Gedion Timotiwos , MoJ Photo Credit AFP

ዋዜማ ራዲዮ – ባለፉት ሶስት አመታት በመላ አገሪቱ በተከሰቱ የብሔርና የእምነት ተኮር ግጭቶች ጋር በተያያዘ ከ10ሺህ በላይ ሰዎች ክስ እንደተመሰረተባቸው ግን ደግሞ የፍትሕ ሂደቱ የተሳካ እንዳይሆን የፖለቲካ መዋቅሩ እክል መፍጠሩን የፍትሕ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡


በዚህ ሂደት ውስጥ ክስ የተመሰረተባቸው ወንጀሎች በመደበኛው የወንጅል የፍትህ አካሄድ ክስ ተመሰርቶ ወንጀሎችን ለማጣራትና ክስ መስርቶ ለመሄድ የተደረገው ሙከራ ፍትህን ለማረጋገጥ አስችሏል ተብሎ በቂ ሁኔታ ለመግለጽ አያስደፍርም ማለታቸውን የዋዜማ ሪፖርተር ዘግቧል።


ሚንስትሩ ለዚህ እንደእንቅፋት አድርገው በዋነኝነት የተጠቀሱት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራው እንደምንም አልቆ ክስ ቢመሰረትባቸው እንኳ ከምርመራው ጀምሮ በየአካበቢው ያለው ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛና በወንጀሉ የተሳተፈ የአስተዳድር አካል ተጠርጣዎቹ እንዳይያዙና ምርመራው እንዳይሳክ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል፡፡


በብዙ ጥረት ተጠርጣሪዎቹ ተይዘው የክስ ሂደቱ ሲቀጥል ምስክሮች እንዳይቀርቡ ጫና ስለመደረጉ ፣ እንዲሁም መርማሪውና ከሳሹ የፌደራል ፖሊስና አቃቢ ህግ ቢሆንም እንኳ ዳኛው የክልሉ በመሆኑ ይህ የክልል ዳኛ ላይ ክልሎች የተለያየ የፖለቲካ ጫና በማድረግ በጣም ትልቅ ወንጀል የፈጸመውን ሰው ቅጣቱን አቅልለው ሲለቁ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡


በዚህ የተነሳ ባለፉት ሶስት አመታት የነበረውን ልምድ በማየት ሰውን በመክሰስ ብቻ ፍትህን ማስፈን እንደማይቻል በመረጋገጡ የሽግግርና የተሃድሶ ፍትህ በማስፈን ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ይቻል ተብሎ መታሰቡን ገልጸዋል፡፡


የፍትህ ሚንስትሩ ይህን የተናገሩት የተቋማቸውን የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከየካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ለዕረፈት ለሚወጣው 6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሐሙስ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም ባቀረቡበት ወቅት ነበር፡፡
ሚንስትሩ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት መንግስት ከሶስት ሳምንታት በፊት ጉዳያቸው በህግ እየታየ የነበሩ የህወሓትና ሌሎች ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች መፈታት ከፓርላማ አባላቱ በርካታ ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር፡፡


የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ ክስ በተቋረጠላቸው ሰዎች መዝገብ ላይ የሚገኙ አካላት በዘር ማጥፋትና በጅምላ ፍጅት የተሳተፉ ግለሶቦችን ወንጀል የማቋረጥ ስልጣን አዋጁ ይሰጣል ወይ ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡


አክለውም እነዚህ ወንጀሎች በባህሪቸው አለማቀፍ ከመሆናቸውም በላይ ግለሰቦቹ የተያዙት ቤታቸው ተቀምጠው ሳይሆን ቆላ ተንቤን በረሃ ውስጥ በመሆን ከሌሎች አጋር የጦር አመራሮች ጋር የጦር ትዕዛዝ ሲሰጡ እንደነበርና ወጣቶችን በማሰልጠን አንድ ማህበረሰብን እየጠቀሱ በዚያ ህዝብ ላይ ጅምለ ጭፍጨፋና ዕልቂት እንዲፈጸም የጦር ማነሳሳትና ትዕዛዝ የሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡


በመሆኑም በህዘብ ላይ ጅምላ እልቂት የፈጸሙ አካለትን እንዴት ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ተለቀዋል ሊባል ይችላል? ሲሉ ሚንስቴሩን ጠይቀዋል፡፡ አክለውም ውሳኔው በተጎጅዎችና በጅምላ የተጨፈጨፉት ሰዎች ላይ ክህደት እንደተፈጸመ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል፡፡


‹‹በዚህ ጉዳይ በማህበረሰቡ ዘንድም ሆነ ምክርቤት ላይ ጥያቄ መነሳቱ እኛም የምንጠብቀው ጉዳይ ነው›› ያሉት የፍትህ ሚንስትሩ ክሱ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠባቻው ሁለት መዝገቦችና በከፊል የተቋረጠላቸው ስድስት ሰዎች ‹‹ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑና አነሰም በዛም ደጋፊ ያላቸው ታዋቂ የሆኑ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ አመራሮች ›› ክስ ቢቋረጥ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች በሚደረገው ምክክር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ ቢሆኑ የምክክር ሂደቱን አካታችና ውጤታማ በማድረግ ተዓማኒነቱን ሊያሳድጉ ይችላሉ ብለዋል፡፡በመሆኑም ውሳኔው ዘላቂ አገራዊ መፍትሄ ለማምጣት ታስቦ የተደረገ እንደሆነ አብራተዋል፡፡


ሚንስትሩ አክለውም በአዋጅ ቀጥር 943/2008 ዓ.ም. መሰረት ለህዝብ ጥቅም ሲባል ክስ እንዲቋረጥ የተወሰነባቸው አካላት ላይ መዝገቦቹ ሲደራጁና ምርመራው ሲሰራ የተለፋው ልፋትና የተደረገው ጥረት በጣም ከባድ እንደሆነ በመግለጽ እነዚህን መዝገቦች ሲመረምሩ የነበሩ አቃቢ ህጎችና ፖሊሶች ከፍተኛ ዛቻ እንዲሁም ምስክሮች ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡


የመንግስት ውሳኔ የረጅም ጊዜ ጥቅም ያስገኛል ተብሎ የተወሰነ እንደሆነ የገለጹት ጌዲዮን (ዶ/ር) በምርመራና ክርክር ወቅት ብዙ ተግዳሮትና ጫና ተቋቁሞ ምርመራ ሲያደርግ የነበረ ባለሙያና ተቋም እንደዚህ አይነት ውሳኔ ላይ መድረስ ደስ እያለውና ወይም ቀድሞ የሚደርስበት ውሳኔን እያወቀና ፈልጎት የሚያደርገው አልነበረም ብለዋል፡፡


በተጨማሪም ተጎጅ ተብለው የተለዩ ወገኖች ጉዳያቸውንና እንዲሁም ፍትህን በአንድ ወገን በማስቀመጥ ሲታይ ውሳኔው ‹‹የሚያም፣ የሚቆረቁርና የሚጎረብጥ ነገር ቢኖረውም›› አገራዊ የሆነውን ሊገኝ የሚችል ዘላቂ የሆነ ጥቅምን ግምት ውስጥ በማስገባት እንደተወሰነ ተናግረዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]