Odaa

የሀገራችን ፌደራላዊ ስርዓት በቋንቋ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት የቋንቋ ፖሊሲ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የቋንቋ ፖሊሲ በተመራማሪዎች መካከል ክርክር ሲደረግበት መቆየቱ እሙን ነው፡፡ ጥያቄወ አድናቂዎች ያሉትን ያህል ጠንካራ ትችቶችንም ሲያስተናግድ ኖሯል፡፡ ሀገሪቱም ተጨማሪ የፌደራል የስራ ቋንቋ ያስፈልጋታል ወይስ አያስፈልጋትም የሚለውክርክርም ጎላ ብለው መሰማት ጀምረዋል፡፡
ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ከግዕዝ ይልቅ የላቲን ፊደላትን ወይም “ቁቤ”ን መጠቀም የጀመረው ኦሮምኛ በአፍሪካ ሦስተኛው ትልቁ የአፍ መፍቺያ ቋንቋ መሆኑን ምሁራን ይገልፃሉ፡፡ ስለዚህ ኦሮምኛ ሁለተኛ የስራ ቋንቋ ቢሆን ወይም አማርኛ ብቻውን የስራ ቋንቋ ሆኖ ቢቀጥል በጠቅላላው በሀገሪቱ እና ጉዳዩ በሚመለከተው ብሄር ላይ ምን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎች ይኖሩታል? የጥያቄው አግባብነትስ ምን ያህል ነው? ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃርስ ተግባራዊ ሊሆን ይችላልን? የሚሉትን ጥያቄዎች መፈተሸ ተገቢ ይሆናል፡፡

(ቻላቸው ታደስ በድምፅ ያዘጋጀውን ዝርዝር ዘገባ እዚህ ያድምጡ)


የሀገራችን ህገመንግስት ለሁሉም ቋንቋዎች እኩል እውቅና ቢሰጥም አማርኛን ግን በተናጥል የፌደራል መንግስቱ ለአስተዳደራዊ ስራ የሚጠቀምበት የስራ ቋንቋ አድርጎታል፡፡ በወቅቱ የተሰጠው ምክንያትም ቋንቋው በታሪክና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በርካታ ተናጋሪዎችን ማፍራት መቻሉ ነበር፡፡ ስለሆነም ሀገሪቱ ህብረ ብሄራዊ ከመሆኗ አንፃር በብሄራዊ ቋንቋ ፋንታ አንድ የስራ ቋንቋ ብቻ ቢኖራት እምብዛም አይደንቅም፡፡
ህገመንግስቱ ክልሎች የራሳቸውን ቋንቋ እንዲወስኑ ስለፈቀደላቸው ትላልቅ ክልሎች የሆኑት አማራ ክልል አማርኛን፣ ኦሮሚያ ክልል ኦሮምኛን፣ ትግራይ ትግሬኛን እና ሱማሌ ክልል ደግሞ ሱማሊኛን የስራ ቋንቋቸው አድርገዋል፡፡ የአንድ ቋንቋ ግልጽ የሆነ የበላይነት የማይታይባቸው ደቡብ፣ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ክልሎች ግን በፍቃዳቸው አማርኛን የስራ ቋንቋቸው አድርገዋል፡፡
የፌደራል መንግስቱ የራሱን ስራው የሚያከናውነው እንዲሁም ከክልሎች ጋር ላለው ግንኙነት አማርኛን ይጠቀማል፡፡ ክልሎች እርስበርሳቸው ለሚያደርጉት የስራ ግንኙነትም አማርኛን ይጠቀማሉ፡፡ በፌደራል መንግስቱ ስር ያሉት አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ እንዲሁ፡፡ ስለሆነም ቋንቋው በታሪካዊ ተጠቃሚነቱ እና አሁን ባሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ሳቢያ ብሄራዊ መግባቢያ ወይም “ሊንጓ ፍራንካ” (lingua franca) ሆኗል ብለው የሚከራከሩ ምሁራን ቀላል አይደሉም፡፡

በእርግጥ በሀገራችን ተጨማሪ የፌዴራል ቋንቋ ስለሚኖረው ጠቀሜታ እና ጉዳት በኢትዮጵያዊያንም ሆነ በውጭ ሀገር ምሁራን ብዙ ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በቁጥር አብላጫ ያለው የኦሮም ህዝብ ቋንቋ የሆነው ኦሮምኛ ከአማርኛ በተጨማሪ የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ይሁን የሚል ጥያቄ ጎልቶ መምጣት ጀምሯል፡፡ በተለይ በውጭ በሚገኙ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች አማካኝነት፡፡ ከፖለቲካ ድርጅቶች መካከልም በስደት የሚገኘው የአቶ ሌንጮ ለታ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ጥያቄውን ያስተጋባል፡፡

