kality 2ዋዜማ ራዲዮ-ቀደም ብለው ተመዝግበው በትያትሩ የልምምድ አዳራሽ መቀመጫ ለማግኘት የታደሉ እድምተኞች በእንግዳ መቀበያው አዳራሽ ሞልተው የልምምዱን መጀመር ይጠብቃሉ። የትያትሩ አዘጋጅ ከልምምዱ መጀመር ቀደም ብለው ወደ እንግዳ መቀበያው አዳራሽ በመምጣት ለታዳሚዎቹ ስለቲያትሩ ማብራርያ ሲሰጡ በጉጉት የሚያዳምጣቸው ታዳሚ ትኩረት ራሱን የቻለ አስገራሚ ትእይንት ነው። አፕሪል 4 የሚከፈተው ”ቃሊቲ” የተሰኘው ቲያትር ከመጀመሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በነበሩ የቲያትሩ ልምምዶች ላይ ሁሉ የሚታይ ዝግጅት ነበር። ይህ እንግዲህ ስቶክሆልም ከተማ ለመድረክ የሚቀርበው ”ቃሊቲ” ምን ያህል በጉጉት የሚጠበቅ መኾኑን የሚያመለክት ነገር ነው።

ያዲሳባ ጥጓ ቃሊቲ የእስረኞቿ የስቃይና የመከራ ታሪክ ከቅጥሯ አልፎ ሳይወጣ ውጣ ስታስቀር ኖራለች። ከነክብራቸው በሯን አልፈው የገቡትን ሁሉ ከሰውነት ተራ አውጥታ እንደከብት አጉራ፥ ምህረት በሌላቸው የወህኒ ግፈኞቿ ስታስገርፍ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከነሙሉ ጤናቸው ገብተው ተሰብረው የተለቀቁት የስቃይ ሰለባዎቿ ምን እንደተፈጸመባቸው ለማውራት እንኳ ሰበአዊ ክብራቸው እየተናነቃቸው ችግሩ ያልደረሰበት ሰው በደፈናው ከሰማው የስቃይ አይነት ያልሰማው እንደሚልቅ እንዲገምት ብቻ ይገደዳል።

ይህ ክፉ ዝናዋ ግን ተደብቆ የሚቀር አልኾነም። በየጊዜው በክፉ ከሚያነሷት የሰበአዊ መብት ሪፖርቶች በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትጠቀስበት አጋጣሚ አልፎ አልፎም ቢኾን ይከሰታል። የኢትዮጵያ መንግስት በአገር ውስጥ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎች ላይ እንደለመደው፥ ከስድስት ዓመት በፊት ሁለት ስዊድናውያን ጋዜጠኞችን አስሮ ቃሊቲ አውርዶ ነበር። ማርቲን ሺቢን እና ዮሐን ፓርሾንን።  የኢትዮጵያ መንግስት በሌሎች ጋዜጠኞች ላይ እንደሚያደርገው ሁሉ በሽብርተኝነት ከሶ 11 ዓመት እስራት ከፈረደባቸው በኋላ ”በምህረት” ከለቀቃቸው አራት ዓመት አለፈ። የኢትዮጵያ መንግስት እነኚህን ሁለት ጋዜጠኞች ማሰሩ እስከዛሬ ሲደብቀው የኖረውን የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ የሚያጋልጡ ምስክሮች እስከጓዳው ድረስ እያስገባ እንደነበረ የታወቀው አይመስልም።

የጋዜጠኞቹ መታሰር የኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጽማቸውን የሰበአዊ መብት ጥሰቶች፥ የጸጥታ ኃይሎቹ መረጃ ለመፈብረክ በእስረኞች ላይ የሚያደርሱት ስቃይ እና አሳፋሪውን የአገሪቱን የፍርድ ስርዓት፥ ከዚያም አልፎ አስቂኙን የምህረት አሰጣጥ ዓለም ሁሉ እንዲያየው ኾኗል። ጋዜጠኞቹ በራሳቸው ላይ ከደረሰው በተጨማሪም የሌሎቹን እስረኞች ሕይወት ለማየትና ስቃያቸውን ለመካፈል አስችሏቸዋል። ማርቲን እንደሚለውም በቃሊቲ ያሳለፉት ጊዜ እነርሱ ከተለቀቁም በኋላ እስካሁን በእስር ቤት የቀሩት የሙያ አቻዎቻቸው የኾኑት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ስቃይ ሊረሱት በማይችሉት ኹኔታ በኅሊናቸው እንዲታተም አድርጎታል። ይህንንም የቃሊቲ የስቃይ ታሪክ ለመላው ዓለም ማሳወቅ የዋነኛው የሕይወታቸው ተልዕኮ አካል አድርገው ይዘውታል።Kality 1

