• ከኦሮሞ ጋር ወግናችኋል የተባሉ የአማራና የጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጆች ንብረታቸው እየተቀማ ነው

ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች ውስጥ የተነሳው ግጭት ከመብረድ ይልቅ በተለይ በጅግጅጋ (ጅጅጋ) ከተማ መልኩን እየቀየረ መሆኑን ዋዜማ በስፍራው ከሚገኙ ምንጮቹ መስማት ችሏል።

እነዚሁ ምንጮች እንዳሉት ከሆነ “ከዚህ ቀደም በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉትን ለማቋቋም የተሰበሰበው ገንዘብ ለሶማሌ ተፈናቃዮች አይውልም ተብሏል፤ እንዲሁም በክልሉ የሚኖሩ የአማራና የጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጆች ከኦሮሞዎች ጋራ ወግነዋል” የሚል ቅስቀሳ ለግጭቱ አቅጣጫ መቀየር ዋና ምክንያት እየሆነ ነው።

ይህን ተከትሎም ከትናንት ረቡዕ ጥቅምት 1 ጀምሮ በጂጂጋ ከተማ ለዘመናት የኖሩ የአማራ እና የጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጆች የመኖሪያ ቤትና የንግድ ሱቆች እየተነጠቀ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ድርጊቱ በዋናነት የሚፈጸመው “በሱማሌ ክልላዊ መንግስት ይደገፋሉ” በሚባሉ ሰዎች ነው ተብሏል። የዋዜማ ዘጋቢዎች “ንብረታቸውን ተነጠቁ፣ ተባረሩ” የተባሉትን እነዚህን ሰዎች በቀጥታ አግኝተው ለማረጋገጥ አልቻሉም።

በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጀምሮ በተስፋፋው ግጭት ከሰባ ሺህ በላይ ዜጎች እንደተፈናቀሉበት የሚታወቅ ነው። በዚህ ግጭት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች እርዳታ ይሁን በሚል ከተለያዩ ባለሀብቶች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየተሰበሰበ ነው። ሆኖም ምንጮቹ እንዳሉት፣ ይህ ከባለሀብቶቹ የተሰበሰበው ገንዘብ “በግጭቱ ለተጎዱት የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት ማቋቋሚያ ብቻ እንደሚውል” ተደርጎ በመንግስታዊው የዜና አውታር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መነገሩን ውጥረቱን ወደ ጥቃት እንዳሸጋገረው የዋዜማ ምንጮች አስረድተዋል። በጅጅጋ “በሱማሌ ብሔረሰብ አባላት ላይ ጉዳት አልደረሰም እንደውም ለደረሰውም ግጭት በቀጥታ ተጠያቂው የሱማሌ ክልላዊ መንግስት ነው ተብሏል” የሚል ግንዛቤ መስፋፋቱ ታውቋል።

“አማራዎችና ጎራጌዎች በክልላችን እየኖሩ ከኦሮሞው ጎን መቆማቸውን በይፋ ድጋፍ በማድረግ ጠላቶቻችን እንደሆኑ አሳይተዋል። ስለዚህ እዚህ ያፈሩት ሀብትና ንብረት የሀገሬው በመሆኑ ተነጥቀው ለሱማሌው መሰጠት አለበት” የሚል ምንጩ ያልተረጋገጠ ቅስቀሳና አቋም እየተሰራጨ መሆኑን ከምንጮቻችን ለመረዳት ተችሏል። ምንጮቻችን በዚህ እንቅስቃሴና አቋም ውስጥ የክልሉ መንግስት እንዳለበት ይጠረጥራሉ።

ከአካባቢው ሀሞስ ዕለት ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ አንድ የረድዔት ድርጅት ባልደረባ በጅጅጋ ና አካባቢው ካለፈው አንድ ወር ወዲህ ያለው ውጥረትና ስጋት በግልፅ የሚታይ ሲሆን ከኦሮሞ ማህበረሰብ መፈናቀል ተከትሎ የሌላ ብሄር ተወላጆች “የጥቃት ኢላማ እንሆናለን” በሚል የንግድ ተቋሞቻቸውን የዘጉ፣ ንብረታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያሸሹ መኖራቸውን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት በክልሉ ሚሊሻዎች አንድ መቶ ሺ ብር አምጣ ተብሎ ፈቃደኛ ያልሆነ ነጋዴ ለአቤቱታ ወደ ክልሉ የፀጥታ ሀላፊዎች ሲሄድ አግኝቼዋለሁ ብለዋል። ስርዓት አልበኝነትና ሌላውን ኢትዮዽያዊ በአይነ ቁራኛ መመልከቱ እየተጠናከረ መምጣቱን ታዝቤያለሁ ብለውናል ግለሰቡ።
በጅጅጋ ነዋሪ የሆነና ያለፉትን አስራ ስድስት አመታት በንግድ ስራ ያሳለፈ ሌላ አስተያየት ስጪ “ከዛሬ ነገ ምን ያደርጉናል በሚል በስጋት ቆይተናል፣ ከትናንት በስቲያ ማክስኞ ማንነታቸውን የማናውቃቸው ግለሰቦች ንግድ ቤቶቹን አስረክቡ፣ ገንዘብ አምጡ ሲሉን ውለዋል። ተመልሰው እንደሚመጡ ነግረውናል”
ቢያንስ አስራ አንድ የሌላ ብሄር ተወላጅ በመሆናቸው የንግድ ቤትና መኖሪያቸው መወረሱ እንደተነገራቸው፣ ከነሱም ውስጥ አራቱ ዕሮብ ዕለት ሸሽተው ከተማውን ለቀው መውጣታቸውን አውቃለሁ ይላል።

በአሁኑ ወቅት በምስራቁ የኢትዮጵያ አካባቢ ያለውን ሁኔታ በተመላከተ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነገሩን አሳንሶና የተረጋጋ አስመስሎ ቢሞክርም የውጭም ይሁን የአለም አቀፍ የመገናኛ አውታሮች ወደ ቦታው ለመሄድ እንዳልቻሉ እየገለጹ ነው።
ይሁንና ጉዳዩ ግን መንግሥቱ ከሚናገው በላይ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን በስፍራው ከሚገኙት እና በጭንቀት ውስጥ ከሚገኙት ነዋሪዎች፣ እንዲሁም ከአካባቢው ሽሽተው ከወጡ ሰዎች እየተሰማ ይገኛል ።

የኢትዮጵያ መንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዬች ሀላፊው ግጭቱ ተነስቶ ብዙ ጥፋት ከደረሰ በኃላ ዘግይቶና በተለያየ ጊዜ በሰጠው መግለጫው የግጭቱን ወቅታዊ መንስኤ አለማወቁንና ግጭቱንም ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንዳልተቻለ መግለጹ የሚታወቅ ነው። አሁን “ጂጂጋ የሚኖሩ የአማራ እና የጎራጌ ብሔረሰብ አባላት ንብረት እየተነጠቀ ነው” የሚለው መረጃ ፍጹም አለመረጋጋት የሚያመጣና ግጭቱን ወደላቀ ትርምስ ሊያንደረድር የሚችል መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ገልጸዋል ።