Somali and Oromia regional leaders – FILE

ዋዜማ- ከሰሞኑ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ባቢሌ አካባቢ በጫት ቀረጥ ሰበብ የተቀሰቀሰው ግጭት ውጥረት መፍጠሩን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርበት ካለቸው ምንጮች ተረድታለች፡፡ 

ግጭቱ የብሔር መልክ የያዘው ከኦሮሚያ በኩል የተነሱ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ዩኒፎርም የለበሱ የታጠቁ ኃይሎች፣ በቆሎጂ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ በሰፈሩ የሶማሌ ተፈናቃዮች ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ኃይሎች በተፈናቃዮቹ ላይ በከፈቱት ተኩስ፣ ሁለት ህጻናትን ጨምሮ ከ10 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን በወቅቱ በቦታው የነበሩና አሁን ወደ ጅግጅጋ የሸሹ የአይን እማኝ ለዋዜማ ተናግረዋል።

በተፈናቃዮቹ ካምፕ ላይ በተከፈተው ተኩስ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን ተከትሎ፣ በአካባቢው የሚገኙ የሶማሌ ክልል የጎሳ ታጣቂዎች  ከኦሮሚያ ክልል ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል።

የግጭቱ መነሻ ከኦሮሚያ አወዳይ ተነስቶ በጅግጅጋ ወደ ጎረቤት ሶማሊያ የሚወጣ ጫት “ትቀርጣለህ አትቀርጥም” የሚል የሁለቱ ወገኖች ውዝግብ መሆኑ የዋዜማ ምንጮች በተመሳሳይ ገልጠዋል።

መጀመሪያ የነበረው ግጭት በሶማሌ ክልል ታጣቂዎችና በኦሮሚያ የጽጥታ ኃይሎች መካከለ የነበረ ሲሆን፣ ኃላ ላይ ወደ ብሔር ግጭት አድጓል ተብሏል።

የተኩስ ልውውጡ የተጀመረው የሶማሌ ኃይሎች ካራ ማራ አካባቢ የነበራቸውን መቅረጫ ጣቢያ ወደ ባቢሌ ማዛወራቸው እና የኦሮሚያዎቹም እንደዚሁ ወደ ወሰን ተጠግተው ሁለቱም ወገኖች አማካኝ ቦታ ላይ ኬላ ከዘረጉ በኋላ  ነው፡፡

ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ዕለት በሁለቱ ወገኖች መካከል ለስዓታት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር፣ ግጭቱ ሸሽተው ወደ ጅግጅጋ የተፈናቀሉ የአይን እማኞች ጠቁመዋል።

ከግጭቱ  መቀስቀስ በኋላ ወደ አካበቢው ያቀናው የአገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ዋና መስመሩን የተቆጣጠረው ሲሆን፣ ከዋናው መስመር ወጣ ባሉ ተራራማ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጡ ቀጥሎ ሰንብቷል። 

ይህ ዜና በተጠናቀረበት ወቅት በአካባቢው የነበረው የተኩስ ልውውጥ መጀመሪያ ከነበረው ሁኔታ የመርገብ አዝማሚያ ማሳየቱ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ምንጮች ገልጠዋል።

ምንም እንኳን በአካባቢው የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ቢሰማሩም፣ ሁለቱም ክልሎች የጸጥታ ኃይሎቻቸውን ግጭት ወደተፈጠረበት ቦታ ማስጠስጋታቸውን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ቀድሞውንም በአካባቢ እንደነበሩ የተገለጠ ሲሆን፣ አሁን ላይ የሶማሌ ክልል መንግሥት መደበኛ የጸጥታ ኃይሉን ወደ አካባቢው ማስጠጋቱ ታውቋል። 

ዋዜማ ያነጋገርናቸው የሁለቱን ክልሎች ውዝግብ የሚከታተሉ ሰላም ደህንነት ጉዳዮች አዋቂ፣ የችግሩ መነሻ የጫት ቀረጥ ቢሆንም አሁን ላይ መልኩን መቀየሩ ስጋት የሚፈጥር መሆኑን ይገልጣሉ።

የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች አዋቂው እንደሚሉት ቀድሞውንም በአካባቢው በወሰን ይገባኛል እና በብሔር ግጭት ውዝግብ ውስጥ የቆዩት ሁለቱ ወገኖች መፋጠጥ በአግባቡ ካልተዳኘ አስጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የሁለቱ ክልሎች ግጭት በቀላሉ የሚበርድ አይደለም ያሉት ባለሙያው፣ አሁን የሚታየው አዝማሚያ አወዛጋቢ ቦታዎችን “የመጠቅለል” ፍላጎት መሆኑን ይገልጣሉ። 

የወሰን ላይ የይገባኛል ውዝግቡ ካገረሸ በሁለቱ ክልሎች መካከል ከዚህ ቀደም ከነበረው ቁርሾ ጋር ተዳምሮ የከፋ ግጭቱ ሊያስከትል አንደሚችል ስጋት አላቸው።

ግጭቱ በተከሰተበት የቆሎጂ መጠለያ ጣቢያ ከሰፈሩ ተፈናቃዮች መካከል የተወሰኑት ወደ ጅግጅጋ፣ ደጋሃና ባቢሌ ከተማ ሸሽተዋል።

ተፈናቃዮቹ የተጠለሉበት ቦታ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን እና ሱማሌ  ክልል ፈንታሌ ዞን አዋሳኝ ቦታ ነው። የሁለቱ ክልል ተወላጆች በተለይ በወሰን አካባቢዎች በስፋት ተሰባጥረው የሚኖሩ ቢሆንም፣ የብሔር ግጭት ውስጥ ከገቡ በኋላ አልፎ አልፎ ውጥረቶች ይታያሉ።

ስለ ግጭቱም ይሁን ስለፈጠረው ውጥረት የሁለቱ ክልሎችም ይሁን  የፌዴራል መንግሥቱ እስካሁን በይፋ የሰጡት መረጃ የለም። [ዋዜማ]