ከቃሊቲ እስር ከተለቀቁ ጀምሮ በስዊድን የመገናኛ ብዙኀን እየቀረቡ የኢትዮጵያውያኑን የኅሊና እስረኞች ሁኔታ አሰፍስፎ ለሚጠብቃቸው ስዊድናዊ ታዳሚ አስረድተዋል። በሺህ ኪሎሜትር እየተጓዙ፥ በብዙ መድረኮች እየቀረቡ የዚህችን የሰቆቃ ቤት የቃሊቲን ጉዳይ ደከመን ሳይሉ አስረድተዋል። ”438 Dagar” ወይም 438 ቀናት በመባል የሚታወቅ ዝነኛ መሐፍ አሳትመው መልእክታቸውን በሰፊው አስተላልፈዋል። በዚህ ሁሉ ንግግራቸው ግን ዋነኛው መልእክታቸው ”እኛ የሚሟገትልን ስላለን ተፈተናል። አሁንም በዚህ ስቃይ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ግን ልንረሳቸው አይገባም።” የሚል ነው።

ማርቲና እና ዮሐን ”ቃሊቲ ፋውንዴሽን ” የሚባል በዓለም ዙሪያ ይህን በመሰለ ስቃይ ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞችን የሚረዳ ድርጅትም አቋቁመዋል። ድርጅቱ ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች በእስር በነበሩ ጊዜ እነርሱን እና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት በስዊድን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማኅበር አማካኝነት ተሰብስቦ በነበረው የእርዳታ ገንዘብ እና ”438 ቀናት” ከሚባለው መጽሐፋቸው የሚገኘው ገቢ የሚደጎም ድርጅት ነው። የድርጅቱን ዓላማ የሚደግፉ ሰዎች የሚያዋጡትም ገንዘብ ለዚሁ የድርጅቱ ዓላማ ይውላል።

ይህ ሁሉ ተግባራቸው ማርቲን እና ዮሐንን በስዊድን ትልቅ የታዋቂነት ስፍራ ሰጥቷቸዋል። እነርሱን የማያውቅ ስዊድናዊ መኖሩ እስከሚያጠራጥር ድረስ። እነርሱ ይገኙበታል የተባለ መንኛውም ጉባኤ በብዙ ክፍያም ቢኾን ትኬት ቆርጠው የሚገቡ ሰዎች ብዛት አስገራሚ ነው። ቃሊቲ የተባለውም ቲያትር የተወጠነውም በዚሁ ታዋቂነታቸው ምክንያት ነው።

በአንድ ወቅት በተለመደው የስራ ጉዞው ምክንያት ጎትላንድ በምትባለው የስዊድን ትልቋ ደሴት ላይ የተገኘው ማርቲን መንገድ ለይ ሰላም ከሚሉት ሰዎች መካከል ከአንዱ ጋር ውይይት ይጀምራል። ታሪኩን መስማቱንና ምን ያህል በታሪኩ ልቡ እንደተነካ ለሚነግረው ሰው ማርቲን  ”የኔ ታሪክ ምን ይገርምሃል አሁንስ በእስር የሚማቅቁ እስረኞች አሉ አይደል?” የሚል ምላሽ ይሰጠዋል። ይህ ሰው በስዊድን ብሔራዊ ትያትር የሚሰራና የቲያትር ባለሙያ መሆኑን ነግሮት እነዚህ እስረኞች ታሪካቸውን መጻፍ ይችሉ እንደኾን ይጠይቀዋል። ”የታሰሩትስ ለምን ኾነና ” የሚል ምላሽ የሰጠው ማርቲን በዚሁ ውይይታቸው ምክንያት ይህን የእስረኞቹን ታሪክ ወደቲያትር የመለወጥ ሐሳብ መወጠኑን ለዋዜማ አጫውቷል።

