Et troops in Somaliaዋዜማ ራዲዮ- በሶማልያ ባለው የኢትዮጵያ ስራዊት ላይ በስብዓዊ መብት ረገጣና ብሎም ንፁሀን ዜጎችን በመግደል ክስ ሲቀርብበት ያሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ከአራት አመት በፊት የኢትዮጵያ ስራዊት ፈፅሞታል በተባለው ወንጀል ምርመራ ተደርጎበት ለደረሰው ጥቃት ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፍል መደረጉ ይታወሳል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሶማሊያ በተሰማራው የኢትዮጵያ ስራዊት ላይ አዲስ ዘመቻ ተከፍቷል። በአፍሪቃ ህብረት ስር ያሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ያነጣጠረው ይህ አዲስ የማጥላላት ዘመቻ “ሀገራችንን ለቃችሁ ውጡ”  “በናንተ ድጋፍ ስላም ሊመጣ አይችልም” የሚል ነው። ዘመቻው በማህበራዊ ሚዲያ አሁንም ድረስ እየተራገበ ሲሆን በጉዳዩ ግር የተሰኘው የሰራዊቱ ማዘዣ ወታደሮቹ ከመቼውም በላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መመሪያ አስተላልፏል።
የሰራዊቱ አባላት ለጥንቃቄ በሚል በሚወስዱት እርምጃ ሳቢያ ከታዋቂ ሶማልያውያን ሳይቀር ተጨማሪ ቅሬታ እየቀረበባቸው ነው። የባይዶዋ አየር ማረፊያን ፀጥታ እንዲያስከብሩ የተመደቡ የኢትዮጵያ ወታደሮች “ለአንድ ሰዓት ያህል አግተውኛል አካላዊ ጥቃትም አድርሰውብኛል” በማለት ታዋቂዋ የሶማሊያ የመብት ተሟጋች አሚና አራል በቲውተር ተቃውሞዋል ይፋ አድርጋለች።
የውጪ ሀገር ሚዲያ ዘጋቢ የሆነው አብዱልአዚዝ ቢሎ በበኩሉ በባይዶዋ ከአንድ የኢትዮጵያ ወታደር ጋር የገጠመውን ግብ ግብና ጉዳዩን እንዲፈቱለት የጠየቃቸው የሰራዊቱ አዛዥ ግን አርፎ ከአየር ማረፊያው እንዲወጣ፣ ጉዳዩን ሪፖርት ካደረገ ዳግም በዚህ አየር ማረፊያ ማለፍ እንደማይችል ከማስፈራሪያ ጭምር ነግረውኛል ብሏል።
ስለጉዳዩ መልስ እንዲስጡ የጠየቅናቸው በአሚሶም የኢትዮጵያ ስራዊት ሀላፊዎች “እናንተ ምን አገባችሁ፣ ይህ የሶማሌ ጉዳይ ነው” ሲሉ አጣጥለዋል።
የአፍሪቃ ህብረት ግን ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን ገልፆ ምርመራውን እንደጨረሰ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ሌሎች ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ጉዳይ የሚሰሩ ባለሙያዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል የተሰጣቸው ምክር ከወትሮው በተለየ ጠርጣራ አድርጓቸዋል ይላሉ።
በሶማሊያ አዲስ ፕሬዝዳንት ከተመረጠ በኋላ የውጪ ሀይሎች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው። ይህ ተቃውሞ በኢትዮጵያ ላይ ይበረታል። ይሁንና ሶማሊያ የራሷን ፀጥታ ለማስከበር በምትችልበት አቋም ላይ አይደለችም።
የሶማሊያ የጦር ሀይልን ለመገንባት የአፍሪቃ ህብረትና የምዕራብ ሀገራት በሰፊው እየሰሩ ይገኛሉ። የፈራረሰው የሶማሊያ አየር ሀይል በቱርክ ድጋፍ የመጀመሪያ ዙር አብራሪዎቹን በአንካራ አስመርቋል።
በውጪ ሀይላት ድጋፍ ያለው የሶማሊያ ጦር ሀይል አባላትም ቢሆኑ ለማመን የሚቸግር ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ኬን ያ አቋም ማንፀባረቅ ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
አዲሱ የሶማሊያ አስተዳደር ሀገሪቱን ከውጪ ሀይላት ተፅዕኖ ነፃ አወጣለሁ ማለቱና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር የበለጠ ሸሪክ እየሆነ መምጣቱ እየተቀዛቀዘ ለሄደው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት አንዱ ስበብ ነው።
በሶማሊያ ከሁለት ሺህ የማያንሱ ወታደሮቿን ለገበረችው ኢትዮጵያ  አሁን እያደገ የመጣው የጥላቻ ስሜት ከቀደመ ታሪካችን የሚቀዳ ይመስላል። ኢትዮጵያና ሶማሊያ  ሁለት ትልልቅ ውጊያዎችን ማድረጋቸው ይታወቃል።