ያደገው በሽረ እንዳ ሥላሴ ከተማ ገባር ሽረ በተባለ አካባቢ እንደሆነ ለዋዜማ የገለጸ ሲሆን፣ በዚያም የሚተዳደረው በብረት ብየዳ ሥራ እንደነበር፣ በጦርነቱ ምክንያት ግን ያለው ሃብት ንብረት በሙሉ እንደወደመትና ባዶ እጁን እንደቀረ ይናገራል።

ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት መሆኑን የሚገልጸው ሕሉፍ የሚያደርገው ቢጠፋው የራሱንንና የቤተሰቡን ሕይወት ለማሰንበት በሕገ ወጥ መንገድ መሰደድን መምረጡን ገልጿል።

ሕሉፍ ያሰበውና የሆነው ለየቅል እንደሆነበትና በሳውዲ አረቢያ የጸጥታ ኃይሎች ተይዞ በእስር ቤት ውስጥ አስቸጋሪ ሕይወት መግፋት ከጀመረ አምስት ወራት መቆጠራቸውን አስረድቷል።

ሌላኛው ከውቅሮ ከተማ ተሰዶ እንደወጣና ትምህርቱን ከአስራ አንደኛ ክፍል እንዳቋረጠ የሚናገረው ሀበን ተስፋይ ቤተሰቦቹ ሊያስተምሩት አቅማቸው ባለመፍቀዱ ስደትን መምረጡን ገልጿል።

በእስር ቤቶቹ ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ ተሰደው የወጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች መኖራቸውን ዋዜማ በእስር ቤቱ ወስጥ ካሉ ሰዎች ማረጋገጥ ችላለች።

ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸው የክልሉ ወጣቶች ቢሮና የወጣቶች ማኅበር ወጣቶቹን ከስደት ለመታደግ በፌዴራል መንግስቱም ይሁን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት እጅግ አነስተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል። [ዋዜማ]