ከዚህ በፊት በቲያትር ተሳትፎ አድርጎ የማያውቀው ማርቲን ከሌሎች ባለሞያ (professional) ተዋንያን ጋር በመኾን በመድረኩ ላይ ይቀርባል። ይህን አዲስ ሙከራውን ሌላ አይነት የሰበአዊ መብት ተሟጋችነት ተደርጎ ሊወሰድ ይችል እንደኾነ ሲጠየቅ “የለም ይህ ተሟጋችነት አይደለም” ሲል አስረግጦ ይናገራል። “ ይህ ቲያትር የሚያሳየው የቃሊቲን በመሰለ ፈታኝ ሕይወት ውስጥ የሰወነትን ክብር ሳያስደፍሩ የመኖርን ትግል የሚያሳይ ኪን እንጂ ተሟጋችነት አይደለም። ” ይላል። የቲያትሩ አዘጋጅ ሞንስ ላገርለፍ ስለቲያትሩ ይዘት ሲገልጹ ይህንኑ የማርቲንን ሐሳብ ይደግማሉ “ይህን በመሰለ ስቃይ ውስጥም ኾኖ ሰው ኾኖ መቀጠልን እና ጋዜጠኛ ኾኖ መኖርን የሚያወሳ ነው።”

የቲያትሩ ይዘት ቀደም ሲል በቃሊቲ ታስረው የነበሩና አሁንም በእስርና በስደት ላይ ያሉ ጋዜጠኞች በጻፏቸው መልእክቶች ላይ የተመሰረተ ነው። በቲያትሩ ጽሑፋቸው የተካተተላቸው ጋዜጠኞች መካከል እስክንድር ነጋ፥ ርእዮት ዓለሙ፥ የትነበርክ ታደለ፥ አቤል ዋበላ፥ ማርቲን ሺቢይ፥ ጫላ ኃይሉ፥ ዘላለም ክብረት፥ ዮሐንስ ካሳሁን እና ሌሎች ብዙ ጋዜጠኞችና ጦማሪዎች ይገኙበታል።

በቲያትሩ መግቢያ አካባቢ የርዕዮት ዓለሙ ጽሑፍ በእንግሊዘኛ ከመነበቡ በቀር የሌሎቹ ጋዜጠኞች ጽሑፍ እና ሌሎቹ የትያትሩ ክፍሎች በስዊድንኛ ተተርጉመው የቀረቡ ናቸው።

ከማርቲን ሺቢይ በተጨማሪ በትያትሩ ላይ የሚተውኑት ሁለቱ ተዋንያን አንጀሊካ ራድቮልት እና ዴቪድ ለነማን ከዋዜማ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከዚህ በፊት ስለኡትዮጵያ የነበራቸው እውቀት ውሱን ቢኾንም በቲያትሩ ምክንያት ስለ ኢትዮጵያ ብዙ መስማት እንደጀመሩ ይናገራሉ። ከኢራን ከመጡ ስደተኞች የተወለደችው አንጀሊካ የቲያትሩ ሐሳብ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ኢራንን ከመሰሉ ተመሳሳይ ችግር ካለባቸው አገራት ከመጡ ሰዎችም ሕይወት ጋር የሚያዛምደው ሐሳብ እንዳለው ትናገራለች።

በተለይ የዞን ዘጠኙ አቤል ዋበላን የሚመለከቱ ክፍሎች ላይ የሚተውነው ዴቪድ ሌነማን የአቤል ታሪክ ልቡን እንደነካው ይናገራል። በሌሎቹ እስረኞች ታሪክ ውስጥ የሚንጸባረቀውንም በስቃይ ውስጥ ኾነው ያለመበገር ባሕርይ እንደሚያደንቅ ዴቪድ ይናገራል።

የትያትሩ አዘጋጅና ተዋንያን የማርቲ ሺቢይ ታሪክ የሚስባቸው ብዙ ስዊድናውያን ትያትሩን ለማየት እንደሚመጡ ይጠብቃሉ። ያም ኾኖ በስቶክሆልምና አካባቢዋ ያሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ቲያትሩን ቢያይላቸው ደስ እንደሚላቸውም ለዋዜማ ተናግረዋል።