በሀገር ውስጥም ተቃዋሚው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ የህዝብ ቁጥርን መሰረት በማድረግ ኦሮምኛን አማራጭ የፌደራል የስራ ቋንቋ ለማድረግ እንደሚታገል ሲገልፅ ይሰማል፡፡ በአንፃሩ የኦሮሚያ ክልልን የሚያስተዳድረው ኦህዴድ “ቋንቋችን የፌደራል የስራ ቋንቋ ለመሆን ገና በደንብ አላደገም፤ ወደፊት ኢኮኖሚያችን ሲያድግ እናስብበታልን” የሚል አቋም ይዟል፡፡ ምንም እንኳ የራሱ የድርጅቱ እውነተኛ አቋም ስለመሆኑ በእጅጉ አጠራጣሪ ቢሆንም፡፡
ከዓመታት በፊትም ተቃዋሚ የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የስራ ቋንቋው አማርኛ በሆነው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በኦሮምኛ ቋንቋ መናገራቸው በህግ አውጭው አካል የሚነሱትን አጀንዳዎችም ሆነ የሚወሰኑትን ውሳኔዎች የማይሰሙ በርካታ ኦሮሞዎች መኖራቸውን ለማስገንዘብ እና የቋንቋ ፖሊሲ ጉዳይ አሳሳቢ ስለመሆኑ መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልገው እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡
የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ቋንቋ ሰዎች ለመረጃ፣ ለትምህርት እና ለሌሎች እድሎች ያላቸውን ተደራሽነት ይወስናል፡፡ ከዚህም በመነሳት የጥያቄው ደጋፊዎች የኦሮሞ ህዝብ ሃሳቡን በነፃነት የመግለፅ ሰብዓዊ መብቱ በተሟላ ሁኔታ እንዲከበር የፌደራል ስራ ቋንቋ መሆን እንዳለበት ይገልፃሉ፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ የሚታተም ነፃ ፕሬስም ሆነ የግል ሬዲዮ ጣቢያ ላለመኖሩም ሰበብ የሚያደርጉት የቋንቋውን ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ ቋንቋው የስራ ቋንቋ ቢሆን በመንግስት ባለቤትነት የተያዙት መገናኛ ብዙሃን በሙሉ ከአማርኛ ቋንቋ በእኩል ኦሮምኛን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለሆነም እንዚህ ወገኖች ከመንግስትም ድጎማ ስለሚያገኝ እስካሁን የተገታው ዕድገቱ ይፋጠናል ብለው ይከራከራሉ፡፡
እያንዳንዱ ሀገር የራሱ ታሪካዊና ነባራዊ ባህሪያት ቢኖሩትም የአጀንዳው አቀንቃኞች ግን የሌሎች ሀገሮችን ልምድም ሲጠቀሱ ይታያል፡፡ የፌደራል ስርዓት ያላቸው ካናዳ እና ህንድ ሁለት፣ ስዊዘርላንድ እና ቤልጄዬም ሦስት፣ ደቡብ አፍሪካ አስራ አንድ የስራ ቋንቋዎች መጠቀማቸው እንደመከራከሪያ ያቀርቡታል፡፡

በሌላ ወገን ያሉ ምሁራን ደግሞ የስራ ቋንቋ መብዛቱ ለሀገሪቱ እድገትና አንድነት ብሎም አንድ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንቅፋት ይሆናል ይላሉ፡፡ በናይጀሪያም ቢሆን አናሳ ብሄሮች በሚያነሱት ቅሬታ ሳቢያ የቋንቋ ፖሊሲው ብሄራዊ መግባባት መፍጠር አልቻለም፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያም አንድን ቋንቋ ብቻ መጠቀሙ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ከማፋጠንም ሆነ ከአዋጭነቱ አንፃር ጠቃሚ መሆኑንያስረዳሉ፡፡

በእርግጥም ኦሮምኛ የስራ ቋንቋ ቢደረግ መንግስት ህገመንግስታዊና የፖሊሲ ማሻሻዎችን ለማድረግ ይገደዳል፡፡ በተለይ በትምህርት ተቋማት ሲተገበር ደግሞ ከፍተኛ ወጪ መጠየቁ ብቻ ሳይሆን በተግባርም የመቻሉ ነገር አጠራጣሪ ይመስላል፡፡
ለመለስተኛ ጥያቄዎች እንኳ የሃይል ምላሽ ሲሰጥ የኖረው መንግስት እንዲህ ዓይነቱን ግዙፍ ጥያቄ ለማስተናገድ የሚችልበት ዴሞክራሲያዊ መዋቅርና ባህሪ እንደሌለው እሙን ነው፡፡