ዋዜማ ራዲዮ- ሰማያዊ ፓርቲ እና የመላው ኢትዮጵይ አንድነት ፓርቲ ወደ ውህደት የሚወስዱ ስራዎችን በጋራ ለማከናወን  የስምምነት ፊርማ ዛሬ (ሀሞስ) በመኢአድ ቢሮ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ ወደ ሙሉ ውህደት አልያም ጥምረት ያደርስናል ብለዋል ፓርቲዎቹ።
ሁለቱ ፓርቲዎች  ባለፉት 4 ወራት ስድስት አባላት ያለው የጋራ ኮሚቴ ከሁለቱም ፓርቲ መርጠው ሲሰሩ መቆየታቸውን የኮሚቴው ሰብሳቢና የመኢአድ ዋና ፀሐፊ አቶ አዳነ ጥላሁን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም እንደተደረጉት አይነት የፓርቲዎች ቅንጅት አይነት እንዳይሆን ግንኙነታችን በሰፊው በመጠናናት ወደ ውህደት አሊያም ቅንጅት መሄድን ስለመረጥን መጠናናቱ ላይ ልዩ ትኩረት መስጠትን መርጠናል ሲሉም አቶ አዳነ ገልፀዋል።

በቅርቡ የምታስቡትን ለማሳካት ትችላላችሁ ወይ?  የተባሉት ሀላፊው “ሁኔታዎች በሚመሩን መሰረት እንጓዛለን ሌሎች ውጫዊ ጫናዎችም ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ሊፈጥሩ ስለሚችሉ በዚህ እለት ያሰብነውን እናደርጋለን ብለን ለመናገር ይከብዳል” ብለዋል ።

መኢአድና ሰማያዊ በጋራ እንሰራለን ብለው መነጋገር ከጀመሩ ሁለት አመት አካባቢ ሆኖታልና አሁንም ገና እንጠናናለን ማለቱ ግንኙነቱ የማይሆን መሆኑን የሚያመለክት ነው ተብሎ ቢያስተቸው ልክ አይሆንም ወይ?  የተባሉት ሀላፊ ” እስከ አሁንም የቆየነው ዝርዝር ጉዳዮችን ስንነጋገር ነው ግንኙነታችን ሳንካ እንዳይገጥመው በመፍራት እንጂ በፕሮግራምና መሰረታዊ በሚባሉ ነጥቦች ጭምር ከስምምነት ደርሰናል” ብለዋል ።

የአሁኑ የአብረን እንስራ የቅድመ ውህደት ስምምነት የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ከማንም ወገን የእውቅና ፈቃድ አይጠየቅበትም ተብሏል።
ሁለቱ ፓርቲዎች የቅድመ ውህደት የስምምነት ስራዎች ብለው ከጠቀሷቸው ነጥቦች መሀከልን አባላትን በጋራ መመልመል፣ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለውን መዋቅራቸውን ማዋሀድድ፣ የፕሮግራም ይዘታቸውን ማቀራረብ የሚሉት ይገኛሉ ።

ፓርቲዎቹ  በውህደት ደረጃ ወደ አንድ ፓርቲነት ለመጠቃለል የሚወስኑ ከሆነ የስያሜና የፓርቲ የአመራር አባላት ጥያቄ ጉዳይ መሰረታዊው አጀንዳ ስለሚሆን ምርጫም ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዋዜማ ምንጮች ገልፀዋል።

ሁለቱም ፓርቲዎች (ሰማያዊና መኢአድ) በውስጣዊ ሽኩቻና ውዝግብ ሲታመሱ ቆይተው አመራሮቻቸውን በአዲስ መተካታቸው ይታወቃል።