Yonas Adaye (PhD), member of ENDC

ዋዜማ- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከመንግሥት ጋር እየተፋለሙ የሚገኙ ታጣቂ ኃይሎችን ለማነጋገር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ለዋዜማ ገልጿል።

ኮሚሽኑ በአማራ ክልሉ በፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ውጊያ መቀስቀሱን ተከትሎ፣ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው እንዲነጋገሩ መጠየቁ የሚታወስ ነው።

ኮሚሽኑ ባቀረበው የሰላም ጥሪ ላይ ታጣቂ ኃይሎችን እና መንግሥትን ለማቀራረብ ሁኔታዎችን የማመቻቸት በራሱ ኃላፊነት ወስዷል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ውጊያ አቁመው እንዲነጋገሩ የጀመረው ጥረት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ዋዜማ  የኮሚሽኑ አባል አነጋግራለች። 

ዋዜማ ያነጋገርናቸው የኮሚሽኑ አባል ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎችን ለማነጋገር ሂደት መጀመሩን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በጀመረው መንግሥትን እና ታጣቂዎችን የማቀራረብ ጥረት፣ ከመንግሥት አካላት ጋር መነጋገሩን ኮሚሽነር ዮናስ ጠቁመዋል። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት መንግሥት ግጭት አቁሞ ለመነጋገር ፈቃደኝነት ካሳየ በኋላ፣ ኮሚሽኑ ወደ ታጣቂ ኃይሎች ማነጋገር የሚያስችለውን ሂደት ጀምሯል።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀስውን ፋኖን እና መንግሥትን ማወያየት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ፣ ኮሚሽኑ የአማራ ክልል ምሁራንንና የክልሉን አመራሮች ማነጋገሩን ዮናስ ገልጸዋል። 

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውንና ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራውን  ታጣቂ ኃይል በተመለከተ፣ በቅርቡ ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን ኮሚሽነሩ አመላክተዋል። በተደረገው ውይይት ባለሥልጣናቱ የኮሚሽኑን ጥረት እንደሚደግፉና እንደሚተባበሩ መግለጻቸውንም ጠቁመዋል።

እስካሁን የተደረጉ ጥረቶች አዎንታዊ ውጤት ማሳየታቸውን የጠቆሙት ዮናስ፣ ኮሚሽኑ በቀጣይ ታጣቂ ኃይሎችን እንደሚያነጋግር ለዋዜማ አረጋግጠዋል።

በሁለቱም ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ለማነጋገር ኮሚሽኑ እርግጠኛ መሆኑን ተከትሎ፣ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ዮናስ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ የጀመረው የንግግር ጥረት ቀጣይ ሂደት ነፍጥ አንስተው ከመንግሥት ጋር እየተፋለሙ የሚገኙትን ታጣቂ ኃይሎች አለን የሚሉትን ችግርና ጥያቄ ማዳመጥ መሆኑንም አክለዋል።

መንግሥት ከታጣቂዎች ጋር ያለውን ልዩነት በንግግርና ድርድር ለመፍታት የሚኖረውን የመጨረሻ ቁርጠኝነት በተመለከት፣ ለዋዜማ  አስተያየታቸውን የሰጡት ኮሚሽነሩ “ጉዳዩ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነው” ሲሉ ገልጸውታል። 

ኮሚሽኑ ታጣቂ ኃይሎችን ለማነጋገር በያዘው ዕቅድ መሰረት የፋኖ ታጣቂዎችን የማነጋገር ኃላፊነት የተሰጣቸው ኮሚሽነር ዮናስ፣ ታጣቂ ኃይሉ የተለያየ አደረጃጀት እንዳለው ጠቁመዋል። 

ኮሚሽነሩ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ወጣቶች በተመለከተ “የኛው ልጆች ናቸው፣ ችግራቸውን የማናዳምጥ ከሆነ፣ የማንነጋገርና የማንተማመን ከሆነ ምኑ ጋር ነው ኢትዮጵያዊነታችን?” ሲሉም ይጠይቃሉ። 

ታጣቂ ኃይሎች የሚነጋገር ሂደት ላይ የሚገኘውን ውጤት ኮሚሽኑ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። 

ኮሚሽኑ ባቀረበው አስቸኳይ የሰላም ጥሪ ላይ ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መቀጠላቸው የአገርን ህልውና የሚፈታተን ሁኔታ መፍጠራቸውን ገልጾ ነበር። 

ኮሚሽኑ የምክክሩ አጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ አካላት ልየታን በሰጠው መግለጫ ላይ ተፋላሚ ወገኖች መሳሪያ አስቀምጠው እንዲደራደሩ ጠይቋል።

የኮሚሽኑ ዋና ስብሳቢ መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ግጭቶች እየተባባሱ ወደ ጦርነት እያደጉ መሄዳቸው ጭራሽ ችግሩን እያባባሰ፣ በኮሚሽኑ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረና ተጨማሪ ስብራት እየፈጠረ ነው ብለዋል።

በጦር መሳሪያ የተፈታ ችግር አለመኖሩ እስካሁን ታይቷል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ጦርነት ሌላ ጦርነት እየፈጠረ መሆኑን በመገንዘብ መግባባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ነሃሴ 2/2015 ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለመንግሥትና መንግሥትን ለሚፋለሙ ኃይሎች ባቀረበው ጥሪ የአገሪቱን ሕልውና የሚፈታተን ሁኔታ መፈጠሩን መግለጹ የሚታወስ ነው።

ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ማብቃት ማግስት በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውና በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ውጊያ እንዲቆም፣ ከሃይማኖት ተቋማት እሰከ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከሰብዓዊ መብት ተቋማት እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች አጥብቀው እየጠየቁ ነው። [ዋዜማ]