ዋዜማ ራዲዮ- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታ ግድም ወረዳ በማጀቴ ፤ በካራ ቆሬ እና በዙሪያዋ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ላይ ኦነግ ሸኔ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች ከትናንት ምሽት ጀምሮ በከፈቱት ጥቃት በትንሹ ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን ምስክሮችና የአካባቢው ፖሊስ አባላት ለዋዜማ ተናግረዋል።

ብዙዎች ቆስለው ወደ ደሴ እና በአቅራቢያው ወደሚገኘው የኮምቦልቻ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ይህ ዜና እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ተኩሱ አለመቆሙን ነዋሪዎቹ ለዋዜማ ተናግረዋል።

ይህ ጥቃት የተፈፀመው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከፍተኛ ልዑክ ክሪስ ኩን በትግራይ ቀውስና በሱዳን የድንበር አለመግባባት ዙሪያ ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ወደ አዲስ አበባ እያቀኑ ባለበት ሰዓት ነው።

እስካሁን በትንሹ 20 የሚሆን አስከሬን መነሳቱን እና ሌላውን ለማንሳት በተኩሱ ምክኒያት እንዳልተቻለ የዐይን እማኞች ነግረውናል ። የሟቾች ቁጥር ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችልም ተነግሯል።

በተለይ ከማጀቴ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ በሚገኝ ጭሬ በተባለ ስፍራ ተኩሱ ጸንቶ መዋሉን ነዋሪዎች ይገልፃሉ።

የአጣየ ከተማ ነዋሪዎች ደግሞ ለዋዜማ እንደገለጹት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከተማዋን ከበው ይዘዋል።

የኦነግ ሸኜ ወደ ከተማው የገባው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ በቅርቡ ተነስቶ ወደ ሌላ ዞን መዛወሩን ተከትሎ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

በስፍራው የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የመንግስት ታጣቂዎች የነበሩ ቢሆንም የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በከባድ የጦር መሳሪያ የታገዙ በመሆናቸው መከላከል እንዳልቻሉ የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ ከደቡብ እና ከሰሜን ወሎ ዞኖች ወደ አካባቢው እያመራ መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]